የዜግነት መብት

0
13

አገልግሎት ሙያን እና አውቀትን መሠረት አድርጎ የተገልጋዩን ፍላጎት ለመሙላት የሚደረግ ተግባር ነው፡፡ ማኅበረሰቡ የሚፈልገውን አገልግሎት የመጠየቅ እና የመገልገል መብት እዳለው ሁሉ አገልጋዩ አካልም የሚፈልጉትን ግልጋሎት በተቀመጠው ጊዜ የመስጠት  ግዴታ ተጥሎበታል፡፡

የሕዝብ ተጠያቂነትና የመንግሥት አሠራር ግልጽነት መኖር እንዳለበት ደግሞ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 12  በዝርዝር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህ አንቀጽ ማንኛውም የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበትና ማንኛውም ኃላፊ ደግሞ ሕዝብ  የሰጠውን አደራ ተቀብሎ አገልግሎቱን የማሳለጥ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ  ይደነግጋል። በዚሁ አንቀፅ ቁልፍ መርህ ላይ “የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መካሄድ አለበት።” ሲል ተገልጋይ ዜጋ ፈጣንና ግልጽ አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳለውና አሠራሮች ለሙስና እና እንግልት የተጋለጡ መሆን እንደሌለባቸው ያሳያል። ይህ ካልሆነ ደግሞ በቦታው ያለው ማንኛውም የተመረጠ ተወካይ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ በሥራው ጉድለት ምክንያት በሕዝብ እምነት ካጣ የመነሳት ወይም ተጠያቂ የመሆን  ግዴታ እንዳለበት ያመለክታል።

በተለይም መንግሥት ለሕዝቡ ከሚሰጣቸው መሠረታዊ አገልግሎቶች  የማህበራዊ አገልግሎቶች የሚባሉት የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ፣ ጤና እና እውቀት ለማሻሻል የሚሰጡ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ትምህርት ከቅደመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት (ዩኒቨርሲቲ) ድረስ ያለውን የትምህርት ዕድል ማመቻቸት፣ ትምህርት ቤቶችን መገንባት እና መምህራንን መቅጠር ያካትታል፡፡

ጤና ጥበቃ ደግሞ  ሆስፒታሎችንና ጤና ጣቢያዎችን መገንባት፣ የሕክምና መሣሪያዎችንና መድኃኒቶችን ማቅረብ እንዲሁም የክትባትና የበሽታ መከላከያ ዘመቻዎችን ማድረግ፤ ንጹሕ መጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን፣ ለሕዝቡ ንጹሕና አስተማማኝ የመጠጥ ውኃ ማቅረብ፣ የፍሳሽና የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓቶችን የመዘርጋት ኃላፊነት አለበት፡፡ በማኅበራዊ ዋስትና እና ድጋፍ በኩልም  ለአረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች እና አቅመ ደካሞች የሚደረጉ ድጋፎች፣ የጡረታ አበል አከፋፈል እና የአደጋ ጊዜ ዕርዳታዎች ማድረግን ያካትታል።

የኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች የሚባሉት ደግሞ መንግሥት ለማህበረሰቡ ከሚሠጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ  የሀገሪቱን የንግድ፣ የሥራ እና የልማት እንቅስቃሴዎች ለማቀላጠፍ የሚዘረጉ መሠረተ ልማቶች ናቸው፤ መጓጓዣ እና  መሠረተ ልማት ፣ የኃይል/ኤሌክትሪክ አቅርቦት  እንዲሁም ለቀን ተቀን ሕይወት እና ለኢንዱስትሪዎች የሚሆን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እና ማሰራጨት፣ የኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማት የፖስታ፣ የቴሌኮም  እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕዝብ እንዲደርሱ ማድረግ ነው። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41፣ 89 እና 90  የሰፈሩትን እነዚህ አገልግሎት አሰጣጦች መንግሥት በየጊዜው የማሳደግና የማሳለጥ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ  እንዳለበት ነው የተቀመጠው።

አንቀጽ 41 ንኡስ አንቀፅ 4 ላይም በዝርዝር እንደሰፈረው “መንግሥት ለሕዝብ የሚሰጣቸውን የጤና፣ የትምህርትና ሌሎችም የማሕበራዊ አገልግሎቶችን በየጊዜው እያደጉ በሚሄዱ የአሠራር ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የሚያስፈልገውን የሀብት መጠን የማቅረብ ግዴታ አለበት።” ሲል ይደነግጋል፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 90 ላይ እንደሰፈረው እነዚህ (ማኅበራዊ  ዓላማዎች) ፖሊሲዎች አቅም በፈቀደ መጠን ዜጎች ሁሉ የትምህርት፣ የጤና፣ የንጹሕ ውኃ፣ የቤት፣ የምግብ እና የማኅበራዊ ዋስትና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ መሥራት እንዳለባቸው ይገልጻል። ይህን ለማሳካት ደግሞ ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት መዘርጋት የግድ እና ወሳኝ ነው ይላል።

የሕዝብ ሉዓላዊነትና የመንግሥት ሥልጣንን በተመለከተ የሚያትተው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 ላይ የሀገሪቱ የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ በመሆኑ የመንግሥት ተቋማት የሚቋቋሙት ሕዝብን ለማገልገል ነው። ስለዚህ ማንኛውም የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋም ዜጋን ማዕከል ያደረገ እና ፍላጎቱን የሚያሳልጥ መሆን እንዳለበት ከመሠረታዊው የሕዝብ ሉዓላዊነት መርሕ የሚመነጭ እንደሆነ ነው።

