ዘመናዊው የእግር ኳስ ዓለም በገንዘብ ኃይል እና በታክቲክ ልህቀት የሚደረግ ፍልሚያ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል፡፡ በዚህ ፍልሚያ ውስጥ ማንችስተር ሲቲ ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት የፈጠረው ተጽዕኖ ወደር አይገኝለትም፡፡ ውኃ ሰማያዊ ለባሾቹ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን በበላይነት ከመቆጣጠር አልፈው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ክብርንም አሳክተዋል፡፡ ክለቡ በዋንጫዎች ከመንቆጥቆጡ በተጨማሪ ሜዳ ላይ በሚያሳየው አስገራሚ የኳስ ፍሰት በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደጋፊዎችን አፍርቷል፡፡
የፔፕ ጋርዲዮላ የፍልስፍና ልህቀት እና የሼክ መንሱር ረብጣ ቢሊዮን ዶላር ማንቸስተር ሲቲን ክፍ ያለ ደረጃ አስቀምጦታል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ሁሉ አንጸባራቂ ስኬት እና የዋንጫዎች ክምችት ጀርባ አንድ ትልቅ ጥቁር ደመና በኢትሀድ ሰማይ ላይ አጥልቶ ይገኛል፡፡ ክለቡ የፋይናንስ ደንብን በከፍተኛ ደረጃ መጣሱ ተሰምቷል፡፡
ክሱን በተመለከተ ቢቢሲ ባቀረበው ዘገባ ማንችስተር ሲቲ ከ115 በላይ በሆኑ የፋይናንስ ደንብ ጥሰቶች ተከሶ ራሱን ለመከላከል የሕግ ሂደቱን እየተጋፈጠ ይገኛል፡፡ ክለቡ ከ2009 እስከ 2018 እ.አ.አ ባለው ጊዜ ውስጥ የፋይናንስ ደንቦችን ሆነ ብሎ መጣሱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ቢቢሲ በዝርዝር እንዳስቀመጠው ክሶቹ በዋናነት በሶስት መከፈላቸውን ያስነብባል፡፡ ክለቡ ገቢውን አጋኖ በማቅረብ በተለይም የስፖንሰርሺፕ ገቢውን ከሼክ መንሱር ኪስ እየተከፈለው እንደ ሕጋዊ የንግድ ገቢ አስመስሎ ማቅረቡ የመጀመሪያው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የአሰልጣኞች እና የተጫዋቾችን ክፍያ በተመለከተ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ በመስጠት በስውር ተጨማሪ ክፍያዎችን መፈጸሙ ነው፡፡
ሶስተኛው እና እጅግ አሳሳቢው ደግሞ ፕሪሚየር ሊጉ ለሚያደርገው ምርመራ ተገቢውን ትብብር አለማድረጉ መሆኑን የቢቢሲ ስፖርት መረጃ አመልክቷል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ከዚህ ቀደም በማንቸስተር ሲቲ ላይ ተመሳሳይ ክስ አቅርቦ የሁለት ዓመት እገዳ ጥሎበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ክለቡ ጉዳዩን ወደ ስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት(ካስ) ወስዶ የጊዜ ገደብ አልፎበታል በሚል በሕግ ከለላ ቅጣቱን ማስነሳቱ አይዘነጋም፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ያቀረበው ክስ ግን እጅግ ውስብስብ እና ከዚህ የተለየ መሆኑን የስፖርት መገናኛ አውታሮች እየዘገቡት ነው፡፡ ፕሪሚየር ሊጉ በራሱ ሕግ መሰረት የሚያካሂደው በመሆኑ እና የጊዜ ገደብ የሚባል ሕግ በፕሪሚየር ሊጉ መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ባለመካተቱ ሲቲ የቀድሞውን አይነት የማምለጫ ቀዳዳ ፈጽሞ ሊያገኝ አይችልም፡፡
ይህ የሕግ ኮሚሽን የሚያደርገው ማጣራት ወራትን አልፎ ዓመታትን ሊፈጅ የሚችል ሲሆን ውሳኔውም የማያዳግም እንደሚሆን የቢቢሲ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህ ክስ በክለቡ ላይ ካስከተለው ከፍተኛ ውጥረት ባሻገር ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ሊመጡ የሚችሉ ቅጣቶች እጅግ አሳሳቢ መሆናቸውን የዘገበው ደግሞ ዘ ቴሌግራፍ ነው፡፡ የእንግሊዙ ጋዜጣ እንዳስነበበው ማንችስተር ሲቲ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የሚጠብቀው ከገንዘብ ቅጣት የዘለለ ይሆናል፡፡
እንደ ዘ ቴሌግራፍ ግምት ምናልባት የመጀመሪያው እና ቀላል የሚባለው ከፍተኛ የነጥብ ቅነሳ ነው፡፡ ይህ የነጥብ ቅነሳ እስከ 30 ነጥብ ሊደርስ እንደሚችል እና ክለቡን ከሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ውጭ እንደሚያደርገው ይገመታል፡፡ ሁለተኛው እና እጅግ አወዛጋቢው ቅጣት ደግሞ ክለቡ ሕግ በጣሰባቸው ዘጠኝ ዓመታት ያገኛቸውን የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎች መነጠቅ ነው፡፡
