የበረዶ ዝንቦች በውስጣቸው ሙቀት በመፍጠር እና በሚያመርቱት ገንቢ ምግብ ወይም ፕሮቲን ቅዝቃዜን በቆዳቸው ዘልቆ እንዳይገባ በመከላከል ተቋቁመው መቆየት እንደሚችሉ ሣይንስ ዴይሊድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
በአሜሪካ የኖርዝዌስተርን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ባካሄዱት አዲስ ጥናት የበረዶ ዝንቦች “ስኖውፍላይስ” በውስጣቸው ሙቀት በመፍጠር፣ ፀረ ቅዝቃዜ ገንቢ ምግብ አምርተው በማከማቸት – ቅዝቃዜ ዘልቆ ወደ ውስጣቸው እንዳይገባ በመከላከል ንቁ ሆነው መቆየት እንደሚችሉ አረጋግጠዋል፡፡
የጥናቱ ግኝት በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ፍጥረታት እንዴት አድርገው አስቸጋሪ ሁነቶችን እንደሚላመዱ አዲስ እውነትን ያሳየ መሆኑን ነው ያሰመሩበት – ተመራማሪዎቹ፡፡
በስዊዲን የሉንዳ ዩኒቨርስቲ የስነ ህይወት ፕሮፌሰሩ ማርከስ ስቲንስመር ከአቻ ተመራማሪዎች ጋር በመተባበር የበረዶ ዝንቦችን የስነ ህይወታዊ አወቃቀር መርምረዋል፡፡ በውጤቱም ልክ በቀዝቃዛው ”አርክቲክ” ውስጥ እንደሚኖሩት ዓሣዎች ፀረ ቅዝቃዜ ፕሮቲን እንደሚያመርቱ ነው የደረሱበት-ተመራማሪዎቹ፡፡ በተጨማሪም በበረዶ ዝንቦች የተመረተው ፕሮቲን ከበረዶ ቅንጣቶቹ ጋር በቆዳቸው ስር ተከማችቶ ቅዝቃዜውን ዘልቆ እንዳይገባ ባለበት አግዶ ማስቀረቱን ተገንዝበዋል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


