“ጣና የአገር አድባር የሁላችን ግርማ፣
ቆየን ሰነበትን ህመሙን ስንሰማ!
ቢዋኙበት ምቹ ቢያጠምዱበት ቸር ነው፣
አይተን እንዳላየን ዝምታው ምንድን ነው?
ዓባይን በሆዱ ችሎ ያሳለፈው፣
ዛሬ ቀን ከፍቶበት አረም አሸነፈው!” በማለት ታዋቂው ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ጣና ሐይቅ ስለተደቀነበት አደጋ ከአምስት ዓመት በፊት አንጎራጉሮ ነበር። ድምጻዊው ሐይቁ በተጋረጠበት አደጋ እንዳናጣው እና በውስጡ የሚገኙ ብዝኃ ሕይወት እንዳይጠፉ ተከታታይ ሥራዎች ማከናወን እንደሚገባም በሙዚቃው መልዕክት አስተላልፏል።
ጣና ሐይቅ ʽከታመመʽ 14 ዓመታት ተቆጥረዋል። ዋና ህመሙ ደግሞ እንቦጭ የተባለው መጤ አረም ነው።
ጣና በኢትዮጵያ ከሚገኙ የውኃ አካላት በስፋት ትልቁ ሐይቅ እንደሆነ እና በውስጡ የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎችን በመያዙ የብዙዎች መተዳደሪያ እንደሆነም የዘርፉ ተመራማሪ እሸቴ ደጀን (ዶ/ር) የጣና ሐይቅ ዓሳ ሀብት እና ዘላቂ ልማት በሚል መጽሐፋቸው ላይ አስነብበዋል። ሐይቁ ለዓሳ እርባታ፣ ለመስኖ ልማት፣ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኀይል ለሚያመነጨዉ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ መሰረት፣ ለመጓጓዣ (ትራንስፖርት)፣ ለመዝናኛ፣ ለቱሪዝም፣ ነፋሻማ አየር እንዲኖር… አበርክቶው የጎላ ነው። በባሕር ዳር ከተማ እና በጣና ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎች ሕልውና የተመሰረተውም በጣና ሐይቅ ላይ መሆኑ አያጠያይቅም። በሐይቁ ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮች ውኃውን በመጠቀም አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች የሰብል አይነቶችን በመስኖ ያለማሉ። ምንም እንኳን ጣና ሐይቅ ይህን ሁሉ ጥቅም የሚሰጥ ቢሆንም አሁንም ድረስ ህልውናውን ሊያጠፋው ከወረረው አረም መታደግ አልተቻለም።
ከአማራ ክልል አልፎ ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ አበርክቶው ከፍተኛ የሆነው ጣና ሐይቅ ከእንቦጭ በተጨማሪ በባሕር ዳር ከተማ እና በዙሪያዋ ወደ ሐይቁ የሚለቀቁ ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻዎች፣ ኬሚካሎች፣ በሐይቁ ዳርቻ የሚጣሉ የፕላስቲክ የውኃ መያዣዎች እና መሰል ቆሻሻዎች ለሐይቁ መበከል ተጨማሪ ፈተናዎች እና ተደራራቢ ችግሮች ናቸው::
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት በክረምት ዝናብ የሚታጠበው ለም አፈር (ደለል) በቀጥታ ወደ ጣና ሐይቅ በመግባቱ ለአረሙ መስፋፋት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። ስለሆነም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የእርከን ሥራ፣ ችግኝ መትከል እንዲሁም ልቅ ግጦሽን መከላከልን በዘላቂነት መሥራት እንደሚገባም የዘርፉ ባለሙያዎች ምክረ ሐሳባቸውን እያጋሩ ነው።
የእንቦጭ አረም ለመጀመሪያ ጊዜ በሐይቁ መከሰቱ ከተረጋገጠበት 2004 ዓ.ም ጀምሮ የሐይቁን ህልውና ለመታደግ አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ እያለም ቢሆን ጥረቶች ተደርገዋል፤ ዳሩ ግን እንቦጭን በማስወገድ ጣና ሐይቅን ከገጠመው ፈተና በዘላቂነት ማላቀቅ አልተቻለም። ስለሆነም ሥነ ምህዳራዊ ችግሮችን ከመፍታት ጀምሮ የሐይቁን ሁለንተናዊ ደህንነቱን ለማረጋገጥ አዲስ የንቅናቄ ዘመቻ በባሕር ዳር ከተማ ሽንብጥ ክፍለ ከተማ ባለው የጣና ዳርቻ ከሰሞኑ በይፋ ተጀምሯል።
