ከዚህ በፊት በአምስት ሺህ እና አስር ሺህ ሜትር ውድድሮች የዓለም አትሌቲክስ አፍቃሪ በጉጉት የሚጠብቀው የትኛው ኢትዮጵያዊ ወርቁን እንደሚወስድ እንጂ አሸናፊው ከየት ሀገር እንደሚመጣ አልነበረም:: ዛሬ ላይ ግን የቀደመው የኢትዮጵያ የመም ንግሥና በጎዳና ላይ (የአስፋልት) ሩጫ እየተተካ፣ ብሄራዊ ክብር በአትሌቶች እና በግል ማናጀሮች የጥቅም ስሌት እየተሸረሸረ ነው:: ያ ወርቃማ ዘመን ዛሬ ላይ እንደ ጧት ጤዛ እየሟሸሸ ይገኛል:: አዲሱ የአትሌቲክስ ትውልድ ቀዩን የመሮጫ መም ወደ ጎን ገፍቶ ፊቱን ወደ ጥቁሩ የአውሮፓ እና የአሜሪካ አስፋልት ላይ አዙሯል:: ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ህልውና አጣብቂኝ ወስጥ እየከተተ ነው::
ኢትዮጵያውያን አትሌቶቹ ከመም ውድድር ይልቅ ወደ ጎዳና ላይ ሩጫ ፊታቸውን ያዞሩበት ዋነኛው ምክንያት ዓለም አቀፋዊ የውድድር ምህዳሩ መቀየር እና የገንዘብ ሽልማቱ ጉዳይ መሆኑን በአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከ18 ዓመት በታች አሰልጣኝ የሆነው ታምራት ታደሰ ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ የስፖርት ክፍል ዝግጅት ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል::
አሁን ላይ በበለጸጉት ሀገራት በተለይም በአውሮፓ የነበሩት የአምስት ሺህ እና የአስር ሺህ ሜትር የትራክ ውድድሮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መጥቷል:: የውድድሮቹ አዘጋጆችም ከመም ይልቅ የጎዳና ላይ ውድድሮችን ማብዛት መጀመራቸው አትሌቶቹ የመም የውድድር እድሎችን እያጡ እንደሆነ አሰልጣኙ አልሸሸገም:: ከዚህ በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጁ የማራቶን፣ የግማሽ ማራቶን እና ሌሎች የጎዳና ላይ ውድድሮች ከመም ውድድሮች በተሻለ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ሽልማት እና ማበረታቻ አላቸው:: እናም ገና በለጋ እድሜያቸው አትሌቶች የተሻለ ገቢ ፍለጋ የጎዳና ላይ ውድድሮችን ቀዳሚ አማራጭ አድርገው እየወሰዱ ይገኛሉ::
ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ደግሞ የቪዛ ክልከላ ነው:: “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም አቀፍ የመም ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ከፍተኛ እንግልት እየገጠማቸው እና እየተከለከሉ ይገኛሉ:: እናም በርካታ አትሌቶች በቪዛ ምክንያት በብዛት ወደ አስፓልት ሩጫዎች እንዲያዘነብሉ አስገዳጅ ሁኔታን ፈጥሯል:: ይህ የጎዳና ላይ ፍልሰት በሀገር ውስጥ ካለው እጅግ አሳሳቢ የመሰረተ ልማት እጥረት ጋር ሲዳመር ችግሩን ይበልጥ ውስብስብ ያደርገዋል” ብሏል አሰልጣኝ ታምራት::
