ትኩረት የሚሻው የግብርና ኢንቨስትመንት

0
163

በአማራ ክልል በ1980ዎቹ አጋማሽ የተጀመረው የግብርና ኢንቨስትመንት በአሁኑ ወቅት በ14 ዞኖች እና በ76 ወረዳዎች እየተከናወነ ይገኛል:: የግብርና ኢንቨስትመንት የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ በማምረት፣  ምርታማነትን በማሳደግ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለማኑፋክቸሪንግ ግብዓት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገርም  የሚመለከታቸው አካላት በባሕር ዳር ከተማ ሰሞኑን ውይይት አድርገዋል፡፡

በግብርና ኢንቨስትመንት  ከተሰማሩት መካከል  ወ/ሮ ክብረቴ ዓለማየሁ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የተሰማሩት ግንባር ቀደም (ሞዴል) ባለሀብት ወ/ሮ ክብረቴ ሥራውን ሲጀምሩ አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት እንደሆነ ያስረዳሉ::

የግብርና ኢንቨስትመንት በግብርናው ዘርፍ ላይ ገንዘብን፣ ዕውቀትን፣ ቴክኖሎጂን እና ጉልበትን ጥቅም ላይ በማዋል ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ  እንቅስቃሴ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ወ/ሮ ክብረቴ በቆሎ፣ በርበሬ እና መሰል ሰብሎችን በማምረት ትርፋማ መሆናቸውንም አስረድተዋል:: ለስኬታቸው ምስጢር ደግሞ የተማረ የሰው ኀይል ቀጥረው ማሠራታቸው፣ በጥሩ ሁኔታ ማስተዳደር መቻላቸው እና ሠራተኞቻቸውን በፍቅር እና በአግባቡ መያዝ መቻላቸው መሆኑን በአብነት አንስተዋል::

ባለሀብቷ አርሶ አደሩን ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ እርሻ በማሸጋገር ረገድ ባለሀብቱ ድርሻ ሊኖረው እንደሚገባ ያምናሉ:: የአካባቢው አርሶ አደር በትራክተር እንዲያርስ፣ የተፈጥሮ ጥበቃን እንዲያዳብር በማስተማር እና የግብዓት አጠቃቀምን በማሳየት ትልቅ ኃላፊነት እየተወጡ መሆኑንም ገልጸዋል::

የመሰረተ ልማት እና የግብዓት አቅርቦት እንዲሁም የደላሎች ጣልቃ ገብነት በሥራቸው ላይ እንቅፋት መሆናቸውን ጠቁመዋል:: በዚህም የተመረተውን ምርት በወቅቱ እና በፍጥነት አጓጉዞ ለገበያ ለማቅረብ መንገድ መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ መንግሥት ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበትም ጠይቀዋል::

እነዚህን ችግሮች ለሚመለከተው አካል በማሳወቃቸው ባለፉት ሁለት ዓመት በተለይም በግብዓት አቅርቦት (የአፈር ማዳበሪያ) የተሻለ ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል:: ግብርናው  በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ፣ በምርምር እና በጥናት ተደግፎ እንዲለማ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም ባለሀብቷ አስገንዝበዋል፡፡

የአማራ ክልል የግብርና ኢንቨስትመንት ማኅበር ኘሬዝዳንት አቶ መስፍን ክፍሉ በበኩላቸው በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ77 ሄክታር መሬት ላይ አትክልት እና ፍራፍሬ እያለሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል:: ዘርፉ ምርታማነትን በቀላሉ ከማሳደግ ባለፈ የኑሮ ደረጃን ማሻሻል እንደተቻለ  ገልጸዋል:: ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ እንደ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ሽንኩርት እና የቲማቲም ምርቶችን በስፋት እያመረቱ ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ነው ያስረዱት::

በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት፣ የበጀት እና የግብዓት እጥረት  መሠረታዊ ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል:: ውይይቱ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ ሚና እንዳለው እምነታቸው ነው፡፡  በተለይም አበዳሪ ተቋማት በውይይት መድረኩ መገኘታቸው ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አመላክተዋል::

የገንዘብ እጥረት ለዘርፉ ትልቅ እንቅፋት እንደሆነባቸው  ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም  ለግብርና ኢንቨስትመንት የሚሆን የፋይናንስ ተቋም (የግብርና ባንክ) በክልል ደረጃ እንዲቋቋም ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን በፌዴራል ደረጃ በነበረው ውይይት መነሳቱን አስታውሰዋል:: ይህ ዕቅድ ተግባራዊ ሲደረግ እያንዳንዱ የግብርና ባለሀብት በቂ እና ተመጣጣኝ የሆነ ብድር፣ በተፈለገው ጊዜ፣ በአነስተኛ የወለድ መጠን ለማቅረብ እንደሚያግዝ ተስፋ ተጥሎበታል ብለዋል::

