በደም የተጻፈ የሉዓላዊነት መገለጫ

0
6

ሀገር ማለት መሬት፣ አፈር፣ ድንበር እና ዛፍ ብቻ አይደለችም፡፡ ሀገር ማለት በደም እና በአጥንት ተገንብቶ፣ በሕያው ባሕል ታንጾ፣ የሰው ልጆች ከነሙሉ ክብራቸው የሚኖሩባት ድንቅ ስፍራ ናት፡፡ ይህችን ውድ እና ታላቅ ሀገር በዓለም አደባባይ ደምቃ እና ጎልታ እንድትታይ የሚያደርገው ደግሞ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማትን ያካተተው ሠንደቅ ዓላማችን ነው፡፡ የሥነ ልቦና ምሁራን “የሰው ልጅ በነጻ ላገኘው ነገር የሚሰጠው ዋጋ አነስተኛ ነው፤ በአንጻሩ ደም እና ላቡን ጠብ አድርጎ ላገኘው ጉዳይ ግን ወደር የለሽ ክብር አለው” ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማም እንዲሁ በዋዛ የተገኘ ሳይኾን፤ አባቶቻችን በጦር ሜዳ ውድ ሕይወታቸውን ገብረው ያቆዩልን የሉዓላዊነት እና የነጻነት ማኅተም ነው፡፡

ለዛሬዋ ኢትዮጵያ መሠረት ይኾን ዘንድ ቀደምት ኢትዮጵያውያን በጦር ሜዳ በጀግንነት ተዋድቀው ጠላትን አንበርክከዋል። ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለሠንደቅ ዓላማቸው ክብር እና ለሀገራቸው ሉዓላዊነት የከፈሉት መስዋዕትነት በዓለም ታሪክ አቻ የማይገኝለት ከተራራ የገዘፈ የጀግንነት ገድል ነው።

ሰንደቅ ዓላማ አንድን ሀገር ከሌሎች ሀገራት የሚለይ፣ የሀገርን ማንነትና ሉዓላዊነት የሚወክል ሀገራዊ ምልክትም ነው። በይፋዊ ዝግጅቶች፣ በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ ሀገራዊ ሥነ-ሥርዓቶች ውስጥ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ይውለበለባል።

ሰንደቅ ዓላማን ማክበር ማለት የሀገርን ማንነትና የጋራ ምልክቶችን በአክብሮት መመልከት ማለት ነው። ይህ አክብሮት በተግባር ሲገለጽ ሰንደቅ ዓላማን በአግባቡ መያዝ፣ ሲወጣና ሲወርድ የተመለከተውን ሥነ-ሥርዓት መከተልና ስለ ትርጉሙ ትክክለኛ ዕውቀት ማዳበርን ያካትታል።

ሰንደቅ ዓላማን ማክበር በሥነ-ሥርዓት ተሳትፎ ብቻ አይገደብም። ለሀገር ፍቅር ማሳየት ማለት ሕግን ማክበር፣ ለሌሎች መብት ጥበቃ ማድረግ፣ ለሰላም መትጋት፣ በሐቀኝነት መሥራትና ለሀገር ልማት አስተዋጽኦ ማድረግም የሰንደቅ ዓላማ ክብር ተጨማሪ መገለጫዎች ናቸው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ታዲያ ሀገራችንም የሰንደቅ ዓለ።ማ ቀንን በየዓመቱ በማሰብ በተለያዩ ዝግጅቶች ታከብራለች። እኛም በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በሚገኘ ትምህርት ቤቶች ተገኝተን ነበር፡፡

እዮብ መሳፍንት በዕውቀት ፋና አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው፡፡ ተማሪ እዮብ “ሠንደቅ ዓላማችን የነጻነታችን አርማ ነው፤ እኛ ተማሪዎች ደግሞ ይህንን ክብር የምንጠብቀው በትምህርታችን በመበርታት፣ ሕግን በማክበር፣ የትምህርት ቤታችንን ንጽሕና በመጠበቅ እና እርስ በርስ በመከባበር ነው” በማለት ነው ስሜቱን ያጋራን፡፡ ትናንት በጦር ሜዳ የተገለጠው አርበኝነት ዛሬ በትምህርት ገበታ ላይ መተግበር እንዳለበትም ነግሮናል፡፡

በተመሳሳይ የፈለገ ዓባይ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ቤተል አዳሙ በበኩሏ ሠንደቅ ዓላማን ስለማክበር እና ስለ ልዩነት ያላትን ምልከታ ታጋራለች፡፡ “ሠንደቅ ዓላማን ማክበር ልዩነቶቻችንን አክብረን በአንድነት መቆም መቻል ነው” ስትል ነው የሠንደቅ ዓላማን ትርጉም የገለጸችው፡፡

እነዚህን መልካም ዕሴቶች በተማሪዎች አዕምሮ ውስጥ በመቅረጽ ረገድ የመምህራን እና የወላጆች ሚና የማይተካ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የዕውቀት ፋና አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህርት ወ/ሮ አበባ ሺፈራው መምህራን በተማሪዎች የባሕርይ ግንባታ ላይ ያላቸውን ድርሻ ሲያስረዱ “ስለ ሠንደቅ ዓላማ ትምህርት በንግግር ብቻ መቅረብ የለበትም፤ ተማሪዎች በጥያቄ እና መልስ፣ በውይይት እንዲሁም በሥዕል ዝግጅት በንቃት እንዲሳተፉ በማድረግ እውነተኛ የሀገር ፍቅርን በተግባር እንዲያሳዩ መትጋት አለብን” ይላሉ፡፡ መምህራንም ለተማሪዎቻቸው በሐቀኝነት እና በመቻቻል በምሳሌነት መምራት እንዳለባቸው ያስገነዝባሉ፡፡ ይህንንም በትምህርት ቤቱ እየተገበሩት እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