ምናልባት ይህ ከሆነ ዋንጫዎቹ ሁለተኛ ደረጃ ይዘው ላጠናቀቁ ክለቦች ይሰጣሉ? ወይስ ውድድሩ ይሰረዛል? የሚለው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ሦስተኛው እና እጅግ የከፋው ቅጣት ደግሞ ክለቡን ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ሙሉ በሙሉ ማባረር እና ወደ ታችኛው ዲቪዚዮን ማውረድ ነው፡፡ ዘ ቴሌግራፍ እንደዘገበው ኮሚሽኑ ማንቸስተር ሲቲ ጥፋተኛ ነው ብሎ ካረጋገጠ ይህንን የከፋ እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ አይልም፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ የማንችስተር ሲቲ ታሪክ እና የወደፊት ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል፤ የክለቡ ግዙፍ ፕሮጀክትም በአንድ ጀምበር ሊከስም ይችላል፡፡
በ2009 እ.አ.አ የቀድሞው የአርሴናል አሰልጣኝ አርሴን ቬንገር “ማነቸስተር ሲቲ የገንዘብ አበረታች ንጥረ ነገር እየተጠቀመ ነው፤ ከተነቃበት ትልቅ አደጋ ይገጥመዋል፤ ህልውናውም ያከትማል” ሲሉ መናገራቸውን በርካታ የስፖርት መገናኛ አውታሮች በማስታወስ ጊዜው አሁን መሆኑን ዘግበዋል፡፡
ዘ ጋርዲያን የፋይናንስ ደንብን መጣስ በሌሎች አቅም በሌላቸው ክለቦች ላይ የሚፈጸም ግልጽ ኢፍትሃዊነት መሆኑን በማስረጃ አብራርቷል፡፡ ጋዜጣው ይህንን አሰራር የገንዘብ አበረታች መድሃኒት መጠቀም በማለት ግልጾታል፡፡ አትሌቶች አበረታች መድሃኒት ወስደው ሲያሸንፉ እንደሚወገዙ ሁሉ አንድ ክለብም ከሕግ ውጭ ገንዘብ እያፈሰሰ ስኬት ማምጣቱ ተመሳሳይ ወንጀል ነው ሲል ዘ ጋርዲያን ይሞግታል፡፡
እግር ኳስ በሜዳ ላይ በሚደረግ የችሎታ ፉክክር ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጭ በሚኖር ግልጽ እና ፍትሃዊ የገንዘብ አጠቃቀም መመራት አለበት በማለት ያብራራል፡፡ ይህ ክስ ፕሪሚየር ሊጉ የራሱን ሕግ የማስከበር አቅም እንዳለው ለዓለም የሚያሳይበት ትልቅ ፈተና መሆኑንም ያስገነዝባል፡፡ ሲቲ ከዚህ ክስ በነጻ ከተሰናበተ የፋይናንስ ፍትሃዊነት ደንብ የሚባል ነገር ትርጉም አልባ ይሆናል፤ ሌሎች ሀብታም ክለቦችም ሕግን በመጣስ የገንዘብ ኃይላቸውን ያለገደብ እንዲጠቀሙ ያበረታታቸዋል፡፡ እናም ሕግን ማስከበር የእግር ኳሱን ነፍስ የማዳን ውጊያ መሆኑን ጋዜጣው አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ የክለቡን ንጽህና በተደጋጋሚ በአደባባይ ቢሟገትም ባሳለፍነው ዓመት የሚወራው እውነት ከሆነ ክለቡን እለቃለሁ ሲል እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ምንም እንኳን ተጫዋቾቹ በሜዳ ላይ የሚያሳዩት ብቃት ባይቀንስም ከጀርባ ያለው ስነልቦናዊ ጫና ግን ቀላል የሚባል አይሆንም፡፡
የክሱ ሂደት መጓተት በስብስቡ ውስጥ ትልቅ ስጋትን ፈጥሯል፡፡በዚህ ምክንያት የቡድን አባላቱ እጅግ ውጥረት የበዛበት እና እያንዳንዱን ቀን በጥርጣሬ እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል፡፡ የተጫዋቾች ወኪሎችም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን ዘገባው አብራርቷል፡፡
ከክለቡ ውጭ ያለው ማዕበል እና የተፎካካሪ ክለቦች አቋም ጉዳዩን ይበልጥ አወሳስቦታል፡፡ ዴይሊ ሜል እንደዘገበው ሌሎች የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በማንችስተር ሲቲ ላይ ፈጣን እና የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡ በተለይም ታላላቆቹ ክለቦች አርሰናል፣ ማንችስተር ዩናይትድ፣ ሊቨርፑል እና ቶተንሃም ሲቲ ሕግን ጥሶ የበላይነት መውሰዱ ክፉኛ አስቆጥቷቸዋል፡፡
ኤቨርተን እና ኖቲንግሃም ፎረስት በተወሰኑ የፋይናንስ ደንብ ጥሰቶች ምክንያት ብቻ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን የነጥብ ቅነሳ ቅጣት መቀበላቸው አይዘነጋም፡፡ ታዲያ ከ115 በላይ ክሶች ያሉት የቢሊየነሩ ሼክ መንሱር ክለብ ማንቸስተር ሲቲ ጉዳይ መጓተቱ ተቀናቃኝ ክለቦችን ይበልጥ አስቆጥቷል፡፡ “ሕጉ ለሁሉም እኩል መሆን አለበት” የሚለው የክለቦቹ የጋራ ድምጽ ሆኗል፡፡
የሲቲ ደጋፊዎች ክለባችን በስኬቱ ምክንያት አድልዎ እና ጥላቻ እየተፈጸመበት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ የሌሎች ክለቦች ደጋፊዎች ግን ፍትህ የዘገየችበት እና ፕሪሚየር ሊጉ ትልቁን ክለብ ለመቅጣት የፈራበት አጋጣሚ ነው እያሉ በማጉረምረም ላይ ናቸው፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የጥቅምት 2 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


