በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ50ሺህ እስከ 60ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ውሻን በሚያሳብድ በሽታ ይሞታሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በእስያ እና በአፍሪካ አህጉራት የሚገኙ ሕፃናት ናቸው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ፣ የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት እና ሌሎች ተቋማት ውሻን የሚያሳብድ በሽታን እ.አ.አ. እስከ 2030 ከዓለማችን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት “ዚሮ ባይ ሠርቲ” በሚል መርሃ-ግብር እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
በሰሜን አሜሪካ እና በምዕራብ አውሮፓ በውሾች ላይ በተደረገ ሰፊ የክትባት ዘመቻ ምክንያት ከቤት እንስሳት የሚመጣ ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ጠፍቷል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በታዳጊ ሀገራት ግን የባለቤት አልባ ውሾች መብዛት፣ የእንስሳት ክትባት እጥረት እና በግንዛቤ ማነስ ምክንያት በሽታው አሁንም ከፍተኛ የሕዝብ ጤና ሥጋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ውሻን የሚያሳብድ በሽታ በኢትዮጵያ
በኢትዮጵያ ባህላዊ ሕክምና ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ከጥንት ጀምሮ ይታወቃል፡፡ በሕዝቡ ዘንድም “ውሻን የሚያሳብድ በሽታ” ወይም “የውሻ እብደት” በመባል ይታወቃል፡፡ ዘመናዊ ሕክምና ከማደጉ በፊት እስከ ዛሬም ድረስ በአንዳንድ አካባቢዎች ሕብረተሰቡ የዕፅዋት ቅጠሎችን፣ ስሮችን እና ልዩ ልዩ ባህላዊ መድኃኒቶችን በመጠቀም በሽታውን ለመከላከል ወይም ለማከም ይሞከራል፡፡
በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ደግሞ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሕክምና ተቋማት መመስረት ሲጀምሩ ከቀደሙት የሕዝብ ጤና ስጋቶች አንዱ ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ነበር፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የፓስተር ኢንስቲትዩት በ1944ዓ.ም (በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትተብሎ የሚጠራው ተቋም – EPHI) ሲቋቋም የመጀመሪያው እና ዋናው ትኩረቱ ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ክትባትን ማምረት እና ምርምር ማካሄድ ነበር፡፡
የጤና ሚኒሥቴር እና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ውሻን በሚያሳብድ በሽታ ከፍተኛ የሰው ሕይወትን ከሚያጡ ሀገራት አንዷ ሆና ቆይታለች፡፡ በየዓመቱም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በውሻ ይነከሳሉ፤ ተገቢውን የክትባት ሕክምና ያላገኙ በርካታ ዜጎች ደግሞ ለሞት ይዳረጋሉ፡፡
በአማራ ክልል ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ያለበት ሁኔታ
ከክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው ውሻን የሚያሳብድ በሽታ በክልሉ ከፍተኛ የሕብረተሰብ ጤና ስጋት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2018 ዓ.ም አምስተኛ ወር ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ በክልሉ በአጠቃላይ 56ሺህ 959 ሰዎች ውሻን በሚያሳብድ በሽታ የተጋለጡ ሲሆን 272 ሞት ተመዝግቧል፡፡ የተመዘገበው የሞት ቁጥር በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚከሰቱና ሪፖርት የማይደረጉ የሞት አደጋዎችን ያካተተ ባለመሆኑ ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ይገመታል፡፡
በሽታው በተለይ ከፍተኛ የሰው ቁጥርና በጎዳና ላይ የሚልከሰከሱ ባለቤት አልባ ውሾች በብዛት በሚገኙባቸው ከተሞች ተስፋፍቷል፡፡ ለአብነትም በባሕር ዳር 6ሺህ 668 እንዲሁም በጎንደር ከተማ 5ሺህ 950 ሰዎች ውሻን በሚያሳብድ በሽታ ተጋልጠው ተገኝተዋል፡፡ የውሻ ክትባት ሽፋን ዝቅተኛ መሆንና ከንክኪ/ተጋላጭነት በኋላ የሚሰጠው የድኅረ-ንክኪ/ተጋላጭነት መከላከያ ክትባት እጥረት ዋነኛ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ከክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተቋም ያገኘነው ማስረጃ ይጠቁማል፡፡
ለመሆኑ ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ምንድን ነው?
