ሀገራት የነዳጅ እጥረቱን እንዴት እየተቋቋሙት ነው?

0
127

ከመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት በኋላ የዓለም የነዳጅ አቅርቦት ችግር ውስጥ ገብቷል:: የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል በመጋቢት ወር ብቻ በከፍተኛ መጠን ከፍ ብሎ ታይቷል:: ዋጋውም  ከግጭቱ በፊት ከነበረበት 80 ዶላር  ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ወደ 120 ዶላር ደርሷል::

ችግሩን ለመቋቋም ታዲያ ሀገራት የሚወስዱት መፍትሔ አንድ አይነት አይደለም፤ ነገር ግን በአብዛኛው መፍትሔዎቻቸው በአራት ትልቅ መሠረቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው:: እነሱም አስቸኳይ የነዳጅ ክምችትን መልቀቅ፣ የነዳጅ ፍጆታን መቀነስ፣ አማራጭ አቅርቦትን መፈለግ እና የዋጋ ጫናን በመንግሥት መቆጣጠር ናቸው::

ብዙ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ ሀገራት የመጀመሪያ ርምጃ ቀደም ሲል ያከማቹትን ነዳጅ ወደ ገበያ ማስገባት ሆኗል:: ይህን የሚያደርጉትም በእጥረቱ ምክንያት ዋጋ እንዳይጨምር እና የገበያ መዋዥቅ እንዳይበረታ ለመከላከል ነው::

የዓለም አቀፉ የኢነርጂ ተቋም (International Energy Agency – IEA) እንዳስታወቀው የተቋሙ 32 አባል ሀገራት በመጋቢት 11 ቀን 2026 እ.አ.አ 400 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ከአስቸኳይ ክምችታቸው ለመልቀቅ ሙሉ ለሙሉ ተስማምተዋል፤ ይህም በዓለም አቀፉ የኀይል ተቋም ታሪክ እስካሁን ትልቁ የአስቸኳይ ርምጃ መሆኑ ተገልጿል:: በኋላም ይህ መጠን በአጠቃላይ 426 ሚሊዮን በርሜል እስኪደርስ አባል ሀገራት እንደሚያዋጡ ነው ያረጋገጡት:: አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና የአውሮፓ ሀገራት በዚህ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ይይዛሉ::

ይህ የሚያሳየው የነዳጅ እጥረት በሚከሰትበት ጊዜ በገበያ ላይ ብቻ መወሰን እንደማይቻል ነው:: መንግሥታት በቀጥታ ገብተው አቅርቦትን መደገፍ እንደሚጠበቅባቸውም ያመላክታል::

ሀገራት እየተገበሩት የሚገኘው ሁለተኛው ርምጃ ፍጆታን መቆጣጠር ነው፤ ብዙ ሀገራት የነዳጅ እጥረት ሲከሰት “ከየት እናምጣ?” ከሚለው በተጨማሪ “እንዴት እንቀንስ?” የሚለውን ጥያቄ ያነሳሉ፣ ምላሽም ይሰጡበታል::

የዓለም አቀፉ የኢነርጂ ተቋም እንደሚያብራራው አባል ሀገራት በአስቸኳይ ጊዜ የመደበኛ የነዳጅ ፍጆታቸውን እስከ 10 በመቶ ለጊዜው ለመቀነስ የሚያስችላቸውን የፍጆታ መቆጣጠሪያ ዕቅድ እንዲኖራቸው ተጠይቀዋል:: እነዚህ ርምጃዎች ከቀላል ወደ ጠንካራ መፍትሔዎች የሚያመሩ ሲሆን ሥራዎችን  በመኖሪያ ቤት  ውስጥ መሥራት  (telecommuting/work-from-home)፣ መኪና መጋራት (car-pooling)፣ የሕዝብ ትራንስፖርት መጠቀም፣ የፍጥነት ገደብን መቀነስ፣ ፍትሐዊ የነዳጅ ስርጭት (rationing) እና የግዢ መጠን ላይ ገደብ መጣል ናቸው::

አቅራቢ መፈለግ ደግሞ ሦስተኛው አማራጭ ነው፤ ሀገራት አንደኛው የአቅርቦት መስመር ሲቋረጥ በፍጥነት ሌላ መንገድ መፈለግ ግድ ይላቸዋል:: ይህ ዛሬ በእስያ እና በአፍሪካ በግልጽ እየታዬ ነው::

ሬውተርስ እንደዘገበው ኢንዶኔዢያ ከጃፓን ጋር  ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝን (LNG) በፈሳሽ ፔትሮሊየም ጋዝ (LPG) የሚተኩበት ሁኔታ ላይ እየተወያዩ ነው፤  ጃፓን ለፊሊፒንስ ዲዘል አቅርባለች፤ ደቡብ ኮሪያ ከሩሲያ ናፍታ አስመጥታለች፤ ሕንድ፣ ስሪላንካ፣ ታይላንድ እና ቬትናም አዳዲስ የክሩድ እና የተጣራ ነዳጅ አቅራቢዎችን በአስቸኳይ እያፈላለጉ ናቸው:: ይህ ሁኔታ የሚያሳየው የነዳጅ ገበያ በቁጥጥር ውስጥ ያለ የንግድ ገበያ ብቻ እንዳልሆነ ነው፤ በቀውስ ጊዜ የኀይል ግብይት ወደ ዲፕሎማሲ ልውውጥ ስምምነት እና ሀገራዊ ትብብር ይቀየራል::