ኢትዮጵያ ለአትሌቲክስ ስፖርት የማይነጥፍ የተፈጥሮ ፀጋ ያላት ሀገር ናት። በየርቀቱ እንደ አብሪ ኮከብ የሚወረወሩ አትሌቶች የሚፈለፈሉባት ሀገር ጭምር ናት:: ይሁን እንጂ በዘመናዊ መንገድ ቀርፆ ለማውጣት የሚያስችል በቂ እና ደረጃውን የጠበቀ የመሮጫ መም አሁንም የላትም:: በአንድ ወቅት የአትሌቶች ዋነኛ መፈጠሪያ እና መለማመጃ የነበረው አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ላይ በመሆኑ ለውድድርም ሆነ ለልምምድ ዝግ ከሆነ ሰነባብቷል::
በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ለልምምድ ክፍት የሆኑት የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እና በሱሉልታ የሚገኘው የቀነኒሳ በቀለ የመሮጫ መሞች ብቻ ናቸው:: በክልል ከተሞች እንደ ባህር ዳር፣ ድሬዳዋ እና ወልዲያ ያሉ ትልልቅ ስታዲየሞች ውስጥ የመሮጫ መሞች ቢኖሩም እነዚህ ስፍራዎች አትሌቶችን ከማፍራት እና መደበኛ የመም ውድድሮችን ከማስተናገድ አንፃር ትርጉም ያለው ሥራ እየሠሩ አይደለም:: ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች የመሮጫ መሞች ቢኖሩም ብቁ የሆኑ አትሌቶችም ሆኑ ማናጀሮቻቸው ወደ እነዚህ አካባቢዎች ሄደው የሚወዳደሩበት አሰራር አልተዘረጋም:: እናም ተተኪ አትሌቶች በቂ የመም ልምምድ ሳያደርጉ እና አቅማቸውን በደንብ ሳያዳብሩ በቀጥታ ወደ ጎዳና ላይ ውድድር ለመግባት ይገደዳሉ::
“ታዳጊ አትሌቶች ብቃታቸውን የሚያሳድጉበት እና የመም ላይ ቴክኒኮችን የሚማሩበት በቂ ስታዲየም ባለመኖሩ ገና በለጋ እድሜያቸው ወደ ጎዳና ሩጫ እንዲገቡ እየተገደዱ ነው፤ ይህም የትራክ ላይ መሰረታቸውን በማጥፋት ለረጅም ጊዜ ውድድር ብቁ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ይገኛል” በማለት በአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከ18 ዓመት በታች አሰልጣኝ የሆነው ታምራት ታደሰ ስጋቱን ይገልፃል::
አብዛኛዎቹ አትሌቶች የሚመጡት ከገጠር አካባቢ በመሆኑ ተፈጥሯዊ የሆነ የፅናት እና የጉልበት አቅም አላቸው:: ልምምዳቸውንም የሚያደርጉት በጫካ፣ በኮረብታ እና በተራራማ ስፍራዎች በመሆኑ ለሀገር አቋራጭ እና ለረጅም ርቀት ሩጫዎች ተስማሚ የሆነ አካላዊ ቁመናን ይገነባሉ:: ነገር ግን የመም ውድድር ጠፍጣፋ እና ፈጣን ሜዳ ላይ የሚደረግ በመሆኑ ከተራራ ልምምድ በቀጥታ ወደ መም ወርዶ ስኬታማ መሆን አዳጋች ነው:: የመሮጫ መም ልምድ የሌለው አትሌት የፍጥነት፣ የፍፃሜ አጨራረስ እና የታክቲክ ክህሎት ስለሚጎድለው በውድድሮች ላይ በቀላሉ ስኬታማ እንደማይሆን የትራክ ኤንድ ፊልድ መረጃ ያመለክታል::
በቂ የመም ልምምድ ሳያደርጉ አቅማቸውን ከማጎልበታቸው በፊት ወደ አስፓልት እና ረጅም ማራቶን የሚገቡ አትሌቶች የስፖርት ዘመናቸው እጅግ አጭር እንዲሆን ያደርገዋል:: እንደ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ያሉት የቀድሞ ጀግኖች ወደ ማራቶን ከመግባታቸው በፊት ለዓመታት በመም ላይ ተወዳድረው ፍጥነታቸውን እና ታክቲካቸውን አዳብረው ነበር ወደ ጎዳና ውድድር ያመሩት::
