ብሩናይ 

0
126

ዳሩ ሠላም ብሩናይ በደቡብ ምሥራቅ እስያ የምትገኝ በነዳጅ እና በተፈጥሮ ጋዝ ሀብቷ የምትታወቅ ሀገር ናት። ዋና ከተማዋ ባንዳር ሴሪ ቤጋዋን ትባላለች፡፡

ብሩናይ አምስት ሺህ ሰባት መቶ ስልሳ አምስት ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚገመት የቆዳ ስፋት አላት፡፡ የሀገሪቱ ከፍተኛ ቦታ ፓጎን ፒክ ነው ፤ 6 ሺህ 70 ጫማ  (1 ሺህ 850 ሜትር)  ከፍታ አለው።

ዳሩ ሠላም ብሩናይ በሁለት ሺህ ሀያ ስድስት ግምታዊ መረጃ መሠረት 465 ሺህ 600 ያህል ነዋሪዎች አሏት፤ ከሕዝቧ ውስጥ ከአንድ አምስተኛ በላይ የሚሆነው ዕድሜው ከ15 ዓመት በታች ነው፤ ግማሽ ያህሉ ደግሞ ከ30 ዓመት በታች ነው። አማካይ የሕይወት ዘመን ጣሪያ 78 ዓመት አካባቢ ነው፤ ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ ዶት ኮም ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው  መረጃ እንደሚጠቁመው፡፡

የብሩናይ የሥራ ቋንቋ ማላይ ይባላል፤ እንግሊዝኛም  ከማላይ ቀጥሎ  በስፋት ይነገራል፡፡

ብሩናይ በዓለማችን ላይ ከሚገኙት ጥቂት ንጉሣዊ (ሱልጣኔት) ሀገሮች አንዷ ናት። የብሩናይ ሱልጣን መኖሪያ የሆነው ኢስታና ኑሩል ኢማን ቤተ መንግሥት  ከ1 ሺህ 700 በላይ ክፍሎች አሉት፡፡ ይህም በዓለም ላይ በትልቅነቱ በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀስ  ቤተ መንግሥት ያደርገዋል፡፡ ቤተ መንግሥቱ በየዓመቱ በ”ሀሪ ራያ” (ዒድ) በዓል ወቅት ለሦስት ቀናት ለሕዝብ ክፍት ይሆናል፡፡ ሕዝቡ እንዲሁም ጎብኝዎች ወደ ቤተ መንግሥቱ በመግባት ከሱልጣኑ ጋር በመጨባበጥ ሰላምታ የመለዋወጥ እና የተዘጋጀውን ምግብ የመመገብ (ግብር የመብላት) ልዩ ዕድል አላቸው፡፡ ከሱልጣኑ ጋር ግብር በነፃ የመብላት ባህሏ በቀደመው ዘመን የሀገራችን ነገሥታት ሕዝቡን እየጠሩ ያበሉት የነበረውን ግብር  ያስታውሰናል፡፡

ዳሩ ሠላም ብሩናይ ስሟ እንደሚያመለክተው ፍጹም ሰላማዊ ሀገር ናት፡፡ ሕዝቧ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና የተረጋጋ የኑሮ ዘይቤን ይከተላል። አልኮል መሸጥም ኾነ መጠጣት በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡ የእስልምና ተከታይ ያልሆኑ ጎብኝዎች ለራሳቸው ፍጆታ ብቻ የሚሆን ጥቂት አልኮል አሳውቀው ይዘው መግባት ቢፈቀድላቸውም በሕዝብ መገልገያ ቦታዎች ላይ በሕዝብ ፊት መጠጣት አይችሉም።

ብሩናይ የእስልምና የሸሪዓ የወንጀል ሕግን በመተግበር በደቡብ ምሥራቅ እስያ የመጀመሪያዋ ሀገር ናት። የሸሪዓ የወንጀል ሕግን ከመደበኛው ሕግ ጎን ለጎን ትጠቀማለች። የሸሪዓ ሕጉ እንደ ስርቆት፣ ምንዝርና እና መሰል ከባድ ወንጀሎች ላይ እጅግ እጅን እስከ መቁረጥ፣ ከዚያም አልፎ እስከግድያ የሚደርሱ ጥብቅ ቅጣቶችን ይደነግጋል፡፡ ቅጣቶቹ በአድልኦ አይፈጸሙም፤ የሱልጣኔቱ ልጆች ላይም ተፈጻሚ ይሆናሉ፤ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ፡፡

ለዚህም አንድ አብነት ማንሳት ይቻላል፡፡

በቀድሞ ዘመን የሱልጣኑ ወንድ እና ሴት ልጆች ሲወሰልቱ ተገኝተው በሞት እንደተቀጡ ይነገራል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ቅጣቶቹ ተግባራዊ የሚሆኑት ወንጀሎች ስለመፈጸማቸው በተለያዩ ጥብቅ ማስረጃዎች ከተረጋገጠ ብቻ ነው፡፡