አራተኛው  የዋጋ ጫናን ለመቆጣጠር ድጎማ እና ግብር ቅናሽ ማድረግ ነው፤ ብዙ መንግሥታት ሕዝቡ ወዲያውኑ እንዳይጨነቅ ግብር ይቀንሳሉ ወይም ድጎማ ያደርጋሉ:: ለአብነትም  አውስትራሊያ የነዳጅ ግብርን በግማሽ ቀንሳለች፤ አንዳንድ የመንገድ ክፍያዎችንም አንስታለች::

አውሮፓም ከሦስት ዓመት በፊት የኀይል ቀውስ አጋጥሟት በነበረበት ጊዜ የወሰደቻቸውን የመፍትሔ ርምጃዎች ድጋሚ ለመተግበር እያሰበች መሆኑን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል:: እነሱም የኤሌክትሪክ ግብር መቀነስ እና የጋዝ ዋጋ ገደብ የሚሉት ይገኙበታል::

ርምጃው አስቸኳይ መፍትሔ ቢሆንም ረጅም ጊዜ ይተግበር ቢባል ግን የበጀት ጫናን ያመጣል:: የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) መረጃ እንደሚጠቁመው የኀይል ድጎማ ከተራዘመ በመንግሥት ፋይናንስ ላይ ከባድ ጫናን ያመጣል፤ ስለዚህ በተመረጡ ሴክተሮች ላይ ብቻ የሚያተኩር ድጋፍ ይመከራል::

ሌሎች ሀገራትስ ምን መላ ዘየዱ?

ሀገራት በመካከለኛው ምሥራቅ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ለተነሳው ዓለም አቀፍ የነዳጅ እጥረት ምላሽ ለመስጠት እየተሯሯጡ ነው፤ በመላው እስያ ያሉ ሀገራት በኮቪድ – 19 ወረርሽኝ ወቅት የተገበሩትን የቤት ውስጥ ፖሊሲዎችን እና የማነቃቂያ ርምጃዎችን ለመተግበር እየመዘኑ ነው:: በተመሳሳይ ደቡብ ኮሪያ ሰዎች ከቤት እንዲሠሩ የቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብ በበጎ ተመልክታዋለች::

ቀውሱን ለመቋቋም 400 ሚሊዮን በርሜል የሚጠጋ ዘይት ከስልታዊ ክምችቶች ለመልቀቅ የተስማማው ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ተቋም፣ ከቤት ውስጥ መሥራት እና የአየር መጓጓዣ የመሳሰሉ የነዳጅ ዋጋ ጫናዎችን ለማቃለል የሚያስችሉ ሀሳቦችን አቅርቧል::

ለኀይል ፍላጎቷ በመካከለኛው ምሥራቅ ነዳጅ ዘይት ላይ የተመሠረተችው ፊሊፒንስ በተወሰኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ የሥራ ቀናትን ቀንሳለች::  ፕሬዝደንት ፈርዲናንድ ማርኮስ ግጭቱ በሀገሪቱ የኀይል አቅርቦት ላይ አደጋ እንደሚፈጥር በመግለጽ የብሔራዊ ኢነርጂ የአደጋ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል::

በተመሳሳይ ፓኪስታን ለሁለት ሳምንታት ትምህርት ቤቶችን ዘግታለች፤ የቢሮ ሠራተኞች አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ወስናለች:: የሲሪላንካ ደሴት የነዳጅ አቅርቦቷን የበለጠ ለማገዝ በየሳምንቱ ረቡዕ ሕዝባዊ በዓል አውጃለች::

የእስያ የፋይናንስ ማዕከል የሆነችው ሲንጋፖር ሰዎች እና የንግድ ድርጅቶች ንብረቶቻቸውን ወደ ኀይል ቆጣቢ ዕቃዎች እንዲቀይሩ እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እንዲጠቀሙ አሳስባለች:: የታይላንድ ጠቅላይ ሚኒሥትር አኑቲን ቻርንቪራኩል የአየር ማቀዝቀዣ የሙቀት መጠን ከ25 ዲግሪ ሴልሺየስ (77 ዲግሪ ፋራናይት) በላይ እንዳይጠቀሙ፣ በአሳንሰር ፋንታ ደረጃዎችን እንዲጠቀሙ እና ከቤት እንዲሠሩ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል::