ውሻን የሚያሳብድ በሽታ (ራቢስ/Rabies) በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ፣ በማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓት እና በአንጎል ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ አጣዳፊ ተላላፊ በሽታ ነው፡፡ ቫይረሱ አንዴ ወደ አንጎል ደርሶ ምልክቶች መታየት ከጀመሩ በኋላ በሽታው መቶ በመቶ ለሞት ይዳርጋል፡፡
የበሽታው መተላለፊያ መንገዶች
በአማራ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የአንድ ጤና ምልከታ ሴክረታሪ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ቢረሳው ታዛዬ እንደገለጹት በበሽታው የተያዘ እንስሳ (በተለይ ውሻ) ሰውን ሲነክስ ወይም ሲቧጭር በለሃጩ ውስጥ የሚገኘው ቫይረስ ወደ ደም እና ነርቭ ይገባል፡፡ የበሽታው አስተላላፊ የሆነው እንስሳ ለሃጪ ክፍት ወይም የቆሰለ የሰው ልጅ ቆዳ፣ ዐይን፣ አፍ ወይም አፍንጫ ላይ ሲያርፍ ይተላለፋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ እና በኢትዮጵያ በሽታው ከ99 በመቶ በላይ ወደ ሰው እንዲተላለፍ የሚያደርገው ዋናው ምክንያት ውሻ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቀበሮ፣ ጅብ፣ ድመት እና የሌሊት ወፍ ቫይረሱን ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡
ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ዓመቱን ሙሉ የሚከሰት ሲሆን በአብዛኛው ግን ከመስከረም እስከ ሕዳር ባሉት ወራት ጎልቶ ይታያል፡፡ ይህ ወር የውሾች የመራቢያ ወቅት እንደመሆኑ አስፈላጊው ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል፡፡
ምልክቶቹ
በሰዎች ላይ ትኩሳት፣ራስ ምታት፣ የድካም ስሜት መሰማት ሕመሙ ሲጀምር የሚታዩ ምልክቶች ናቸው፡፡ በሽታው ቆየት ሲልም ታማሚው የእንቅልፍ ማጣት፣ የመጨናነቅና የመቅበዝበዝ ሁኔታዎች ይታዩበታል፡፡ በተጨማሪም የተወሰኑ የአካል ክፍሎቹ ወይንም ሙሉ በሙሉ ይዝላል/ልምሻ ይኖረዋል፡፡ ቅዠት፣ የምራቅ መዝረክረክ፣ ሰውንም ሆነ ያገኙትን ነገር ለመተናኮል መሞከር፣ ለመዋጥ መቸገር፣ ውኃ መፍራት የመሣሰሉት ምልክቶች ይታያሉ፡፡ ታዲያ እነዚህ ምልክቶች መታየት በጀመሩ በጥቂት ቀናት ውስጥ ሕመምተኛው ሊሞት ይችላል፡፡
በእንስሳት ላይ የሚታዩ ምልክቶች ደግሞ በአካባቢያቸው በሚያገኟቸው እንስሳትም ሆነ ሰዎች ላይ ይጮሃሉ፤ ወይንም ሊነክሱ ይሞክራሉ፡፡ ከዚህም ሌላ እንስሳቱ እረፍት አልባ መሆን ወይም መቅበዝበዝ፣ የአጥቂነት ወይንም ከተለመደው ባሕርይ በተለየ መፍዘዝ/መቀዛቀዝ ይታይባቸዋል፡፡ በተጨማሪም መዘለፍለፍ፣ መንቀጥቀጥ፣ ለመተንፈስ እና ለመዋጥ መቸገር፣ የልኃጭ መዝረብረብ እንደሚኖራቸው አስተባባሪው አብራርተዋል፡፡
