መልካም ጅምር

0
100

ወይዘሮ እመቤት ሀብታሙን  ያገኘናቸው በባሕር ዳር ከተማ በቀበሌ  አራት ዋናው ገበያ ነው፡፡ ወይዘሮዋ ባዶ ዘንቢላቸውን ይዘው ነው ከገበያ መውጫው በር ላይ  ያገኘናቸው፤ ትክዝ ብለው ወደ ቀኝ እና ወደ ግራ አቅጣጫ ያማትራሉ፡፡ ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ   ወደ ገበያ ምን ሊገዙ እንደ መጡ ጠየቅናቸው፡፡  “የመጣሁትማ ለበዓል ሚሆን  ልገዛ አስቤ ነበር፡፡ ሆኖም እየተዘዋወርኩ የሚያስፈልጉኝን ሸቀጦች ስጠይቅ ከአሰብሁት በላይ ዋጋ ጨምሯል፡፡ በዚህም ምክንያት ምንም ሳልገዛ ወደ ቤቴ እየተመለስሁ ነው” አሉን  እንባ ያቀረረ አይናቸውን ወደ መሬት ተክለው ትክዝ እያሉ፡፡

እኛም የኑሮ ውድነቱ የወይዘሮ እመቤት ወይንም የባሕር ዳር ነዋሪዎች ችግር ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍል እየፈተነ መሆኑን እያሰላሰልን ተሰናብተን ወደ ገበያው ዘለቅን፡፡  የኑሮ ውድነትን የፈቱ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየው በዋናነት የምንዛሬ ተመንን በማረጋጋት፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ የግብርና ግብዓት ድጋፍ እና ውጤታማ ስርጭት መዘርጋት ነው።  የሲንጋፖር እና የአንዳንድ አውሮፓውያን ሀገራት ተሞክሮ የሚያስገነዝበውም ይህንኑ ነው፡፡   የምንዛሬ ተመንን በማረጋጋት እና የውጭ ምርቶችን በቀላሉ በማቅረብ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ችለዋል።

ሀገራቱ ከዚህ በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ የሚታየውን የዋጋ ንረት መቀነስ እንደቻሉ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡  የገበያ ቁጥጥር በተለይ መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የሚታየውን ያልተገባ  ጭማሪ ለመግታት በሕግ የተደገፈ ቁጥጥር በማድረግ እንዲሁም የመሠረተ ልማት እና ስርጭት ሥርዓት በመዘርጋት ምርት በቀላሉ ለገበያ እንዲቀርብ የአቅራቢዎችን ሰንሰለት በማሳጠር የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት የሕዝባቸውን የመግዛት አቅም ማሻሻል ችለዋል።

በሀገራችንም አምራቹ እና ሸማቹ ከደላላ ጣልቃ ገብነት ውጭ በሆነ መንገድ የሚገበያዩበት የገበያ ስፍራ እና በዓላትን ተከትሎ ደግሞ ባዛር በማዘጋጀት     ገበያውን የማረጋጋት ሥራ እየተካሄደ ነው፡፡ በአማራ ክልል የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደርም የምርቶችን ዋጋ መናር ተከትሎ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ   በከተማዋ ጣና ክፍለ ከተማ ዘመናዊ የንግድ ማእከል ገንብቶ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን የከተማ አሥተዳደሩ ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ  ገነት አሰፋ ገልፀዋል፡፡

እኛም በገበያ ማዕከሉ  ለትንሳኤ ዋዜማ በተከፈተው ባዛር ላይ ተገኝተን ነበር፡፡ በማዕከሉ የፋብሪካ ምርቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎች፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ለሕዝቡ ቀርቧል። በማዕከሉ ያነጋገራናቸው ነዋሪዎች የተለያዩ ዓይነት ምርቶች በተመጣጣኝ  ዋጋ ማገኘታቸው  ትልቅ እፎይታ እንደ ፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

በማዕከሉ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ዘይት፣ ፍርኖዱቄት፣ ቅቤ፣ ማር፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ሽንብራ፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ እና ሌሎችም በአይነት ቀርበዋል፡፡ በዚህም ሸማቾች ምርቶችን ከመደበኛው የገበያ ዋጋ በተሻለ እና በተመጣጣኝ ሁኔታ በማግኘታቸው ደስተኞች ናቸው።

ሀሳባቸውን  ለበኵር  ያጋሩት ወይዘሮ ጥሩነሽ አልታሰብ እንደተናገሩት  የዘይት ዋጋ ከመደበኛው ገበያ ጋር ሲነጻጸር በሊትር ከፍተኛ ቅናሽ አለው፡፡  “ውጭ ከሁለት ሺህ ብር በላይ የሚሸጠውን ዘይት በማዕከሉ በ1 ሺህ 750 ብር አግኝቻለሁ” ብለዋል። ሆኖም  ባለ አምስት ሊትር ዘይትና ሌሎች  ተፈላጊ ምርