እንጦጦ

0
123

መገኛ እና ገጽታ

የእንጦጦ ተራራ ከአዲስ አበባ ከተማ በስተሰሜን በቅርብ ርቀት ከባሕር ወለል በሦስት ሺህ ሁለት መቶ ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል፡፡ የተራራዉ ሰንሰለት  ስድስት ሺህ ሦስት መቶ ሄክታር ይሸፍናል፡፡  ዳግማዊ አፄ ምኒልክ  እና እቴጌ ጣይቱ  አዲስ አበባን ከመመሥረታቸው በፊት መቀመጫቸውን በእንጦጦ ተራራ ላይ አድርገው ኢትዮጵያን መርተዋል።

የእንጦጦ ተራራ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ  ንጹህ አየር እየሳቡ አዲስ አበባን እና አካባቢዋን ቁልቁል አሻግሮ በመመልከት ተፈጥሮን ለማድነቅ በእጅጉ ምቹ ስፍራ ነው፡፡ በተለይ ጠዋት ከተራራዉ ላይ ሆነው ወደ አዲስ አበባ እና አካባቢዋ ሲመለከቱ የሚታየው ጭጋጋማ አየር እና የፀሐይ ጮራ  ልዩ ደስታን ይለግሳል። ከዚህም በላይ ቁልቁለታማ እና ዳገታማ መንገዶች ተራራውን ለእግር ጉዞ እና ለብስክሌት ስፖርት አፍቃሪዎች ተመራጭ ስፍራ አድርገውታል።

የእንጦጦ ተራራ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የረዥም ርቀት ሯጮች ተመራጭ የመለማመጃ ስፍራ ነው፡፡ አትሌቶቹ ቦታውን ለመለማመጃነት የሚመርጡት ዳገት በወጡ ቁጥር እየሳሳ የሚሄደውን አየር እየሳቡ ዳገቱን በመውጣት እንዲሁም ቁልቁለቱን በመውረድ አስደናቂ ብቃትን ስለሚገነቡበት ነው፡፡

ቅርሶች

በእንጦጦ ተራራ እና አካባቢዉ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ በርካታ ቅርሶች ይገኛሉ፤ የእንጦጦ  ማርያም ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ መዛግብት እና ማስታወሻዎች፣የአዲስ አበባ ቱሪዝም ቢሮ ሪፖርቶች እና ሕትመቶች እንዲሁም የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ሰነዶች እንደሚጠቁሙት፡፡ ከእነዚህ ቅርሶች መካከል  የእንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን፣ቤተ መዘክር እንዲሁም የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት ይጠቀሳሉ፡፡

እንጦጦ ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተገነባችው በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነው፤ በ1877 ዓመተ ምሕረት ገደማ፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ከአዲስ አበባ መቆርቆር እና ከዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ጥልቅ ቁርኝት አላት፡፡  አፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ የንግሥና ሥርዓታቸውን የፈጸሙት በዚች ቤተ ክርስቲያን እንደሆነ ከፍ ሲል የጠቀስናቸው የመረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ የኢትዮጵያ ጀግኖች ወራሪዉን የጣሊያን ጦር ለመፋለም ወደ ዐድዋ ሲዘምቱ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እንዲሁም እቴጌ ጣይቱ ሥርዓተ ጸሎት ያደረጉባት፣ በድል ሲመለሱም ለፈጣሪ ምስጋና ያቀረቡባት ታሪካዊ ሥፍራ ናት፡፡ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና የእቴጌ ጣይቱ አስከሬን ወደ በዓታ ለማርያም ገዳም ከመዛወሩ በፊት  ያረፈው በዚች ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በ1910 ዓ.ም. በተሠራው “ሸራ ቤት” በተባለው መቃብር ውስጥ ነው፡፡

ከቤተ ክርስቲያኗ ጎን የእንጦጦ ቤተ መዘክር ይገኛል፡፡ በቤተ መዘክሩ ውስጥ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ  ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ የንግሥና ሥርዓታቸውን ባከበሩበት ዕለት የለበሷቸው ባለወርቅ ጥልፍ ካባዎች እና የክብር ዘውዶቻቸው ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የንጉሣዊዉ ቤተሰብ አልባሳት እና ጌጣ ጌጦች፣ከእንግሊዝ ንግሥት ከንግሥት ቪክቶሪያ ለእቴጌ ጣይቱ የተበረከተ መስታዎት፣በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ሲያገለግሉ የነበሩ አልጋዎች እንዲሁም ሌሎች የዕደ ጥበብ ውጤቶች በቤተ መዘክሩ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ጦር የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ድል በነሳበት በዐድዋ ጦርነት ላይ ጥቅም ላይ የዋሉ ጋሻዎች፣ ሰይፎች እና ጠመንጃዎችም በቤተ መዘክሩ ውስጥ ከሚገኙ ቅርሶች ተጠቃሽ ናቸው። በጥንታውያን ብራናዎች ላይ የተጻፉ የወንጌል መጻሕፍት፣ በወርቅ እና በብር የተሠሩ መስቀሎች፣ ምንጣፎች… በቤተ መዘክሩ ይገኛሉ፡፡

