የምርጫ ቅስቀሳ የት ይካሔዳል?

0
108

ምርጫ ማለት ምን ማለት ነው? ለሚለው ፅንሰ ሀሳብ  ብላክስ ሎው የተባለ የሕግ መዝገበ ቃላት የሚከተለውን ትርጓሜ ሰጥቶታል፡፡ “ከበርካታ መብቶች ወይም መፍትሔዎች መካከል አንዱን የመምረጥና ሌላውን የመተው ሂደት ወይም አንድን ግለሰብ የፖለቲካ ሥልጣን እንዲይዝ የሚደረግ የመምረጥ ሂደት ነው” ይላል፡፡ የሀገራችን ሕግ ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀጽ 2 ንኡስ አንቀጽ (5) ላይ “በፌዴራልና በክልል ሕገ መንግሥታት እንዲሁም አግባብ ባላቸው ሕጎች መሰረት የሚካሄድ የጠቅላላ፣ የአካባቢ፣ የማሟያ ወይም የድጋሚ ምርጫ” መሆኑን ደንግጓል፡፡ ከዚህም በመነሳት በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ምርጫ ማለት ዜጎች ተወካዮቻቸውን፣ የሕግ አስፈፃሚውንና የሕግ ተርጓሚውን አካል በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚቆጣጠርላቸውን እንዲሁም የሚተዳደሩበትን ሕግ የሚያወጣላቸውን ከሦስቱ የመንግሥት አካላት አንዱ የሆነውን የሕግ አውጪ አካል የሚመረጥበት የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ መሆኑን መረጃው አመላክቷል፡፡

ምርጫ ዜጎች ይመራናል ለሚሉት ተፎካካሪ ፓርቲ ይሁንታቸውን የሚሰጡበት ሥርዓት ነው፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በመራጮች ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት የፖሊሲ አማራጮቻቸውን በተፈቀደላቸው ቦታ፣ ሚዲያ…ያቀርባሉ፡፡  ኢትዮጵያም ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ቅድመ ሁኔታዎችን በማካሄድ ላይ ናት፡፡

የኢትዮጵያ  ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ሰባተኛው  ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ መጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም  ድረስ እንደ ሚካሄድ አሳውቋል፡፡ የድምጽ መስጫ ቀን ግንቦት 24/2018 ዓ.ም መሆኑንም ቦርዱ  ጠቁሟል፡፡ በግንቦት ወር የሚያካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ አስቻይ ሁኔታ ባለባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ሁሉ እንደሚካሄድም አስታውቋል።

ቦርዱ የምርጫ ክልሎችን እና የምርጫ ጣቢያዎችን በመላው ሀገሪቱ እንዲያቋቁም በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀፅ 7 ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚሁ አዋጅ ምዕራፍ 3 ላይ እንደተመላከተው የምርጫ ዘመቻ / የምርጫ ቅስቀሳ / ለማካሄድ  አንድ እጩ ተወዳዳሪ በእጩነት ተመዝግቦ የመታወቂያ ካርድ ካገኘበት ቀን አንስቶ ምርጫው አራት ቀን እስኪቀረው ድረስ ከአስተዳደሩም ሆነ ከማዘጋጃ ቤት ፈቃድ መጠየቅ ሳያስፈልገው በጽሑፍ በማሳወቅ ብቻ ሕጋዊ ግዴታዎቹን በማክበር በራሱም ሆነ በደጋፊዎቹ አማካኝነት የድጋፍ ስብሰባዎችን የመጥራት ወይም ሰላማዊ ሰልፍ የማደራጀት መብት አለው፡፡ ለምርጫ ውድድሩ ይጠቅሙኛል ያላቸውን መረጃዎችም ከቦርዱ የማግኘት መብት እንደሚኖረው ተቀምጧል፡፡

እጩዎች በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ነፃ የአየር ጊዜ አግኝተው የመጠቀም መብት አላቸው፡፡  አዋጁም በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉትን  ሬድዮ፣ ቴሌቪዥን እና ጋዜጦችን ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለ አድልዎ የመጠቀም መብት እንዳላቸው አስፍሯል፡፡  መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን  አጠቃቀምን በተመለከተ ቦርዱ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶችን ባሳተፈ አካሄድ በሚያወጣው የድልድል መመሪያ መሠረት ይከናወናል፡፡