የፌዴራል መንግሥት የፖሊሲና ስትራቴጂ የማውጣት ሥልጣን አንቀጽ 51 ንኡስ አንቀፅ 2 የፌዴራሉ መንግሥት የሀገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የልማት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ዕቅዶች የማውጣትና የማስፈጸም ሥልጣን አለው ሲል በዝርዝር አስቀምጧል። በዚህም  መንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና የዲጂታላይዜሽን (እንደ ፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ያሉ) አሠራሮችን የመዘርጋት ሕጋዊ መሠረት ያገኛል ማለት ነው።

በአጠቃላይ  ሕገ መንግሥቱ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎታቸውን በግልጽነት፣ በተጠያቂነት፣ ያለ አድልዎና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ በመስጠት የዜጎችን ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዳለበት ያስገድዳል። ይሁን እንጂ ዜጎች ከመንግሥት ማግኘት ያለባቸውን እና የጠየቁትን አገልግሎት በማግኘት በኩል ችግር እንዳለበት  የአማራ ክልል እርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በመሥከረም ወር የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ በሪፖርታቸው አሳታውቀዋል፡፡

ርዕሠ መሥተዳደር  መስተዳድሩ እንደገለፁት  በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የክልሉ መንግሥት የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት በትኩረት ይሠራል። እስካሁን ድረስ በክልሉ ቀልጣፋ፣ ግልፅነት እና ወጥነት ያለው የአገልግሎት አሠጣጥ  ሥርዓት ባለመዘርጋቱ የተነሳ ዜጎች ለአንድ አነስተኛ  ጉዳይ ተደጋጋሚ ምልልስ የሚያደርጉበት ጊዜአቸውን እና ገንዘባቸውን  የሚያባክኑበት ሁኔታ እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታየው ግልፅነት የጎደለው አካሄድ  ለብልሹ አሠራር እና ሙስና የተጋለጠ በመሆኑ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታ እና ርካታ እየቀነሰው እንደሚገኝ ነው ያነሱት፡፡ አብዛኞቹ ተቋማት በባሕላዊ እና አሁንም በወረቀት ላይ የተመሰረተ አሠራር የሚሠሩ እና የሚመሩ በመሆናቸው  የአገልግሎት አሠጣጡ ግልፅነት የጎደለው እና ቀርፋፋ አድረጎታል በማለት ርዕሰ መሥተዳደሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ዜጎች የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት በተለያዩ ተቋማት እንዲንከራተቱ በመገደዳቸው ተጨማሪ እንግልት መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ ችግሮች የሕዝቡን ቅሬታ ከማብዛቱ በላይ የክልሉን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የኢንቨስትመንት እና ሌሎች የታቀዱ የልማት ሥራዎች በተባለው ጊዜ እንዳይሠሩ በእጅጉ እንቅፋት ሆኖ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ስር የሠደደውን የአገልግሎት አሠራር ችግሮች እንዲሻሻሉ እና ዜጎችን ማዕከል ያደረጉ ቀልጣፋ አገልግሎቶች እንዲያገኙ የሚያስችል ሥራ በቀጣይ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል፡፡

በቀጣይ ሥራ ሕዝብን  ያማረሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት እንደሚደረግም እርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ  ገልጸዋል።  ዜጋን መሠረት ያደረገ የአገልግሎት አሠጣጥ ለማቅረብ እንደሚሠራም ተናግረዋል። በቀጣይ አምስት ዓመታት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን ለመፍታት በሚደረገው ሂደት እና ጥረት ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት እንደሚደግፍ ቃል ገብተዋል፡፡

የህግ አንቀጽ

የዲሲኘሊን ጥፋት አይነቶች

  • የዲስፕሊን ቅጣት ዓላማ የመንግሥት ሠራተኛው በፈጸመው የዲስፕሊን ጉድለት ተፀፅቶ በአመለካከቱና በሥነ-ምግባሩ እንዲታረምና ብቁ ሠራተኛ እንዲሆን ለማስቻል ወይም ለማሰናበት እንደሆነ ነው አዲሱ የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 አንቀጽ 96 ላይ የተደነገገው፡፡
  • ከባድ የዲስፕሊን ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶች ምን ምን እንደሆኑ በአዋጁ አንቀፅ 98 ላይ በዝርዝር ስናየው
  • ሕጋዊ ትዕዛዝን ባለማክበር፣ በቸልተኝነት፣ በመለገም፣ ወይም ሆነ ብሎ የአሠራር ሥነ-ሥርዓት ወይም የመንግስትን ፖሊሲ ባለመከተል በሥራ ላይ በደል ማድረስ፤
  • ጉዳዮችን ሆን ብሎ ማዘግየት ወይም ባለጉዳዮችን ማጉላላት፤ ተቋምን አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር መሠማራት ወይም ሥራ እንዳይሠራ ሆን ብሎ ማወክ ወይም ከሚያውኩት ጋር መተባበር፤
  • በተደጋጋሚ ከሥራ መቅረት ወይም የሥራ ሰዓት አለማክበር፤ በሥራ ቦታ በጠብ አጫሪነት መደባደብ፤
  • ጉቦ መቀበል ወይም እንዲሰጠው መጠየቅ፤ የሌብነት ወይም የእምነት ማጉደል ድርጊት መፈጸም፤
  • የማታለል ወይም የማጭበርበር ድርጊት መፈጸም፤ በመሥሪያ ቤቱ ንብረት ላይ ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ፤
  • በሥልጣን አለአግባብ መገልገል፤ በሥራ ቦታ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት መፈፀም ናቸው፡፡

ምንጭ- የአማራ የፍትሕ እና ሕግ ኢንሲቲትዩት

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የጥቅምት 9 ቀን 2019 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here