እየጨመረ የሚሄደው የነዳጅ ወጪ በቤተሰብ በጀት ውስጥ ስለሚገባ አንዳንድ ሀገራት  የማነቃቂያ ርምጃዎችን እወሰዱ ነው:: የጃፓን መንግሥት ከሰሞኑ እንዳስታወቀው የነዳጅ ዋጋን በአማካይ በሊትር 170 የን ላይ ለማቆየት ለሚደረገው ድጎማ 800 ቢሊዮን የን (5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ) የመጠባበቂያ ገንዘብ ለማግኘት አቅዷል:: ልኬቱ በወር እስከ 300 ቢሊዮን የን ወጪ ያስወጣል:: ኒውዚላንድ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰቦች በየሳምንቱ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ የ29 ነጥብ 3 ዶላር ጊዜያዊ የገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች::

የነዳጅ እጥረቱ ዓለምን ክፉኛ እየፈተናት በሚገኝበት በዚህ ወቅት አፍሪካ ያለባት እጥረት ከዋጋ በላይ ነው:: አፍሪካ ለዚህ ቀውስ በልዩ ሁኔታ ተጋላጭ ናት:: ምክንያቱም ብዙ የአህጉሪቱ ሀገራት የነዳጅ ምርት ያላቸው ቢሆንም የማጣሪያ አቅማቸው ዝቅተኛ ስለሆነ የተጣራ ነዳጅን ከውጭ ማስገባት ይጠበቅባቸዋል:: ይህም እጥረት ሲመጣ በዓለም ገበያ የከፋ ተጎጂ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል::

ሬውተርስ የአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራትን ርምጃዎች በዘገባው አመላክቷል፤ ለአብነትም ሞሪሸስ ኀይል ቆጣቢ ናቸው ያለቻቸውን ርምጃዎች አስታውቃለች፤ ደቡብ ሱዳን በአቅርቦት ፍትሐዊ የነዳጅ ዘይት ክፍፍል ለመተግበር እየሞከረች ነው:: ይህ ለአፍሪካ አንድ ግልጽ ትምህርት አለው፤ የነዳጅ ሀብት መኖር ብቻ የኀይል ደኅንነትን አያረጋግጥም:: የማጣሪያ አቅም፣ የክምችት አወቃቀር እና የስርጭት መሠረተ ልማት ካልተጠናከረ ሀብት ራሱ መፍትሔ አይሆንም::

የኢትዮጵያ መንግሥትም በነዳጅ አቅርቦት ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመቋቋም የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ይፋ አድርጓል:: በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ጦርነት በኢትዮጵያ የነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ነው የሀገሪቱ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒሥትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) የተናገሩት:: ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር የነበራት የረጅም ጊዜ የነዳጅ ግብይት ውል በጦርነቱ ምክንያት በመስተጓጎሉ አቅራቢ ሀገራቱ ምርቱን ማቅረብ አልቻሉም:: በዚህም ምክንያት በግዥ ሂደት ላይ የነበረ ከ180 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ነዳጅ መቅረብ አልቻለም::

ሚኒሥትሩ እንዳስታወቁት በጦርነቱ ምክንያትም በነጭ ናፍታ ላይ የነበረው የቀን አቅርቦት ከዘጠኝ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሊትር ወደ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሊትር ዝቅ ብሏል:: ይሁንና መንግሥት የዜጎችን ኑሮ ለመታደግ በአሁኑ ወቅት በነጭ ናፍጣ ላይ በአንድ ሊትር 95 ብር በቤንዚን ላይ ደግሞ 42 ብር ድጎማ እያደረገ ይገኛል::

ይህን ችግር ለመቋቋምም  የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭትን የሚከታተል፣ ርምጃ የሚወስድና ነዳጅ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች የሚለይ ልዩ ክፍል ተቋቁሟል:: በዚህም መሠረት ነዳጅ የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች በማደያ የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው፣ ከፍተኛ አምራችና የኤክስፖርት ድርጅቶች በቀጥታ እንዲያገኙ፣  ልዩ ትኩረት የሚሹ የመንግሥትና የግል ፕሮጀክቶች፣ የገቢና ወጪ ንግድን ጨምሮ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች፣ ግብርናን የሚያዘምኑ ትራክተሮች፣ የከተማና ሀገር አቀፍ የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች እንዲሁም በናፍታ የሚሠሩ ሌሎች ለሕብረተሰብ አግልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በቅድሚያ እንዲያገኙ  የሚያደርግ የቅድሚያ የነዳጅ አጠቃቀም አሠራር  የሚተገበር መሆኑን ገልጸዋል::

ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ተቋም እንደሚለው፣ የአስቸኳይ የነዳጅ ምላሽ ዓላማው ዋጋን ለረጅም ጊዜ መቆጣጠር ሳይሆን አጭር ጊዜ የአቅርቦት መቋረጥን ለመሻገር ነው:: የረጅም ጊዜ መፍትሔ የሚመጣው ከነዳጅ ጥገኝነት በመውጣት፣ አቅርቦትን በመለያየት እና አማራጭ ኀይል ላይ በመተማመን ነው::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here