በዙሪያቸው ያለው ዓለም ተቀይሯል። መንገዱ፣ አየሩ፣ ሰዎቹ፣ ቴክኖሎጂው… ሁሉም አዲስ ነው። አንዳንድ ሰዎች ግን ትናንት ላይ ቆመው በሌለ መድረክ ላይ የትናንትናውን ቴአትር ለመተወን ይጥራሉ። “ድሮ እኮ እኔ ማንም ደፍሮ የማያየኝ ባለስልጣን ነበርኩ!፣ የዚያ መሥሪያ ቤት የልብ ትርታ እኔ ነበርኩ!፣ የእኔ ፋሽን እኮ ከተማውን ያነጋግር ነበር!” ይላሉ።
ዓለም በፍጥነት ወደ ፊት እየገሰገሰች እነሱ ግን ወደ ኋላ ዞረው ይጓዛሉ። የትናንት ማንነታቸው፣ ስልጣናቸው፣ ውበታቸው፣ ወይም ያነበቡት አንድ መጽሐፍ ላይ ተቸንክረው ቀርተዋል። እነዚህ ሰዎች አያናድዱም፤ ይልቁንም የሚያሳዝኑ ናቸው። ምክንያቱም በህይወት እያሉ የሞቱ ይመስላሉና።
ታላቁ የቻይና የጦር ሊቅ ሳን ዙ ሕይወትንም ሆነ ጦርነትን ከውሃ ጋር ያመሳስለዋል። “ውሃ ቅርፁን እንደሚፈስበት መሬት ገፅታ እንደሚቀይር ሁሉ ድልም እንደየሁኔታው ይቀያየራል” ይላል። የትናንት እውቀትህን ወይም የቀድሞ ሹመትህን ዛሬ ላይ ለመተግበር መሞከር በደረቀ የድንጋይ ቋጥኝ ላይ ጀልባ ልቅዘፍ ብሎ እንደመታገል ነው። ትናንት ያዋጣህ ስልት፣ የዛሬው ትልቁ ድክመትህ ሊሆን ይችላል። ዓለም ሲቀየር አብሮ የማይቀየር አስተሳሰብ ልክ እንደ ደረቅ እንጨት በዘመኑ ማዕበል ይሰበራል።
የስትራቴጂ ጠቢቡ ኒኮሎ ማኪያቬሊ ስለ ስልጣንና ፖለቲካ ሲሞግት እንዲህ ይላል፤ “አንድ ሰው ውድቀቱ የሚጀምረው አካሄዱን ከዘመኑ መንፈስ ጋር ማስማማት ሲያቅተው ነው”። ትናንት በጭካኔው ወይም በጥበቡ ያሸነፈ ሰው ዛሬ አውዱ ተቀይሮ መተሳሰብ ሲያስፈልግ ያንኑ የድሮ ካርዱን ቢመዝ ወድቆ ይቀራል። ‘ድሮ’ የሚለው ቃል ለማኪያቬሊ የመቃብር ስም ነው። ስኬት ማለት የነፋሱን አቅጣጫ አይቶ ሸራን ማስተካከል እንጂ ካለፈው ነፋስ ጋር መታገል አይደለም።
የዓለምን ግማሽ ያስተዳድር የነበረው የሮም ንጉሥና ፈላስፋ ማርክስ ኦሪሊየስ ዘውድ አድርጎ እንኳን በስልጣኑ አይታበይም ነበር። ለራሱ በማስታወሻው ላይ እንዲህ ብሎ ይፅፋል፤ “ዓለም በማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ ናት። ታላቁ እስክንድርም ሆነ የእስክንድር በቅሎ ነጂ ሲሞቱ እኩል አፈር ሆነዋል፡፡” ማርክስ እንደሚያስተምረን “ድሮ ባለስልጣን ነበርኩ” ብሎ መኩራራት የድንቁርና ጥግ ነው። ያ ስልጣን የአንተ አልነበረም፤ የጊዜ የውሰት እቃ እንጂ የሚለውን ነው። በትናንት ዝናህ የምትታበይ ከሆነ፣ በውሰት ልብስ እንደሚያጌጥ ለማኝ ነህ ይላል።
ከስቶይሲዝም ፍልስፍና አስተማሪዎች አንዱ ሴኒካ ሰዎችን የሚኮንነው “ጊዜያቸውን በከንቱ ስለሚያባክኑ” ነው። ላለፈው እያለቀሰ ወይም ባለፈው ማንነቱ እየተመፃደቀ ዛሬን የሚያባክን ሰው ገና ሳይኖር የሞተ ነው ብሏል። ትናንትን መመለስ አይቻልም፤ ስለሆነም “ድሮ እንዲህ ነበርኩ” ማለት አሁን ያለህን ብቸኛ ሀብት ዛሬን በራስህ እጅ አሳልፈህ ለትናንት ሙት መንፈስ መገበር ማለት ነው።
የስነ ልቦና ጠቢቡ ፍሬድሪክ ኒቼ እንዲህ ብሏል፤ “ቆዳዋን መግፈፍ (መቀየር) ያቃታት እባብ መሞቷ አይቀርም። አስተሳሰቡንና ማንነቱን መቀየር የተሳነው አእምሮም እንደዚሁ ነው።” አንዳንዶች በአንድ የፖለቲካ አቋም፣ በአንድ እውቀት ወይም በአንድ ዕይታ ላይ ለዘላለም ተቀርቅረው ይቀራሉ። ራስን ማሸነፍ ማለት የትናንትን “እኔነት” እያፈረሱ አዲስ “እኔነትን” መገንባት ነው። ማደግ ማለት የዱሮ ማንነትህን እየገደልክ መሄድ ማለት ነው! ይላል።