አስተባባሪው እንዳስረዱት ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ወይም ራቢስ ያለበት ሰው ወይም እንስሳት ምልክቶቹ የሚታዩበት የጊዜ መጠን ከአምስት ቀናት እስከ አንድ ዓመት ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁንና በአብዛኛው ግን ከሁለት እስከ ሦስት ወራት ውስጥ መታየት ይጀምራል፡፡ ምልክቶቹ ለመታየት የሚወስደው ጊዜ በቁስሉ ውስጥ በገባው የቫይረስ መጠን፣ ንክሻው የተከሰተበት ቦታ እና የቁስሉ ጥልቀትና ክብደት፣ በቁስሉ አካባቢ ያሉ የነርቭ ጫፎችና የነርቭ አውታሮች ብዛት እንዲሁም ቫይረሱ ወደ ሰውነት ማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓት (Central Nervous System) ያለው የመግቢያ ቦታ ርቀት ይወስነዋል፡፡
አቶ ቢረሳው እንዳስረዱት ውሻን በሚያሳብድ በሽታ ተጋላጭ የሆኑ እንስሳት ሲታዩ ወዲያውኑ በቅርብ ለሚገኙ የእንሰሳት ወይንም የሰው ጤና ባለሙያዎች ማሳወቅ ይገባል፡፡ ምልክት እያሳየ ያለው እንሰሳ የቤት ከሆነ ለ10 ቀናት ለብቻው አስሮ ለውጡን መከታተል ይመከራል፡፡
የተነከሰውን ቦታ ወዲያውኑ በደንብ በንጹህ ውኃና በሳሙና ለ15 ደቂቃ ማጠብ፣ የተነከሰው ሰው ይህን ማድረግ የማይችል ከሆነ ይህን የሚያደርግ ሌላ ሰው የደም ንክኪ እንዳይኖረው ተገቢውን ጥንቃቄ አድርጎ እርዳታውን ማድረግ ይገባል፡፡ ከፍተኛ የመድማት ችግር ከሌለ በስተቀር ቁስሉን ሳያሽጉ ክፍት በመተው በአስቸኳይ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም ማድረስ፣ በጤና ተቋሙ ክትባትም ሆነ እንዳስፈላጊነቱ ተጨማሪ ሕክምና እንዲሰጠው ከታዘዘም በአግባቡ ማጠናቀቅ ይገባል፡፡
የፀረ ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ክትባት ከንክሻ በኋላ በተቻለ ፍጥነት መጀመር አለበት፡፡ ከንክሻው በኋላ ቀናት ወይም ሳምንታት ቢያልፉም እንኳ የራቢስ ተጋላጭነት ካለ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድን አለመዘንጋት ተገቢ መሆኑን አስተባባሪው አሳስበዋል፡፡
የመከላከያ መንገዶች
አቶ ቢረሳው እንዳሉት ውሾችን እና ድመቶችን በየዓመቱ የጸረ ውሻን የሚያሳብድ በሽታ ክትባት በመስጠት በሽታውን ከምንጩ መግታት ይቻላል፡፡ የባህሪ ለውጥ የሚያሳዩ እና ባለቤት አልባ ውሻዎችን እና የእንስሳት ለሃጪን አለመንካት ተገቢ ነው፡፡ ለከፍተኛ ተጋላጭ ወገኖች ማለትም ለእንስሳት ሕክምና ባለሙያዎች አስቀድሞ ክትባት እንዲከተቡ ማድረግ በሽታውን ይከላከላል፡፡ በተጨማሪም በክልሉ ባለቤት አልባ ውሾችን የሚወገዱበት አግባብ በተመለከተ ሕግና ደንብ እንዲጸድቅ ለክልሉ ምክርቤት ረቂቁ ተልኮ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
መረጃ
ውሻን በጥሩ ሁኔታና በጤናማ መንገድ ለማሳደግና መንከባከብ፦
*በየሦስት ወይም ስድስት ወራት በእንስሳት ሐኪም ትዕዛዝ የወስፋት መድኃኒት መስጠትን አይዘንጉ፡፡
*ሁልጊዜ በበቂ ሁኔታ ንጹሕና ቀዝቃዛ ውኃ ማቅረብ፣ እንደ ውሻው ዕድሜና ዓይነት የተመጣጠነ ምግብ መስጠት አይዘንጉ፡፡
*ከቅዝቃዜ፣ ከዝናብ እና ከከፍተኛ ፀሐይ የሚከላከል፣ ንጹሕ እና ደረቅ መጠለያ (የውሻ ቤት) ማዘጋጀት፣ የውሻውን ፀጉር በየጊዜው ማበጠር እና እንደ አስፈላጊነቱ በውሻ ሳሙና ማጠብ አይርሱ፡፡
*ውሻ ማሕበራዊ እንስሳ በመሆኑ ለረጅም ጊዜ ብቻውን ሰንሰለት ላይ አስሮ ማስቀመጥ ለከፍተኛ ጭንቀትና ለጠበኝነት ያጋልጠዋል፤ በመሆኑም ከቤተሰቡ ጋር ጊዜ እንዲያሳልፍና ፍቅር እንዲሰማው ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የመስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