የመንግሥትም ሆነ የግል የመገናኛ ብዙኃን  አጠቃቀም፤ የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ እና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን   የሚመለከቱ  የሥነ     ምግባር   እና  የአፈጻጸም   መርሆዎችን   ቦርዱ   በሚያወጣው    መመሪያ  ይወስናል ፡፡

የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴዎችን ለማሳካት በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች የሚያስተዳድሯቸውን የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ጋዜጦችን እንዲሁም የስብሰባ አዳራሾች ዕጩ ተወዳዳሪዎች  ያለአድልዎ እንዲገለገሉባቸው ለማድረግ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ግዴታ አለባቸው፡፡

የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅትም ቅስቀሳ ለማድረግ የተከለከለባቸው  ቦታዎች  የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2019 አንቀፅ 46 ላይ ተቀምጧል፡፡ እነዚህም፦

  • ቤተ ክርስትያኖች
  • መስጊዶች፣
  • ወታደራዊ ካምፖች እና ፖሊስ ጣቢያዎች፤
  • የመማር ማስተማር ሂደት እየተከናወነ በሚገኝበት ወቅት በትምህርት ቤቶች እና በአካባቢያቸው በ200 ሜትር ርቀት ዙሪያ፤
  • ሕዝብ የዕለት ተለት ግብይት በሚፈፅምባቸው እና በተወሰኑ ቀናት በገጠርም ሆነ በከተማ በይፋ ገበያ እየተካሄደ በሚገኝባቸው ቦታዎች በሁለት መቶ ሜትር ዙሪያ ክልል፤
  • የመንግሥት ወይም የሕዝብ መደበኛ ሥራ በመከናወን ላይ የሚገኙባቸው የመንግሥት እና የሕዝብ ተቋማት ሥራቸውን በሚያከናውኑበት መደበኛ የሥራ ሰዓት እና ቦታ፣
  • ሌላ ሕዝባዊ ስብሰባ እየተካሄደ ባለባቸው ቦታዎች እና አካባቢዎች የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡

የሕግ አንቀጽ

አንድ የምርጫ ጣቢያ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 16 መሠረት ከታች የተዘረዘሩት ሥልጣን እና ተግባር ይኖሩታል፡-

መራጮችን ይመዘግባል፤

  • ከምርጫ ክልሉ የሚላኩ የምርጫ ቁሳቁሶችን ተቀብሎ በጥንቃቄ ይይዛል፤
  • በሕጉ መሠረት ሚስጥራዊነቱ የተጠበቀ ምርጫ ያካሂዳል፣
  • በሕጉ መሠረት የሚቀርቡለትን ቅሬታዎች ያስተናግዳል፣
  • የተሰጠውን ድምፅ ቆጠራ በማካሄድ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ በመለጠፍ ለሕዝብ ያሳውቃል፣
  • የምርጫ ሰነዶች እና ቁሳቁሶች በአግባቡ ተሞልተው እና ተጠብቀው ለምርጫ ክልሉ እንዲላኩ ያደርጋል፣
  • በዚህ አዋጅ አንቀጽ 15 (10) እና ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት የምርጫ ጣቢያውን አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ ሁለት አባላት ያስመርጣል፣
  • በምርጫ ሂደት ለሚከሰቱ ቅሬታዎች እና አቤቱታዎች ፈጣን ምላሽ ይሰጣል፤ የማስተካከያ ርምጃ ይወስዳል፣
  • ከቦርዱ፣ ከክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ወይም ከምርጫ ክልል የሚሰጡትን ሌሎች ተግባራት ያከናውናል፡፡
  • ከዚህም በተጨማሪ  በአዋጅ ቁጥር1162/2011 አንቀጽ 17 መሠረት ቦርዱ ከምርጫ ክልላቸው ርቀው በካምፕ ለሚኖሩ ወታደሮች፣ ሲቪል ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚማሩ ዜጎች፣ ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች እንዲሁም በማረሚያ ቤት ለሚገኙ የመምረጥ መብታቸው ያልተገፈፈ ዜጎች በምርጫ የሚሳተፉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መራጮቹ በሚገኙበት ቦታ ወይም አካባቢ ልዩ ምርጫ ጣቢያ ሊያቋቁም ይችላል፡፡

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here