የስነ ልቦና ተንታኙ ካርል ዩንግ ይህን የሰው ልጅ አባዜ ሲተነትነው “ፐርሶና” (Persona) ወደሚለው ጽንሰ-ሐሳብ ይወስደናል። ፐርሶና ማህበረሰቡ የሚያጠልቅልን ጭምብል ነው (ዶክተር፣ ሚኒስትር፣ ማናጀር፣ መሐንዲስ በሚል ስም ልንጠራ እንችላለን)። ትልቁ አደጋ የሚመጣው ሰዎች ይህንን ጭምብላቸውን ከእውነተኛ ማንነታቸው ጋር አንድ አድርገው ሲሰፉት ነው ብሏል። ስልጣኑ ሲያልቅ፣ ወንበሩ ሲወሰድ፣ ወይም ጡረታ ሲወጡ፣ ማንነታቸው አብሮ የተገፈፈ ይመስላቸዋል። “እኔ እኮ…” እያሉ የሚያለቅሱት ከጭምብሉ ጀርባ ያለውን ባዶነት (ባዶ ፊታቸውን) መቋቋም ስለሚያቅታቸው ነው።
በአርተን ሾፐንሀወር ዕይታ የዓለም መሠረቶች ምኞትና ፍላጎት ነው። ትናንት በነበረን ነገር ላይ ፍላጎታችንን አጣብቀን ስንተው ለውጡ ሲመጣ ወደ ጥልቅ ስቃይ ውስጥ እንገባለን። “ዱሮ እኮ” የሚለው ቃል የሚመነጨው ዓለም ተለዋዋጭ መሆኗን ካለመቀበል ግትርነት ነው። እነዚህ ሰዎች ከስቃይ (ትናንትን በማጣት) እና ከባዶነት (ዛሬን ከመጥላት) መሃል በሚወዛወዝ ፔንዱለም ላይ የታሰሩ ናቸው።
አእምሯችን በሚያስገርም ሁኔታ ራሱን የማደስና አዳዲስ የነርቭ መስመሮችን የመፍጠር እምቅ አቅም አለው፤ ይህም “ኒውሮፕላስቲሲቲ” ይባላል። ሆኖም አንድ ሰው ለአስር እና ሃያ ዓመታት “እኔ አለቃ ነኝ”፣ “እኔ አዋቂ ነኝ” ሲል ወይም በአንድ ዓይነት ርዕዮተ-ዓለም ውስጥ ብቻ ሲታሰር በአእምሮው ውስጥ ያሉት የነርቭ መስመሮች ልክ እንደ በረሀ ይደርቃሉ።
አዲስ ነገር ለመቀበል፣ ከዘመኑ ጋር ለመራመድ ሲሞክሩ አእምሯቸው ከፍተኛ ኃይል ይፈልጋል። ይህን ድካም ለመሸሽ፣ አንጎላቸው ወደለመደውና “ዱሮ” ወደሚለው ምቹ ቀጣና ይመለሳል። ሳይንስ ይህንን “የአእምሮ ግትርነት” ይለዋል። እነዚህ ሰዎች አካላቸው በአዲስ ዘመን ቢኖርም፣ አእምሯቸው ግን አርጅቶ ሞቷል።
ቻርልስ ዳርዊን ስለ ህይወት ህልውና የተናገረው ወርቃማ ህግ አለ “ከዘመናት ለውጥ ተርፈው የሚቀጥሉት በጣም ጠንካሮቹ ወይም በጣም ብልሆቹ ዝርያዎች ሳይሆኑ ለለውጥ ራሳቸውን በፍጥነት ማላመድ የቻሉት ናቸው” ብሏል።
ተፈጥሮ ርህራሄ አታውቅም። ቴክኖሎጂ ሲቀየር፣ የማህበረሰብ ዕይታ ሲቀየር፣ የዓለም ፖለቲካ ሲለወጥ “እኔ ድሮ እንዲህ ነበርኩ” እያለ የሚያላዝን ሰው ይጠፋል። የዝግመተ-ለውጥ ህግ አንድ ነው። “ከአካባቢህ ጋር ተላመድ፣ ራስህን ቀይር፣ አዲስ ክህሎት ተማር… ካልሆነ ግን ከመድረኩ ጥፋ!” የሚል።
“ዱሮ እኮ” ማለትን ማብዛት የአንድን ሰው የትናንት ታላቅነት ሳይሆን የዛሬን ባዶነት፣ ፍርሀት እና የበታችነት ስሜት የሚያጋልጥ የራስ ላይ ክስ ነው። ትናንትናን እንደ ትምህርት ቤት ልንጠቀምበት እንጂ እንደ መኖሪያ ቤት ልንሰፍርበት አይገባም።
ሕይወት ልክ ብስክሌት እንደመንዳት ናት። ሚዛንህን ጠብቀህ ለመቆየት፣ ፔዳሉን ወደ ፊት መርገጥ ግዴታህ ነው። ፔዳሉን መምታት ስናቆም እንወድቃለን። ለማያቋርጠው የዓለም ለውጥ የምንሰጠው ትልቁ ምላሽ ሁልጊዜም እንደ አዲስ ተማሪ ራሳችንን ባዶ አድርገን ለመማር ዝግጁ መሆን ነው። ትላንት ትምህርት ቤት ነው እንጂ መኖሪያ ቤት አይደለም!
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