ብሩናይ በግዙፍ እና ውብ መስጊዶቿ እንዲሁም በባህላዊ እሴቶቿ ትታወቃለች። የማላይ ባህል በዋናነት በባህላዊ እሴቶች እና በእስልምና ሃይማኖት መርሆዎች ላይ የተመሠረተ ነው።

ዜጎቿ እጅግ ትሁት፣ ጨዋ እና እንግዳ ተቀባይ  ናቸው። ሰዎችን ማክበር እና ለቤተሰብ ትልቅ ቦታ መስጠት ባህላቸው ነው። በሰላምታ ወቅት እጅን ቀስ አድርገው ከጨበጡ በኋላ የጨበጡትን እጅ ወደ ልባቸው ያስጠጋሉ፡፡ ይህም በባህላቸው መሠረት የአክብሮት መግለጫ ተደርጎ ይታያል፡፡

የአለባበስ ሥርዓታቸውም በእስልምና ሕግጋት የተቃኘ ነው፤ ወንዶች “ባጁ መላዩ” የተባለውን ባህላዊ ልብስ፣ ሴቶች ደግሞ “ባጁ ኩሩንግ” የተባለውንና መላ አካልን የሚሸፍነውን ልብስ ይለብሳሉ።

ሙስሊም ያልሆኑ ዜጎች እና የውጭ ጎብኝዎች የራሳቸውን እምነት እንዳይከተሉ የሚፈጸምባቸው ጫና የለም፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከራሳቸው እምነት አልፈው የሌላ እምነት መጻሕፍትን በይፋ ማሠራጨት ወይም የሙስሊሙን ማሕበረሰብ ወደ ሌላ እምነት ለመቀየር መሞከር በሕግ ያስቀጣል።

ዳሩ ሠላም ብሩናይ በግርማ ሞገስ የተገነቡትን እንደ ሱልጣን ኦማር አሊ ሰይፉዲን ያሉ ባለ ወርቅ ጉልላት መስጊዶች ለማየት ለሚሄዱ ጎብኝዎች ተመራጭ ናት። በተጨማሪም በውኃ ላይ የተሠራው ግዙፉ መንደር እና የኡሉ ተምቡሮንግ ብሔራዊ ፓርክ ዋነኛ የመስህብ ሀብቶቿ ናቸው።

የውኃ ላይ መንደሩ ካምፖንግ አይር ይሰኛል፤ በማላይኛ ቋንቋ “የውኃ መንደር” ማለት ነው፡፡ የመንደሩ ቤቶች በሙሉ በብሩናይ ወንዝ ላይ በጠንካራ ምሶሶዎች የተገነቡ ናቸው። በጥንት ዘመን የቤቶቹ ግንባታ ይካሄድ የነበረው በሀገር በቀል እንጨቶች እና በቅጠል ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን በኮንክሪት እንዲሁም በዘመናዊ የግንባታ ቁሶች የተገነቡ ቤቶች በርካታ ናቸው።

የመንደሩን ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችን እና መስጊዶችን ርስበርስ የሚያገናኙ ከ29 ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝሙ የእንጨት እንዲሁም የኮንክሪት መንገዶች ተሠርተውላቸዋል፡፡ መንደሩ በውኃ ላይ የተሠራ ቢሆንም ልክ እንደ የብስ ከተማ ሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ፣ የአየር ማቀዝቀዣ፣ የቴሌቪዥን እና የከፍተኛ ፍጥነት በይነ መረብ መስመር አለው። በተጨማሪም መስጊዶች፣ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮች፣ የፖሊስ ጣቢያዎች እንዲሁም የነፍስ አድን ጀልባዎች ያሏቸው የእሳት አደጋ መከላከያ ጣቢያዎች አሉ።

በመንደሩ ውስጥ ምንም ዓይነት መኪና የለም። ዋናዎቹ የመጓጓዣ አማራጮች “የውኃ ታክሲዎች” በመባል የሚታወቁ ትናንሽ የሞተር ጀልባዎች ናቸው።

በመንደሩ ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች  ይኖራሉ። አብዛኛዎቹ ነዋሪዎች የማላይ ዝርያ ያላቸው ብሩናውያን ናቸው። ነዋሪዎቹ ከዘመናዊ ሥራዎች በተጨማሪ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሸጋገሩ እንደ ባህላዊ የሸክላ፣ የቅርጫት፣ የብር እና የናስ ሥራዎች፣ የጀልባ ግንባታ እንዲሁም ባህላዊ ኬኮች ማዘጋጀት ላይ ይተጋሉ።

መንግሥት ለነዋሪዎቹ በየብስ ላይ ዘመናዊ ቤቶችን ሰጥቶ ለማስፈር በተደጋጋሚ ቢሞክርም፣ ነዋሪዎቹ ከባህላቸው እና ከለመዱት የውኃ ላይ ማኅበራዊ ትስስር የተነሳ እዚያው መኖርን ይመርጣሉ።

“አምቡያት” (ከሳጎ ዛፍ ግንድ የሚዘጋጅ) ብሔራዊ ምግባቸው ነው፡፡ ይህን ምግባቸውን በጋራ ይመገባሉ፡፡ ይህም የአንድነትን እሴት የሚያሳይ ትልቅ ምሳሌ ነው።