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ አዲስ አበባን ከመቆርቆራቸው በፊት በ1880ዎቹ መጀመሪያ ያስገነቡትና ኢትዮጵያን ይመሩበት የነበረው ቤተ መንግሥት አሠራር የዚያን ዘመን የኢትዮጵያ ባህላዊ የሕንጻ ጥበብ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ቤተ መንግሥቱ የተገነባው ከአካባቢው ከሚገኝ ድንጋይ፣ ጭቃ እና እንጨት (በተለይም ከዝግባ እና ከእንጨት ምሰሶዎች) ሲሆን ጣሪያው በሳር የተከደነ (በኋላ ላይ በቆርቆሮ የተተካ) ክብና ባህላዊ ቅርጽ ያለው ነው።

ቤተ መንግሥቱ የተለያዩ ክፍሎች አሉት፡፡ ዜና ማርቆስ (ታላቁ አዳራሽ) አንዱ ሲሆን ንጉሠ ነገሥቱ ከባለሥልጣኖቻቸው ጋር የሚመክሩበት፣ እንግዶችን የሚቀበሉበት እና ትላልቅ ግብዣዎችን የሚያደርጉበት  ነው።

የንጉሠ ነገሥቱ እና የንግሥቲቱ የግል ማረፊያ የነበሩ ክፍሎችም አሉት፤ ቤተ መንግሥቱ። በቤተ መንግሥቱ አጠገብ   ምግብ እና እንደ ጠጅ እና ብርዝ ያሉ መጠጦች  የሚዘጋጁባቸው እንዲሁም የጦር መሣሪያዎች የሚቀመጡባቸው  ትንንሽ ሕንጻዎች ተገንብተዋል።

ይህ ቤተ መንግሥት የዐድዋ ጦርነት የታቀደበት፣ በርካታ ታሪካዊ ውሳኔዎች የተላለፉበት እና የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መሠረት የተጣለበት ታሪካዊ ቅርስ ነው።

የተፈጥሮ ሀብት እና ብዝኃ ሕይወት

እንጦጦ ተራራ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከአውስትራሊያ ያስመጡት የባሕር ዛፍ ተክል በብዛት የሚገኝበት ስፍራ ነው፡፡  ከባሕር ዛፍ  በተጨማሪም ሥነ ምህዳሩን ለመጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ 49 ያህል ዝርያዎች ያሏቸው በርካታ ሀገር በቀል እጽዋት ይገኛሉ። ከእነዚህ ሀገር በቀል እጽዋት መካከልም ጽድ፣ ወይራ፣ ኮሶ፣ ቀረሮ፣ አጋም፣ ዶቅማ እንዲሁም እንዶድ ይጠቀሳሉ፡፡  ዘማሪ ወፍ፣ በቀቀን፣ የደጋ ዝይ፣ አንገተ ነጭ ርግብ፣ ባለትልቅ መንቆር ቁራን ጨምሮ እስከ 124 የሚደርሱ የአእዋፍ ዝርያዎች እጽዋቱን መጠለያ አድርገው ይኖራሉ፡፡

የእንጦጦ ተራራ በመንግሥት እና በባለሀብቶች ትብብር ለምቶ በመናፈሻ ማዕከልነት እያገለገለ ይገኛል። “እንጦጦ ፓርክ” በሚል ስያሜ የሚታወቀውና በውስጡ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን፣ የፈረስ መጋለቢያ ቦታዎችን፣ የበጋ መዝናኛዎችን እና የዕደ ጥበብ ውጤቶች መሸጫ ሱቆችን የያዘው ፕሮጀክት አካባቢውን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ  መዳረሻ አድርጎታል።

የእንጦጦ ተራራ እንዲሁም የመናፈሻ ማዕከል በየዕለቱ በአማካኝ አንድ ሺህ ጎብኝዎችን ያስተናግዳሉ፡፡ ከእነዚህ ጎብኝዎች ውስጥ ከአምስት መቶ እስከ ስድስት መቶ የሚደርሱት የውጪ ሀገር ዜጎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ናቸው፡፡በተጨማሪም በየዓመቱ ጥቅምት 21 በሚከበረው የእንጦጦ ማርያም ዓመታዊ የንግሥ በዓል ለመታደም እንዲሁም ለጉብኝት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የውጪ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ይገኛሉ፡፡