በሐይቁ ላይ እየተስፋፋ የመጣውን የእንቦጭ አረም ማስወገድ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ የአማራ ክልል አካባቢ እና ደን ጥበቃ ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ ተስፋሁን ዓለምነህ እንደተናገሩት ጣና ሐይቅ ለአካባቢው ማኅበረሰብም ሆነ ለሀገር ያለው ምጣኔ ሀብታዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ፋይዳ ላቅ ያለ ነው። በሐይቁ ላይ እየተስፋፋ የመጣውን የእንቦጭ አረም በተባበረ ክንድ በማስወገድ የሐይቁን ህልውና መጠበቅ ይገባል።
ባለፉት ዓመታት የተከሰተው የእንቦጭ አረም በሐይቁ ሥነ ምህዳር እና ሕልውና ላይ ከፍተኛ ስጋት ደቅኖ መቆየቱንም አስታውሰዋል። ይህንን ስጋት ለመቅረፍም መንግሥት በበጀት ዓመቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል። በነበረው የጸጥታ ችግር በአንዳንድ የሐይቁ ዳርቻዎች ተገቶ የነበረው የመከላከል ሥራ በአሁኑ ወቅት አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ ሥራውን አጠናክሮ ለመቀጠል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።
በሰው ኀይል እና በማሽን የታገዘውን የአረም ማስወገድ ሥራ ከማጠናከር ባለፈ የሕዝቡን ጠንካራ ተሳትፎ ማዕከል ያደረገ ሥራ እንደሚጠይቅም ኃላፊው አስገንዝበዋል:: የእንቦጭ አረም በቀላሉ የመስፋፋት እና የማንሰራራት ባሕሪ ያለው በመሆኑ ቀጣይነት ያለው ዘመቻ እና የክትትል ሥራ እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥተዋል። የጣና ሐይቅን ደኅንነት ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል::
በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የተስፋፊ አረም ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ጋሻው መሳፍንት ለበኵር እንደተናገሩት የጣና ሐይቅ ላለፉት ዓመታት “እንቦጭ” በተሰኘ አደገኛ አረም ህልውናው ክፉኛ እየተፈተነ ይገኛል። ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ በሐይቁ ላይ መታየት የጀመረው ይህ አረም በወቅቱ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራው እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ አሁን ላይ አረሙ ሐይቁን የመውረር አድማሱን እያሰፋ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። በጣና ሐይቅ ዙሪያ በ30 ቀበሌዎች ላይ የእንቦጭ አረም መከሰቱንም ነው ያስታወቁት።
በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ዙሪያ ብቻ 148 ሄክታር የሚጠጋ መሬት በአረሙ የተሸፈነ መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይም በጣና ሐይቅ ውስጥ የሚገኙ እንደ ቀረሶ፣ ላብዮ ባርባስ እና አምባዛ በተባሉ የዓሳ ዝርያ መራቢያ ስፍራዎች በአረሙ በመወረራቸው የዓሳ ሀብቱ አደጋ ላይ ወድቋል ነው ያሉት።
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ከዚህ በፊት የጣና ሐይቅ እና ሌሎች የውኃማ አካላት ጥበቃ እና ልማት ኤጀንሲ በባለቤትነት ይዞ አረሙን ለማስወገድ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል:: አሁን ላይ ደግሞ የጣናን ህልውና ለመታደግ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በባለቤትነት ይዞ የተስፋፊ እና መጤ አረም ክትትል እና ቁጥጥር ዳይሬክተር አዋቅሮ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል። እንቦጭን ማጥፋት እጅግ ፈታኝ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ የአረሙ የተፈጥሮ ባህሪ እንደሆነም ባለሙያው ጠቁመዋል።
አቶ ጋሻው እንደገለፁት የእንቦጭ ዘር እስከ 30 ዓመት ድረስ ራሱን ደብቆ በውኃ ውስጥ የመቆየት አቅም አለው። ምቹ ሁኔታ ሲያገኝ ደግሞ ወዲያውኑ መልሶ ያቆጠቁጣል። አረሙን አንድ ጊዜ ነቅሎ በማውጣት ብቻ ማጥፋትም አይቻል:: አንዲት የእምቦጭ ዛላ ብቻዋን እስከ አምስት ሺህ ዘር የማፍራት አቅም አላት። በመሆኑም ሥራው ያልተቋረጠ እና ቀጣይነት ያለው የክትትል ሥራን ይጠይቃል።
