በዓለም አትሌቲክስ ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያውያን የረጅም ርቀት ሯጮች ስም ሲነሳ ቀዳሚው ምስል የጽናት እና የድል ማማ ነው፡፡ ሀገራችን በሴቶች የረጅም ርቀት ሩጫ ያስመዘገበችው እና እያስመዘገበች ያለችው አኩሪ ገድል በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን በትውልዶች ልፋት እና ላብ የተገነባ ህያው ሀውልት ነው፡፡ ደራርቱ ቱሉ በባርሴሎና የጀመረችውን አኩሪ ታሪክ ጌጤ ዋሚ፣ ብርሀኔ አደሬ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር፣ አልማዝ አያና እንዲሁም ጉዳፍ ፀጋይ በድምቀት አስቀጥለውታል፡፡
ዛሬ ላይ ደግሞ ይህንን ታላቅ አደራ ተረክባ በዓለም መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጋ እያውለበለበች የምትገኘው ድንቋ አትሌት ልቅና አምባው መሆኗን የዓለም አትሌቲክስ መረጃዎች ይመሰክራሉ፡፡
አትሌት ልቅና አምባው የተወለደችው በምሥራቅ ጎጃም ዞን በቢቡኝ ወረዳ ልዩ ስሟ ሉባ ጊዮርጊስ በተባለች ውብ የገጠር መንደር ውስጥ ነው፡፡ ያደገችውም እዚሁ ደብረ ማርቆስ አቅራቢያ በሚገኘው የትውልድ ቀዬዋ ሲሆን፣ ህይወቷን በግብርና በሚመሩ ታታሪ ወላጆቿ እቅፍ ውስጥ ካሉት ሰባት ልጆች መካከል አራተኛ ሆና ነው ያሳለፈችው፡፡ የሩጫ ፍቅሯ እና ተፈጥሯዊ ተሰጥኦዋ መገለጥ የጀመረውም እዚሁ በገጠሪቱ መንደር ውስጥ ነበር፡፡ ትምህርት ቤት ለመድረስ በየቀኑ በባዶ እግሯ የምትሮጠው ረጅም ርቀት ሳታስበው ለሳምባዋ ጥንካሬ እና ለስኬታማ የሩጫ ህይወቷ የመጀመሪያው የተፈጥሮ ማሰልጠኛ ሆነላት፡፡ ይህች ከሉባ ጊዮርጊስ የተነሳችው ታታሪ እንቁ በጽናት ታግላ ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ የአምስት ሺህ ሜትር እና የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች ላይ ሀገሯን የምታስጠራ ጀግና ለመሆን በቅታለች፡፡
አትሌቷ እ.አ.አ ከ2019 ጀምሮ ላለፉት ሰባት ዓመታት ሙሉ ኑሮዋንም ሆነ ልምምዷን ያደረገችው በአውሮፓ ምድር በስፔን ውስጥ ነው፡፡ በተለይም ከ2022 እ.አ.አ ጀምሮ ባሉት አራት ተከታታይ ዓመታት ውስጥ በአውሮፓ የውድድር መድረኮች ላይ እጅግ ጠንካራ እና አቻ የማይገኝላት አሸናፊ ሆና መዝለቋን የዓለም አትሌቲክስ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ይህን ድንቅ ብቃቷን የተመለከቱ ስፔንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ዜግነቷን ቀይራ ለነርሱ እንድትሮጥ ከፍተኛ ገንዘብ እና የደላ ኑሮ ዋስትና አቅርበውላት ነበር፡፡ ልቅና ግን “የሀገሬን ባንዲራ በዓለም ፊት የማውለብለብ ህልሜን በምንም ገንዘብ አልለውጠውም” በማለት የቀረቡላትን የጥቅም ጥያቄዎች ሁሉ ወደ ጎን በመገፍተር በተስፋ የሀገሯን ጥሪ ስትጠባበቅ ቆይታለች፡፡
