በዓላት እና ኢትዮጵያ ልዩ ቁርኝት አላቸው፤ በዓላት ሲነሱ ኢትዮጵዊ ውበት፣ አንድነት፣ መተሳሰብ፣ የሀገር ፍቅር እና መሰል ትውፊቶች አብረው ይገለጣሉ፡፡ በዓላት ሲደርስ ቤት ይደምቃል፣ ቤተሰብ በሀሴት ይሞላል፤ ከተማ እና ገጠሩ ከወትሮው በተለዬ ይነቃቃሉ፣ በገበያ ቦታዎች መጨናነቅ ይበዛል… ይህ የደስታ እና የአንድነት አየር ግን በራሱ አይመጣም፤ ከኋላው የማይታይ ትልቅ ትጋት እና ድካም አለው። በዓላት በቤት ውስጥ እና በውጭ አብዛኛው የድርሻቸውን ለመወጣት የሚጣደፉበት ወቅትም ነው፡፡
የበዓላት ወቅት የምግብ ዝግጅቱ ከቀላል የምግብ ዝግጅት በላይ ነው፤ የቤተሰብ ዕሴትን፣ የባሕል ቅርስን፣ አንድነትን እና የፍቅር መልዕክትን እንዲሁም ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያዊ ጣዕም እንዲኖራቸው በማድረግ መልዕክትን ያስተላልፋሉ።
ለመሆኑ የበዓል ሰሞን የሴቶች ሁኔታ ምን ይመስል ይሆን? ቤተሰብን ማሰባሰብ፣ የእርስ በርስ ተግባቦትን ማሳደግ፣ ሕፃናትን ስለበዓሉ ክብር ማስተማር እና የተለያዩ ባሕላዊ ክዋኔዎችን ማስቀጠል በዋናነት ለሴቶች የተቸሩ የሚመስሉ ገጸ በረከቶች ናቸው፤ ይህ ሲሆን ደግሞ ሀገር ተረካቢዎች በኢትዮጵያዊነት ፍቅር እንዲያድጉ፣ አንድነትን እንዲያጎለብቱ፣ ፍቅርን እና መተሳሰብን እንዲያጎለብቱ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው፡፡
ለዚህ ማሳያችን ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ወ/ሮ ታገኝ ሙጨ ናቸው፤ ወይዘሮዋ የበዓል ሰሞን ዝግጅትን እና ትውስታዎችን በተመለከተ ከበኵር ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ወ/ሮ ታገኝ “የበዓል ቀናት ለኔ በሕይወቴ የምደሰትባቸው፣ ድባቡን ለማሳመር ቀደም ብየ ዝግጅት የማደርግባቸው እንዲሁም በጉጉት የምጠብቃቸው ናቸው” በማለት ነው ሐሳባቸውን የጀመሩልን።
“ከልጅነት ጊዜዬ ልጀምር” ሲሉም ቀጠሉ፤ “በተለይ የፋሲካ በዓል እናቴ ቅዳሜ ማታ ቤተክርስቲያን ሄዳ ስለምታድር የቤቱ ብቸኛ ሴት ልጅ እኔ በመሆኔ በሌሊት ዶሮ አሳርጀ፣ አጥቤ፣ ሽንቁርት ከትፌ እሠራለሁ፡፡ ሥራየን ካጠናቀቅሁ በኋላ ያለእንቅልፍ መምጣቷን በጉጉት ስጠባበቅ እቆያለሁ፡፡ ከመጣች በኋላ በጋራ ጾሙን እንፈታለን፡፡ ከዛም በኋላ አይደክመኝም፣ አልተኛም፡፡ የበዓላት ቀናት ደስ ብሎኝ ስለምሠራ ቀኑን በየዓመቱ በጉጉት ነው የምጠብቀው” በማለት ነው ሐሳባቸውን ያጠናከሩት።
በዓላት ሰዎች የሚሰባሰቡበት ነው፤ በተለይ በአንድ ግቢ ያሉ ጎረቤታሞች ደግሞ ከመጠራራት ባለፈ ቀደም ብሎ ምግብ ዝግጅት ላይም መሰባሰብ የተለመደ ነው፤ ባለታሪካችን ወ/ሮ ታገኝም ይህንኑ በማስታወስ “ያኔ በሌሊት ዶሮ ሲሠራ ከግቢ ወጥተን አራት ጎረቤታሞች ተራውን ድስት ጥደን ነበር የምንሠራው፤ ትዝታው ልዩ ነው” ብለውናል።