አሁን ላይ ጥቂት አትሌቶች ራሳቸውን ጠብቀው በመም ብቻ የሚወዳደሩ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ግን ወደ ጎዳና ውድድር መውጣትን መርጠዋል:: የመም ልምምድ ሳያደርጉ በቀጥታ በአስፓልት ላይ መሮጥ ለአትሌቶች ጤና እና አካላዊ ጥንካሬ ከፍተኛ አደጋ አለው:: አስፓልት ላይ የሚደረግ ተደጋጋሚ ልምምድ እና ውድድር የጡንቻ መዛልን፣ የእግር መገጣጠሚያ ጉዳቶችን እና የጥንካሬ መዳከምን ያስከትላል:: ከዚህም ባለፈ አትሌቶቹ የአትሌቲክስ ህይወታቸውን ጨርሰው ከስፖርቱ ዓለም በለጋ እድሜያቸው እንዲገለሉ ዋነኛ ምክንያት እየሆነ ነው::
አትሌቶች የትኛው ውድድር ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው የሚወስኑት ከአትሌቶቹ ክለቦች ይልቅ የውጭ ዜግነት ያላቸው የግል ማናጀሮች ናቸው:: ማናጀሮች ደግሞ በዋነኝነት የሚንቀሳቀሱት ለገንዘብ ጥቅም በመሆኑ አትሌቶቹ ሀገርን ከሚወክሉበት የመም ውድድር ይልቅ አትራፊ ወደሆኑት የጎዳና ላይ ውድድሮች እንዲሄዱ ከፍተኛ ግፊት ያደርጋሉ:: ፌዴሬሽኑ እነዚህን ማናጀሮች መቆጣጠር እና አትሌቶቹን ማስተዳደር የሚችልበት ጠንካራ ስርዓት መዘርጋ አለበት የሚለው የአሰልጣኝ ታምራት ሀሳብ ነው:: በተጨማሪም አትሌቶች ለብሄራዊ ግዳጅ ሲጠሩ በሆቴል አቀባበል፣ በምግብ ስርዓት እና በስነ ልቦና ዝግጅት በኩል የሚታየው ክፍተት አትሌቶቹ በፌዴሬሽኑ ላይ እምነት እንዲያጡ እና ትኩረታቸውን በግል ውድድሮቻቸው ላይ ብቻ እንዲያደርጉ ገፋፍቷቸዋል::
እየደበዘዘ የመጣውን የኢትዮጵያ የመም ታሪክ ወደ ቀድሞ ክብሩ ለመመለስ ፈጣን እና መዋቅራዊ ለውጦች ያስፈልጋል ይላል- አሰልጣኝ ታምራት:: መንግስት እና ፌዴሬሽኑ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ግንባታ እና ጥገና ላይ ሰፊ መዋእለ ንዋይ በማፍሰስ የመሮጫ መምን ማዘመን ያስፈልጋል:: “ስታዲየም ውስጥ የሚገኙ የመሮጫ መሞችን ታዳጊ አትሌቶች በነፃነት ልምምድ እንዲሰሩባቸው ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል፤ ለአብነት በአሰላ የሚገኘው ስታዲየም ክፍት ባለመሆኑ ታዳጊዎች አጥር እየዘለሉ ለመለማመድ የሚገደዱበት አሳፋሪ አሰራር በአስቸኳይ ሊወገድ ይገባል:: በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ ዘመናዊ የስፖርት አመጋገብን፣ ስነ ልቦናዊ ዝግጅትን እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ አትሌቶችን ማብቃት ያስፈልጋል” ሲል አሰልጣኝ ታምራት ታደሰ ይናገራል::
ማናጀሮች በአትሌቶች ላይ ያላቸውን ያልተገደበ ስልጣን በሕግ እና በስርዓት ማዕቀፍ ውስጥ በማስገባት አትሌቶች ከግል ጥቅማቸው ጎን ለጎን የሀገራቸውን እና የወደፊት እጣ ፈንታቸውን ያገናዘበ ውሳኔ እንዲወስኑ የሚያስችል ጠንካራ ብሄራዊ ተቋም መገንባት ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ነው::
እየደበዘዘ የመጣውን የኢትዮጵያ የመም ታሪክ ወደ ቀድሞ ዝናው ለመመለስ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምን እየሰራ እንደሆነ ለመጠየቅ ያደረግነው ሙከራ ስልክ ባለማንሳታቸው አልተሳካም፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


