እያስመረቁ  መመረቅ

0
128

ታሪኩ ከእናትነት እና ልጅነት የተሻገረ ነው፤ የታሪኩ ጅማሮ ደግሞ ከአንደኛ ክፍል ይነሳል፡፡ ይህም እስከ ከፍተኛ ትምህርት ቀጥሎ ሥራ ፍለጋንም ያስተሳሰረ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳን ታሪኩ ከአንደኛ ክፍል መነሻውን ቢያደርግም ለብዙኃኑ በአደባባይ የተገለጠው ግን ከሰሞኑ ነበር፤ ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ አስደናቂው ታሪክ ለአደባባይ የተገለጠበት ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከሰሞኑ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን በመደበኛ፣ በኤክስቴንሽን እና በክረምት መርሃ ግብሮች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ አንድ ሺህ 254 ተማሪዎችን በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ድግሪ አስመርቋል፤ ከእነዚህ መካከል ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ እስከ መጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታሉ እናት ልጅ ይገኙበታል።

የታሪኩ ባለቤቶች ወይዘሮ ትዕግስት ታከለ እና ሰላማዊት ተድላ ይባላሉ፤ ሰላማዊት ደግሞ የትዕግስት ልጅ ናት፡፡ ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ አብረው ነው ትምህርታቸውን የተከታተሉት፡፡ እንዴት? የሚለው ምክንያትን የሚፈልግ የሁላችንም ጥያቄ ነው፤ እናት በልጅነታቸው ነበር የልጅ እናት የሆኑት፡፡ ሰላማዊት ደግሞ በልጅነት የተሰጠች ልጃቸው ናት፡፡ በመሆኑም እናት ለትምህርት የደረሰ ዕድሜያቸውን በወቅቱ በይጠቀሙበትም ከልጃቸው ጋር አንደኛ ክፍል በመግባት ትምህርታቸውን መከታል ጀመሩ፡፡

እንደ እናት ልጃቸውን ይንከባከባሉ፤ እንደ ትምህርት ቤት ጓደኛ ደግሞ አብረው ትምህርታቸውን ይከታተላሉ፤ ይህ ሂደት ቀጥሎ ታዲያ እናት እና ልጅ በተመሳሳይ የትምህርት መስክ (ማኔጅመንት) በመጀመሪያ ዲግሪ ለመመረቅ በቅተዋል፡፡

ባለታኮቹ እናት እና ልጅ እንደነገሩን የዩኒቨርሲቲ ምደባቸው የተለያዬ ነበር፤ እናት ትዕግስትታከለ በደብረታ ቦር ዩኒቨርሲቲ እና ልጅ ሰላማዊት ተድላ ደግሞ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ነበር የተመደቡት፡፡ በኋላ ግን ጥያቄ የቀረበለት ትምህርርት ሚኒሥቴር በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በአንድ እንዲመደቡ ዕድሉን ሰጣቸው፡፡ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በመከታተልም ከሰሞኑ ለምረቃ በቅተዋል፡፡

ወይዘሮ ትዕግስት ታከለ “ልጅን እየመረቁ አብሮ መመረቅ ደስታው ወደር የለውም” ይላሉ። የምረቃ ቀናቸውም ከአንደኛ ክፍል የጀመረውን የእናት እና ልጅ የተመሳሳይ ክፍል የትምህርት ሂደት በአደባባይ የሚናገሩበት ልዩ ቀናቸው እንደሆነ አጫውተውናል።

በቆይታቸው ቤተ መጻሕፍት አብሮ መሄድ፣ ማጥናት፣ መረዳዳት እና መሰል የየዕለት ክዋኔዎች እንደ ክፍል ጓደኛ የሚፈጽሟቸው ተግባራት ናቸው፤ ልጅ ጊዜዋን በአግባቡ እንድትጠቀም፣ ለማንኛውም መሰናክል እንዳትበገር፣ አሻግራ እንድትመለከት በየዕለቱ ምክር መለገስ ደግሞ ወይዘሮ ትዕግስት እንደ እናትነታቸው በየዕለቱ የሚያከናውኗቸው ተግባራት መሆናቸውን ነው የነገሩን፡፡