ይህንንም ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በኩል ችግሩን ለመፍታት ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው። የመከላከል ሥራው በሰው ኀይል እና በማሽነሪ በመታገዝ እንዲሁም ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር አረሙን በባዮሎጂካል መንገድ (በስነ ህይወታዊ) ለመቆጣጠር የሚያስችል የምርምር ሥራ በሙከራ ደረጃ ተጀምሯል። ይህ ሥራም ተጠናክሮ ይቀጥላል::
የጣና ሐይቅ ጉዳይ የአንድ ተቋም ወይም የመንግሥት ብቻ ኃላፊነት አደለም ያሉት ባለሙያው ሐይቁ የታላላቅ ጥንታዊ ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት መገኛ እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ የዕለት ተዕለት የኑሮ መሰረት ነው። ስለሆነም በሐይቁ ዙሪያ ያሉ ሆቴሎች በቅርበታቸው ያለውን የሐይቁን አካል መንከባከብ፣ ማፅዳት እና መጠበቅ፣ የእምነት ተቋማት (ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት) ምዕመኑን በማስተባበር መጠበቅ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪክ ማህበራት እና አጠቃላይ ህብረተሰቡ በጉልበትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል።
በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው የአረም ማስወገድ መርሀ ግብር ሲሳተፉ ካገኘናቸው መካከል አዕምሮ አበጀን እና ዘመኑ መኬ አነጋግረናቸው ነበር:: ዓባይ ወንዝ እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያለ ጣና ሐይቅ ህልውናቸው አደጋ ላይ ይወድቃል የሚል ሥጋት እንዳደረበት ዘመኑ መኬ ተናግሯል:: በሐይቁ ውስጥ የሚገኙ ገዳማት እና በውስጣቸው የሚገኙ ቅርሶች ያለ ጣና ሐይቅ ምንም እንዳልሆኑም ወጣቱ ጠቁሟል::
አዕምሮ አበጀ በበኩሉ “ከዚህ በፊት ጣና በእንቦጭ አረም መወረሩን በወሬ እሰማ ነበር፤ ነገር ግን ጣና ሐይቅ በዚህ ልክ ይወረራል የሚል እምነት አልነበረኝም። በኔ እምነት የእንቦጭ አረም ማስወገድ ሥራ የአንድ ቢሮ ወይም የአንድ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ ብቻ ነው ተብሎ በዝምታ እና በቸልታ ሊታይ አይገባም። ስለሆነም የጣና ሐይቅን ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግ በጉልበት፣ በዕውቀት እና በገንዘብ ተረባርቦ የሀገር ሀብት የሆነውን ልናድነው ይገባል። ጣና ሐይቅ እንጀራም፣ ውበትም፣ ኩራትም፣ እስትንፋስም፣ ታሪክም ነው:: ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከዚህ በፊት ያደርጉት የነበረውን ርብርብ መቀጠል ይገባቸዋል” በማለት በቁጭት አስተያየቱን ሰጥቷል::
አረሙ በባሕር ዳር ከተማ ዙሪያ በሚገኝ የሐይቁ ዳርቻ ሳይቀር ተስፋፍቶ ተመልክተናል። በቀጣይ ተቀዛቅዞ የቆየው የእንቦጭ አረም ነቀላ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አጋር እና ባለድርሻ አካላትም በቅንጅት መሥራት ይጠበቅባቸዋል። የጣና ሐይቅ ህመም ያመናል እና ይህን የተፈጥሮ ጸጋ መጠበቅ እና መንከባከብ የመንግሥት፣ የአካባቢው ማህበረሰብ እና የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።
መረጃ
የተፈጥሮ ሀብት ከመሬት በታችም ይሁን ከመሬት በላይ በተፈጥሮ የሚገኝ ሀብት ነው። ይህ ሀብት ሕይወት ያላቸውንም ይሁን የሌላቸውን ያጠቃልላል። እነዚህ ሀብቶችም እፅዋት፣ ሐይቆች፣ የዱር እንስሳት፣ ወንዞች፣ ተራሮች፣ አየር፣ መሬት፣ ማዕድናት፣ ነዳጅ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