በመድረኩ ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው አካላት ተሳትፈዋል:: ከእነዚህም መካከል ከፀደይ ባንክ  የመጡት አቶ ሙጨ ያለው እንደተናገሩት ተቋሙ  ምርታማነትን ለማሳደግ ለአልሚ ባለሀብቶች እና ለአርሶ አደሮች  የመሬት ማረጋገጫ ደብተር በማስያዝ የብድር ተጠቃሚ እየሆኑ ነው:: ብድር የመመለስ ችግርንም በጋራ ለመፍታት እና ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል::

ፀደይ ባንክ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ሙሉ ባንክነት ካደገ በኋላ በግብርና እና በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተርን በማስያዝ የብድር አገልግሎት እየሰጠ ነው፡፡ በዚህም  500 ባለሀብቶችን እና 20 ሺህ አርሶ አደሮችን የብድር ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል::

ይሁን እንጂ ባንኩ ያሰራጨውን ከፍተኛ የብድር መጠን ለመሰብሰብ ችግር እንደገጠመው  አስታውቋል::  በተለይም ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ብድር የወሰዱ በርካታ ባለሀብቶች በፀትታው ምክንያት  “ምርት አላገኘንም” በሚሉና በሌሎች በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ብድራቸውን አልመለሱም::

አቶ ሙጨ እንዳሉት የብድር አከፋፈል ባህሉ እጅግ ደካማ በመሆኑ እና ተበዳሪዎችም ሆን ብለው ገንዘቡን ከመመለስ ወደ ኋላ በማለታቸው እንደሆነ አብራርተዋል:: ይህንን አሠራር ለማስተካከል እና የሕዝብን ሀብት ለማስመለስ ባንኩ በቀጣይ ከመሬት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ለመሥራት ማቀዱን አብራርተዋል::

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እብሬ ከበደ እንደገለጹት በዘርፉ የሚታየውን የፋይናንስ አቅርቦት እና የመሬት አጠቃቀም ችግር ለመፍታት ሁሉም አካል የራሱን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል::

በውይይት መድረኩ ላይ ባለሀብቶቹ የገንዘብ (የፋይናንስ) አቅርቦት እጥረት ዋና ማነቆ እንደሆነባቸው ያነሱ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ አበዳሪ ተቋማት የተሰጠው ብድር በአግባቡ እየተመለሰ አለመሆኑን አቅርበዋል:: ከዚህም ባለፈ አቶ እብሬ እንዳብራሩት አንዳንዶቹ ባለሀብቶች የወሰዱትን ብድር ለታለመለት ዓላማ አለማዋል እንዲሁም ለባንክ መያዣ ያስያዙትን መሬት ከመሬት ቢሮ እውቅና ውጭ ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው የመስጠት ሕገ-ወጥ አሠራሮች ይስተዋላሉ::

በሌላ በኩል ባንኮችም መሬቱን ለጨረታ ሲያቀርቡ ሕጋዊ አሠራርን ተከትለው ከመሬት ቢሮ ጋር አለመቀናጀታቸው ሌላው የችግሩ አካል መሆኑ ተነስቷል:: ለግብርና ኢንቨስትመንቱ በቂ የብድር አቅርቦት ቀርቧል ማለት አያስደፍርም ያሉት አቶ እብሬ ጥረቶች ግን እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል:: ከሀገር ውስጥ አልፎ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለማምረት ሙያዊ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ያስረዱት አቶ እብሬ በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል::

“የግብርና ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቅ በመሆኑ የባንኮች ድጋፍ ወሳኝ ነው፤ ነገር ግን የሚታዩት ችግሮች የሁሉም በመሆናቸው መፍትሔውም የጋራ መሆን አለበት” ያሉት አቶ እብሬ እያንዳንዱ አካል ጣቱን ወደ ሌላው ከመቀሰር ይልቅ የራሱን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል:: በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅንጅት በመፍታት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እና ለውጭ ገበያ የሚውሉ ምርቶችን ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል::

ባለፉት ጊዚያት በተለያዩ ቦታዎች ከተለያዩ አካላት ጋር በዘርፉ ተመሳሳይ  ምክክር መደረጉን አስታውሰዋል:: በቀጣይም ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ባሕር ዳር፣ ጎንደር እና ኮምቦልቻን ጨምሮ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ተከታታይ የውይይት መድረኮች ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር እንደሚካሄድ አቶ እብሬ ገልጸዋል::