የፈለገ ዓባይ አንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አቶ ሙሉጌታ እንየው በበኩላቸው ስለ ሰንደቅ ዓላማ ክብር መጠበቅ የወላጆችን ወሳኝ ሚና ያነሳሉ፡፡ “ቤተሰብ የልጆች የመጀመሪያ የትምህርት ማዕከል ነው፤ በመኾኑም ወላጆች ስለ ሀገር ታሪክ፣ ስለ ዜግነት ኃላፊነት፣ ስለ ሠንደቅ ዓላማ ክብር ከልጆቻቸው ጋር በመወያየት ትክክለኛ ግንዛቤን ሊያስጨብጡ ይገባል” በማለት ነው የትምህርት ቤትን እና የቤተሰብን ትብብር አስፈላጊነት ያስገነዘቡት፡፡

ስለኾንም የሠንደቅ ዓላማን ክብር ለማስጠበቅ እና የዜግነት ኃላፊነትን ለመወጣት በርካታ ተግባራትን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በትምህርት ቤቶች ስለ ሠንደቅ ዓላማ ትርጉም የሚያስተምሩ አሳታፊ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት፣ ተማሪዎች ሀገራዊ ምልክቶችን የሚያንጸባርቁ የጽሑፍ፣ የሥዕል እና የንግግር ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ፣ በየቤተሰቡ ስለ ሀገር ታሪክ፣ ስለ ሰላም፣ ስለ መቻቻል፣ ስለ ፍትሕ እና ስለ የጋራ ኃላፊነት ጤናማ የውይይት ባሕልን ማዳበር እና የሠንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓትን ከዕለት ተዕለት ተግባር ጋር በማስተሳሰር የሥራ ባሕልን ማጎልበት የሚሉት ደግሞ አቶ ሙሉጌታ የዘረዘሯቸው የሸንደቅ ዓላማ ክብር ማስጠበቂያ ተግባራት ናቸው፡፡

ሠንደቅ ዓላማ የሀገር ማንነት እና የጋራ ሕይወት ሕያው መገለጫ ነው፡፡ በመኾኑም የሠንደቅ ዓላማ ክብር የሚረጋገጠው በሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘት ብቻ ሳይኾን በዕለት ተዕለት ተግባራችን ሐቀኝነትን እና መከባበርን ስናስቀድም ነው፡፡

በመኾኑም ወላጆች ልጆቻቸው በሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት ላይ በአክብሮት እንዲሳተፉ ከማበረታታት ባለፈ፣ በቤት ውስጥ ሕግን ማክበር፣ ሌሎችን መርዳት፣ ንጽሕናን መጠበቅና የሀገር ሀብትን መንከባከብ በተግባር ሊያሳዩ ይገባል፡፡ ልጆች የሚማሩት ከቃል ብቻ ሳይኾን ከወላጆቻቸው ዕለታዊ ባሕርይ መኾኑን በመገንዘብ ቤተሰብ የዜግነት ትምህርት የሚጀምርበት መሠረታዊ ቦታ መሆኑን ነው አቶ ሙሉጌታ ያስረዱት፡፡

በአጠቃላይ፣ ሰንደቅ ዓላማን ማክበር በዕውቀት፣ በተግባርና በጋራ ኃላፊነት የሚገለጽ የዜግነት ዕሴት ነው፡፡ ስለሆነም ተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆች በትብብር በመሥራት ሰላምን፣ ፍትሕን፣ መከባበርን እና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሰንደቅ ዓላማ በክብር ሲውለበለብ የሚታየው የሀገር ምልክት ብቻ ሳይኾን፣ ዜጎች በጋራ ለሚገነቡት የተሻለ ሕይወት የሚያደርጉትን ቃል ኪዳን የሚያሳስብ ነው፡፡

መረጃ

የአፍሪካ ባንዲራዎች ታሪክ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማቱ ይታወቃል። እነዚህ ቀለማት በኋላ በብዙ የአፍሪካ አገራት ባንዲራዎች ላይ በተለያዩ ቅርጾች ታዩ፤ ከፓን-አፍሪካዊ ምልክቶችም ጋር ተያያዙ። ለምሳሌ፦

ጋና በ1957፦ በነፃነቷ ዓመት ቀይ፣ ወርቃማ ቢጫና አረንጓዴ ቀለማት ያሉትን ባንዲራ ተቀበለች።

ጊኒ በ1958፦ ቀይ፣ ቢጫና አረንጓዴ ቀለማት ያሉትን ባንዲራ አጸደቀች።

ሴኔጋል በ1960፦ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሉትን ባንዲራ ተቀበለች።

ማሊ በ1960፦ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሉትን ባንዲራ አጸደቀች።

ምንጭ፡- How Ethiopia፞፞፞፞̕s Flag Inspired the Pan-African Idea.

(ሰናይት በየነ)

በኲር የጥቅምት 9  ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here