 

የእንጦጦ – ቀበና ልማት

ስለእንጦጦ ተራራ እና የመስህብ ሀብቶች ሲወሳ  የእንጦጦ ቀበና ወንዝ እንዲሁም የወንዝ  ዳርቻ ልማት ይጠቀሳል፡፡ የቀበና ወንዝ የሚነሳው  ከእንጦጦ ተራራ ስር ነው፡፡ ወንዙ ከተራራው ስር በመነሳት አዲስ አበባ ከተማን ሰንጥቆ ወደ ደቡብ ይወርዳል፡፡ ወንዙን ተከትሎም የወንዝ እንዲሁም የወንዝ ዳርቻ ልማት ተከናውኗል፡፡

ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት  የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የወንዝ ልማቱ አንድ ትልቅ ግድብ፣ አሥራ ስድስት አነስተኛ ግድቦች፣ ሀያ ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር የድጋፍ ግንብ… ተሠርቶለታል፡፡ የወንዝ ዳርቻ ልማቱ  ደግሞ 36 ሺህ 928 ካሬ ሜትር የአፈር እና ሥነ ምኅዳር ጥበቃ ሥራዎች ተከናውነውለታል፡፡

ከወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ጋር ተያይዞ የተቀናጀ የመሠረተ ልማት ሥራ ተከናውኗል፡፡ በዚህም ሀያ አንድ የእግረኛ ድልድዮች፣ ሠላሳ ሦስት ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ የፍሳሽ መስመር እንዲሁም ስድስት መቶ ዘጠና አምስት ተሽከርካሪዎችን ለማቆም የሚያስችሉ ሰባት ቦታዎች ተዘጋጅተዋል፡፡

ይህ የእንጦጦ ቀበና የወንዝ እንዲሁም የወንዝ  ዳርቻ ልማት ለአዲስ አበባ ከተማ እስትንፋስ ከሆነው ከእንጦጦ ተራራ ሥነ-ምህዳር ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው፡፡ የእንጦጦ ጫካ መኖር የቀበና ወንዝን ደኅንነት ለመጠበቅ አስችሏል፡፡ ወንዙ ጫካዉ በፈጠረለት ምቹ ሁኔታ አቅሙ ጎልብቶ ከተራራ ስር እየመነጨ ወርዶ ከአቃቂ ወንዝ ጋር ይገናኛል፡፡ የወንዙን ፍሰት ተከትሎ  የተከናወነው የአረንጓዴ ልማት ሥራ የተለያዩ ዛፎችን እንዲሁም ብዝኃ ሕይወት ሕልውና አስጠብቋል፡፡ ጎብኚዎች ከተራራው ጫፍ በመነሳት እስከ ቀበና ድረስ በማራኪ የተፈጥሮ የመስህብ ስፍራ ውስጥ በመጓዝ ጉብኝት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡

አጫጭር መረጃዎች

በኢትዮጵያ የሚገኙ አራት የተፈጥሮ ፓርኮች እና ሐይቆች

  • የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ፦ የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ከአዲስ አበባ በምሥራቅ በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ይገኛል፡፡ ፓርኩ ወደ 756 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ስፋት አለው፡፡ ፓርኩ የተለያዩ እጽዋት እንዲሁም እንስሳት መገኛ ነው።
  • የያንጉዲ ራሳ ብሔራዊ ፓርክ፦ የያንጉዲ – ራሳ ብሔራዊ ፓርክ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምሥራቅ 500 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ፣ በአፋር ክልል (በገዋኔ እና በአሳይታ መካከል) በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ይገኛል። የዱር እንስሳትን ለመጠበቅ በ1969 ዓ.ም የተመሠረተው ይህ ፓርክ፣ ወደ 4 ሺህ731 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የቆዳ ስፋት አለው።
  • የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ፡- የኦሞ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በኦሞ ወንዝ ዳርቻ የሚገኝ ሲሆን የሳቫና ሳር፣ ከ70 በላይ የአጥቢ እንስሳት ዝርያዎች መገኛ ነው።
  • ጫሞ ሐይቅ፡- ጫሞ ሐይቅ እጅግ ግዙፍ አዞዎች እንዲሁም ጉማሬዎች በስፋት የሚገኙበት የመስህብ ስፍራ ነው፡፡ የሐይቁ ዳርቻዎች በአብዛኛው ረዣዥም  ሳሮች፣ ቁጥቋጦዎች እና ደኖች ይገኙባቸዋል። እጽዋቱ የበርካታ የዱር እንስሳት እና አእዋፍ መገኛ ነው።

 

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን።

 

(ቦረቦር ዘዳር አገር)

በኲር የጥቅምት 2  ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here