የኢትዮጵያን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ በዓለም ፊት የማውለብለብ ህልሟን በማስቀደም ለማንነቷ ያላትን ታማኝነት በተግባር አስመስክራለች፡፡ ይህ ጽኑ አቋሟ ከሯጭነቷ ባሻገር ምን ያህል ሀገር ወዳድ እና የሞራል ልዕልና ያላት ጀግና መሆኗን ለዓለም ያሳየ ታላቅ ምግባር ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የሚያስመዘግበው ውጤት ባሸቆለቆለበት እና ከፍተኛ የሜዳሊያ ድርቅ በተከሰተበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ልቅና አምባው ያስመዘገበችው ድል እጅግ የጎላ ትርጉም አለው፡፡ አትሌቷ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ በሁለት ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ለኢትዮጵያ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማስመዝገብ ችላለች፡፡
በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማህበር እውቅና በተሰጣቸው የወርቅ ደረጃ የሀገር አቋራጭ መድረኮች ላይ ልቅና ተከታታይ ድሎችን ተቀዳጅታለች፡፡ በተለይም በስፔን ምድር በሚካሄዱት የሶሪያ እና የአልኮቤንዳስ ታላላቅ ውድድሮች ላይ ኃያላን አትሌቶችን አስከንድታ ማሸነፏ አይዘነጋም፡፡ በቬንታ ዴ ባኞስ እና በአሞሬቢዬታ ጭቃማ ሜዳዎች፣ በከባድ ዳገቶች እና በአስቸጋሪ የአየር ፀባዮች ውስጥ የሚካሄዱትን ውድድሮች በበላይነት በማጠናቀቅ እውነተኛ የሀገር አቋራጭ ንግሥት መሆኗን በተግባር አረጋግጣለች፡፡
በጎዳና ላይ ሩጫም ቢሆን በአስር ኪሎ ሜትር ርቀት 29 ደቂቃ ከ56 ሴኮንድ በመግባት ታሪክ ጽፋለች፡፡ በዚህም ከ30 ደቂቃ በታች በመግባት በዓለም አቀፍ ደረጃ በፈጣን ሰዓት ከሚጠቀሱ ጥቂት የረጅም ርቀት ሯጮች ተርታ በክብር ስሟን አስመዝግባለች፡፡
አትሌቲክስ የጉልበት ስፖርት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የአዕምሮ ስሌትን እና የታክቲክ ጥበብን የሚጠይቅ የሳይንስ ዘርፍ ነው፡፡ ልቅና አምባው በውድድር መጀመሪያ ላይ ጉልበቷን በከንቱ አታባክንም፡፡ ከተፎካካሪዎቿ ጀርባ በመደበቅ የንፋስ ጫናን ትቀንሳለች፤ የውድድሩን ፍጥነት እያጠናች ኃይሏን ቆጥባ ትጓዛለች፡፡ ውድድሩ ሊጠናቀቅ ጥቂት መቶ ሜትሮች ሲቀሩት ደግሞ ተፎካካሪዎቿ ሊቋቋሙት የማይችሉትን ፈጣን ፍጥነት (Kick) በመጨመር ልዩነት ትፈጥራለች፡፡ ይህ ስልቷ የቀደምት ጀግኖቻችንን የሩጫ ጥበብ ህያው ያደረገ ነው፡፡
የአትሌት ልቅና አምባው የወደፊት ተስፋ እጅግ ብሩህ እና የሚያጓጓ ነው፡፡ አትሌቷ ያላት ድንቅ የተፈጥሮ ብቃት እና ፈጣን የመጨረሻ አጨራረስ ለቀጣዮቹ ታላላቅ ሻምፒዮናዎች ትልቅ መደላድል ጥሏል፡፡
በቀጣይ በሚካሄዱት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና የኦሎምፒክ መድረኮች ላይ በአምስት እና በአስር ሺህ ሜትር የትራክ ውድድሮች ለሀገራችን የወርቅ ሜዳሊያዎችን እንደምታስገኝ ሰፊ ግምት ተሰጥቷታል፡፡ በተጨማሪም ወደ ግማሽ ማራቶን እና ሙሉ ማራቶን በመሸጋገር ክብረ ወሰኖችን የማሻሻል ታላቅ አቅም እንዳላት ይነገራል፡፡
ልቅና እንደ ደራርቱ ቱሉ እና ጥሩነሽ ዲባባ ያሉ ታላላቅ ጀግኖችን ፈለግ በመከተል በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ አድርጋ ለማውለብለብ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሰራች ትገኛለች፡፡ ይህች ከሉባ ጊዮርጊስ መንደር የተነሳችው ብርቱ አትሌት በቀጣይም የዓለምን የስፖርት መድረክ በበላይነት እንደምትመራው እና ታሪክ እንደምትሰራ ሙሉ እምነት ተጥሎባታል፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የመስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