ከአንደኛ ክፍል መነሻውን ያደረገው የእናት እና ልጅ የትምህርት ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም፤ “በዚህ ዕድሜ ተምረሽ ለዚያውም ከልጅሽ ጋር የት ልትደርሽ ነው? እያሉ ለማሳቀቅ የሚሞክሩ ጥቂቶች አልነበሩም  ነበሩ” የሚሉት ወይዘሮ ትዕግስት ታከለ፤ ለትችቱ ግን ቦታ እንዳልሰጡት፣ እንደማይሰጡትም ነው የተናገሩት፡፡

ይህ ጥንካሬ በአሁኑ ወቅት ታዲያ ፍሬ አፍርቶ ከልጃቸው ጋር በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲ፣ በተመሳሳይ ዕለት እንዲሁም በተመሳሳይ የትምህርት መስክ በመጀመሪያ ዲግሪ በመመረቅ ለስኬት በቅተዋል። ትምህርት ዕድሜ እንደማይገድበው በተግባር በማሳየታቸው ደስታቸው ወደር እንደሌለውም ገልፀውልናል።

“ሲበዛ ዕድለኛ ነኝ፤  ደስታዬን ለመግለጽ ቃላት አቅም እንዳጡ ይሰማኛል” በማለት ሐሳቧን የጀመረችልን ደግሞ ከእናቷ ጋር የተመረቀችው  ሰላማዊት ተድላ ናት፤ ለዚህ ደግሞ የእናትነት ፍቅር ሳይለያት ከማደግ ባለፈ እስከ ዩኒቨርሲቲ የዘለቀ  የዘወትር እገዛ ማግኘቷ ነው። ከእናቷ ጋር መማሯ ደግሞ ሰዓቷን በአግባቡ እንድትጠቀም፣ ባልተገባ ቦታ እንዳትውል እና ለስኬት እንድትበቃ እገዛው ከፍ ያለ መሆኑን ነግራናለች።

ሰላማዊት ተድላ እናቷ ለራሷ ስኬት መድረስ ብቻ ሳይሆን እርሷንም እያበረታቱ ለዚህ ስኬት ስላበቋት የተለዬ የደስታ ስሜት እንደፈጠረላት በማንሳት፤ “እናቴ   ለሁሉ ምሳሌ የምትሆን ናት፤ በዚህም ኩራት ይሰማኛል” ብላለች።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በየወሩ የሚያስፈልጋቸው ወጪ ቀላል የሚባል አይደለም፤ ሴትነት በራሱም ተጨማሪ ወጪን ይጠይቃል፤ እናት እና ልጅ በዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ በመሆኑ የወጭው ነገር እንዴት ተቻለ? የሚለው ለባለታሪኮቹ ያስከተልነው ጥያቄ ነበር፤ ከቤተሰብ የሚደረግ ድጋፍ  ደግሞ ምንጩ እንደነበር ነግረውናል፡፡

መረጃ

የጥናት ዘዴዎች

  • ይህም በዋናነት ይዘትን መሠረት አድርጎ የጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀትን ይጠይቃል፡፡
  • በቂ እረፍ እና እንቅልፍ ማግኘት ፦ ይህም የማስታወስ ችሎታን ከፍ ለማድረግ፣ ጥያቄዎችን በአግባቡ ተረድቶ ምላሽ ለመስጠት ያግዛል፡፡
  • ጥናትን ሁሌም በአነጋግ መጀመር ፦ ይህ ሰዓት አዕምሮ እረፍት አድርጎ በአዲስ መንፈስ ሁሉንም ነገር የሚጀምርበት በመሆኑ ውጤታማ ለመሆን ይረዳል፡፡
  • የይዘቶቹን አንኳር ጭብጦች በማስታወሻ ደብተር ማስፈር፣ አዳዲስ ቃላቶችን መዞ ማውጣት እና ትርጉማቸውን ማፈላለግ ይመከራል፡፡
  • ፀጥ ያለ ቦታን መምረጥ፣
  • ከተንቀሳቃሽ ስልክ ነጻ መሆን፣
  • ጥናትን ይዘቱ ከባድ ነው ከሚባለው የትምህርት አይነት መጀመር፣
  • ያለፉ ፈተናዎችን እና መልመጃዎችን መሥራት ተገቢ ነው፡፡

ምንጭ፡- ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ድረ ገጽ፣ ስቱደንት ዶት ኮ

 

(ተክለብርሃን ፈንታ)

በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here