ባለታሪካችን እንደነገሩን በወቅቱ የልጅነት የዕድሜ ክልል ላይ ስለነበሩ ዶሮ ማጠብ እና መሥራት እናታቸው በሚገባ ቢያስተምሯቸውም ከሌሎች ጋር በተመሳሳይ ፍጥነት ማከናወን የቻሉት ግን መተጋገዝ አንዱ የበዓል መገለጫ ነው፡፡ በተለያም ወይኒቱ የተባለች ጎረቤታቸው በአግባቡ ታግዛቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። የነበረውን መልካም ጉርብትና በሚገባ የተገነዘቡት እናቷም ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ልጃቸው የተሰጣትን ሥራ (ዶሮ ወጥ መሥራት) በአግባቡ እንደምትፈጽመው እምነት ስለነበራቸው ነው ኃላፊነቱን የሚሰጧት።
ከእናታቸው በተጨማሪ ጎረቤታቸው ወይኒቱ ስላደረገችላቸው መልካም ተግባር ሲናገሩም “የራሷን ዶሮ ስትበልት ʽይህን እንዲህ አርጊውʽ እያለች በመበለቱ፣ በማጠቡ እና በመመጠኑ እያገዘችኝ ከነሱ እኩል እንድሆን ታደርግ ነበር።
ዶሮ አሠራርን ከእናቴ ያላነሰ እሷ ነች በደንብ ያስለመደችኝ” በማለት ታስታውሳታለች።
ወ/ሮ ታገኝ ሌላም የበዓል ትውስታቸውን አካፍለውናል፤ መተጋገዝ፣ አንዱ የሌለውን ያለው መሙላት ደግሞ ባለታሪካችን ያነሱልን ትውስታ ነው፡፡ ትውስታቸውንም ከፊታቸው ላይ በሚነበበው የትዝታ ባሕር ውስጥ ሆነው “ዶሮ ወጡን ስንሠራ ካንዱ የሌለውን ከሌላው እየሞላን አሳምረን ነበር የምንሠራው። ቅቤ አንዳችን ቀድመን ይዘን ከወጣን ሁሉም ላይ ይጨመራል። አንዱ ቀድሞ ቢጨርስ ያልጨረሰውን ያግዛል እንጅ ትቶ ወደ ቤቱ አይገባም ነበር። በጣም ደስ የሚል ጉርብትና እና ደስ የሚል ጊዜ ነበር”በማለት ነው ያጫወቱን።
ወ/ር ታገኝ ሙጨ በአሁኑ ወቅት ባለትዳር እና የልጆች እናት ናቸው፤ አሁንም በዓልን ለማክበር ቀድመው ነው የሚዘጋጁት። በተለይ የፋሲካ በዓል ልዩ ትውስታ ስላለባቸው በናፍቆት የሚቀበሉት በዓል መሆኑን ነግረውናል። በዓላት ከመቼውም ጊዜ በላይ መተጋገዝ እና ያለው ለሌለው በማገዝ በተግባር ይገጥባቸዋል፤ የወ/ሮ ታገኝ ተሞክሮም ይህን ነው የሚያረገግጥልን፡፡ በተለይ በማንኛውም ሥራ ላይ ባለቤታቸው እንደሚያግዛቸው ነው ሐሳባቸውን ያካፈሉን፡፡
በተለይ ደግሞ እርሳቸው የቤቱን ውስጥ ሥራ ሲያከናውኑ ባቤታቸው ደግሞ ዶሮውን፣ በጉን፣ ጨፌና ጭሳጭሱን ገዝቶ ይመጣል። በተጨማሪም “በዋዜማው ምሽት እኔ ዳቦ ስደፋ እሱ ከልጆቹ ጋር ቤቱን የማሳመር፣ ሶፋዎችን የማለባበስ ሥራ ይሠራል” ነው ያሉት።