በአማራ ክልል የግብርና ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተካሄደው ውይይት ማብራሪያ የሰጡት የአማራ ክልል መሬት ቢሮ የግብርና ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ በላይ በክልሉ በአሁኑ ወቅት  ከአንድ ሺህ 635 በላይ ባለሀብቶች በዘርፉ ተሰማርተዋል፡፡ ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትም እየለማ እንደሚገኝ አስረድተዋል::

በውይይቱ የግብርና ኢንቨስትመንትን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የመንግሥት ጠንካራ ድጋፍ እና ቁጥጥር እንዲሁም የባለሀብቶች ሕግን ያከበረና ዘመናዊ አሠራር ወሳኝ መሆኑን የሚያሳይ ነው:: ሞዴል ባለሀብቶችን በማበረታታት እና ሕገ-ወጦችን ሥርዓት በማስያዝ የዘርፉን ዕድገት ማፋጠንም እንደሚቻል አመላክተዋል::

መሬትን በተሰጠው ውል እና ግዴታ መሰረት አለማልማት፣ በተማረ የሰው ኀይል (ባለሙያ) እና በሰለጠነ መንገድ አለመመራት፣ ሕግ አለማክበር፣ ውል በወሰደበት አግባብ የተፈጥሮ ሀብትን አለመንከባከብ፣ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂን እና የግብርና ግብዓቶችን በስፋት እና በአግባቡ አለመጠቀም፣ መሬትን ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ መስጠት (ማከራየት)፣ ብድርን በወቅቱ አለመክፈል በባለሀብቶች በኩል የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች እንደሆኑ አቶ ጥጋቡ ዘርዝረዋል:: በአንጻሩ ለአካባቢው አርሶ አደር የምርጥ ዘር እና የትራክተር ድጋፍ የሚያደርጉ፣ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ እና ቴክኖሎጂ የሚያሸጋግሩ እጅግ አርአያ የሆኑ ባለሀብቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል::

ስለሆነም የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የባለሀብቶችን አፈጻጸም ይገመግማል:: የተሰጣቸውን መሬት በማያለሙ እና አፈጻጸማቸው ደካማ በሆኑ ባለሀብቶች ላይ የማስጠንቀቂያ እና መሬት የመንጠቅ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ነው ያስታወቁት:: አፈጻጸማቸው ከ50 በመቶ በታች ለሆኑት በዝርዝር ችግራቸው (ጉድለቶች) ተጠቅሶ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል:: ካላስተካከሉ መሬቱ ተነጥቆ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ይደረጋል:: ይህም ለሌሎች አልሚ ባለሀብቶች እንደሚተላለፍ ነው የገለጹት:: በመንግሥት በኩል ያሉ ክፍተቶች ደግሞ የመሰረተ ልማት (መንገድ፣ መብራት፣ ውኃ) አለመሟላት፣ የገበያ ትስስር አለመፈጠር፣ የግብዓት እና የብድር አቅርቦት ማነስ፣ በጸጥታ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸዉን ተበዳሪዎች ልዩ ድጋፍ አለማድረግ  እንዲሁም ጠንካራ የክትትል  እና ድጋፍ ሥርዓት አለመኖር ናቸው:: ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ ነው:: ባለሀብቱ የወሰደውን መሬት በውሉ እና በሕጉ መሠረት ማልማት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል::

የኢንቨስትመንትን ዓላማ ተረድቶ ድጋፍ እና ክትትል አለማድረግ፣ ለባለሀብቱ በቅንነት፣ በታማኝነት፣ በታታሪነት እና በቅልጥፍና አገልግሎት የመስጠት ውስንነት መኖር፣ ሥራው የሚጠይቀውን ዕውቀት እና ክህሎት ተላብሶ አገልግሎት አለመስጠት፣ የአቅም እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውስንነት፣ የኢንቨስትመንትን መረጃ በጥራት አደራጅቶ አለመያዝ በባለሙያው የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው:: ቢሮው እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠራ መሆኑን አስታዉቋል፡፡

በሌላ በኩል ወደ ግብርና ኢንቨስትመንት ለሚገቡ አዳዲስ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑ ተገልጿል፡፡ አሁን ላይ ወደ 20 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ተዘጋጅቶ ባለሀብቶችን እየጠበቀ ይገኛል:: በተጨማሪም በምዕራብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ አዊ፣ ምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም ዞኖች ለግብርና ኢንቨስትመንት የሚውል ከ175 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተለይቷል፡፡ ይህን መሬት ለባለሀብቶች ለማስተላለፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በመግለጽ ነዉ ምክትል ቢሮ ኃላፊዉ ያደማደሙት፡፡

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሚያዚያ 5  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here