የብሩናይ ባህላዊ ሙዚቃ በማላይ የሙዚቃ ስልት እና በባህላዊ መሣሪያዎች ላይ የተመሠረተ ነው። ከሙዚቃ መሣሪያዎቿ ጉሊንታንጋን (ትናንሽ የናስ ጎንጎች ስብስብ)፣ ሬባና (ከበሮ) እና አጉንግ ( ጎንግ) ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ቤላይት በሀገሪቱ ውስጥ ትልቁ ወንዝ ነው። ከሀገሪቱ ግዛት ውስጥ ሦስት አምስተኛ ያህሉ በትሮፒካል የዝናብ ደን የተሸፈነ ነው።  ምጣኔ ሀብቷ የተመሠረተው በነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ምርቷ ነው። ይህ ሀብቷ በዓለም ላይ ካሉ ባለጸጋ ሀገራት በሰባተኛ ደረጃ እንድትመደብ አድርጓታል።

ብሩናይ  ዜጎቿን የገቢ ግብር አታስከፍልም፤ በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችም ሆኑ የውጭ  ነዋሪዎች ከገቢ ግብር ነጻ ናቸው፡፡ መንግሥት ለዜጎቹ ነፃ የሕክምና አገልግሎት እና ነፃ የትምህርት ዕድል (እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ) ይሰጣል፡፡

የብሩናይ ሕዝብ በዓለም እጅግ ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ማኅበረሰቦች አንዱ ነው። የሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዋነኞቹ ተርታ ይመደባል፡፡ ይህም ዜጎች ከፍተኛ የመግዛት አቅም እንዲኖራቸው አድርጓል።

ከነፃ ትምህርት እና ሕክምና በተጨማሪ መንግሥት ለዜጎቹ የመኖሪያ ቤት ግዢን፣ የነዳጅ ዋጋን እና መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በከፍተኛ ሁኔታ ይደጉማል። ይህም የኑሮ ውድነት ጫና እንዳይኖር አድርጓል።

በብሩናይ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎት ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ቤተሰብ በአማካይ ከአንድ በላይ ቅንጡ የቤት መኪናዎች አሉት። ይህም የሆነው ነዳጅ በጣም ርካሽ እንዲሁም የመኪና ግዢ ቀረጥ አነስተኛ በመሆኑ ነው።

 

አጫጭር መረጃዎች

በዓለማችን ሰላም የሰፈነባቸው  አምስት ሀገራት

አይስላንድ

አይስላንድ ላለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ያህል በዓለማችን በአንደኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ እጅግ ሰላማዊ ሀገር ናት፡፡ ሀገሪቱ ቋሚ ወታደራዊ ጦር የላትም፡፡ የወንጀል መጠን እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ እና በሕዝቧ መካከል ባለው ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር ትታወቃለች፡

ኒው ዚላንድ

ኒው ዚላንድ በሰላማዊ ሀገርነቷ በዓለማችን ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ትገኛለች፡፡ በውስጣዊም ሆነ በውጫዊ ግጭቶች ውስጥ ፈጽሞ ባለመሳተፍ ፍጹም ሰላማዊ የሆነ የፖለቲካ መረጋጋት ያላት ሀገር ናት፡፡ እንዲሁም ለዜጎችም ሆነ ለጎብኚዎች ከፍተኛ የግል ደኅንነት ዋስትና በመስጠት ትታወቃለች፡፡

ስዊዘርላንድ

ስዊዘርላንድ በምትከተለው የገለልተኝነት ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትታወቃለች፡፡ በጦርነቶች ውስጥ የማትሳተፍ፣ ጠንካራ ሕግ እና ሥርዓት ያላት፣ የወንጀል መጠን እጅግ አናሳ የሆነባት፣ የፖለቲካ መዋቅሯ እጅግ የተረጋጋ የሰላም ተምሳሌት ሀገር ናት፡፡

ስሎቬኒያ

ስሎቬኒያ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በሰላማዊነቷ በፍጥነት እያደጉ ካሉና በእድገት በአራተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡ የአውሮፓ ሀገራት አንዷ ናት፡፡ ሀገሪቱ ለመከላከያ የምታወጣው ወጪ አነስተኛ ሲሆን፣ የተረጋጋ ማኅበራዊ ሕይወት፣ ዝቅተኛ የወንጀሎችና አስተማማኝ የሕዝብ ደኅንነት አላት፡፡

አየርላንድ

አየርላንድ በአምስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሰላማዊት ሀገር ስትሆን፣ ከዓለም አቀፍ  ግጭቶች ራሷን በማራቅ እና በታሪካዊ የእንግዳ ተቀባይነት ባህሏ ትታወቃለች፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ መረጋጋት ለሰላሟ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ምንጭ፡-‘’ቪዥን ኦቭ ሂዩማኒቲ ዶት ኦርግ’’

 

(ቦረቦር ዘዳር አገር)

በኲር የመስከረም 11 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here