ባታሪካችን እንደነገሩን በተለይ በፋሲካ በዓል ከዋዜማው ጀምሮ ሁሉም ዝግጅቶች ከተጠናቀቁ በኋላ ከቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ እና ጎረቤት ጋር በመጠራራት ያሳልፋሉ፤ በዚህ ወቅት ታዲያ ልጆችም ዋና የበዓሉ ድምቀት ይሆናሉ፡፡ የዚህ መሠረታዊ ምክንያት ደግሞ “ልጆች የሀገራችንን ውብ ባሕል እና ዕሴት በተግባራዊ ማደግ እና እነሱም ለተከታዮቻቸው ማስረከብ ስላባቸው ነው” ይላሉ፡፡
ወ/ሮ ታገኝ ትዳር ከመሰረቱ በኋላ የፋሲካ በዓል ዕለት ከንጋት ጀምሮ የሚያደርጉትን ተግባርም ሲያጫውቱን ፤ “የበዓሉ ዕለት ንጋት ላይ ሁላችንም ተያይዘን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄዳለን። ፈጣሪያችንን አመስግነን ከተመለስን በኋላ ለመግደፊያ ያህል ቁርስ ይበላል። ጨፌው ይጎዘጎዛል፣ ቡናው ይቆላል፣ ጭሱ ይጫጫሳል፣ የዶሮ ዐይን የመሰለው ጠላ እና ጠጅ ይቀርባል፡፡ ከዚያም ጎረቤቶች ይጠራሉ፣ ቤተሰቡ ሁሉ ይሰባሰባል፣ ከዚያ በኋላማ በቃ ደስታ ነው፣ ፌሽታ ነው” በማለት ነበር፡፡
የበዓሉ ድባብ እና ደስታ ደግሞ በቤታቸው ውስጥ የተገደበ አይደለም፤ ለዕለት ጉርስ የተቸገሩ ወገኖችን ማሰብ እና የበዓል ስሜት እንዲፈጠርባው ማድረግ የበዓል ወቅት ተግባቸው መሆኑን ወ/ሮ ታገኝ ሲናገሩ፤ “ምሽት ላይ የአቅማችንን ያክል ለነዳያን ለማብላት ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄዳለን። ልጆቻችንም አብረውን ነው የሚሄዱት፤ ይህንን እያዩ ማደግ አለባቸው የሚል ፅኑ አመለካከት ስላን ነው። ሁሌም በዓላትን እንዲህ ነው የምናሳልፈው። በዚህ ደግሞ እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ” በማለት ነበር።
የበዓላት ወቅት የሚከናወኑ ዝግጅቶች በማሕበረሰቡ ውስጥ የአብሮነትን መስተጋብር በእጅጉ ያጠናክራሉ፤ ይህም ሰዎችን ከተለያዩ የሕይወት ሁኔታዎች ሲመጡ በአንድ ቦታ ሰብስቦ መገናኘትና መጋራት ያስችላል። በእነዚህ ዝግጅቶች ውስጥ የምግብ መካፈል፣ የባሕላዊ ልብስ መልበስ እና መሰል ክዋኔዎች በሰዎች መካከል የተሳሰረ የማሕበራዊ ቅርበትን ይፈጥራል። ይህ የአብሮነት መንፈስ በማሕበረሰቡ ውስጥ እርስ በርስ መከባበርንና መረዳዳትን ያጠናክራል።
በሌላ በኩል፣ የበዓላት ክዋኔዎች ባሕላዊ ዕሴቶችን እና ልማዶችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ዋና መንገድ ሆነው ይገለጣሉ። ልጆች በእነዚህ በዓላት ውስጥ በተሳትፎ ሲካፈሉ የቤተሰብና የማህበረሰብ ታሪክ፣ የሥነ-ምግባር ዕሴቶች፣ እና የባሕል ልማዶችን በቀጥታ ይማራሉ።
የበዓላት ዝግጅቶች ከመዝናኛ በላይ ማሕበራዊ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ፣ ባሕልን የሚጠብቁ እና ትውፊትን የሚያስቀጥሉ ማሕበራዊ መድረኮች ናቸው።
(ሰናይት በየነ)
በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


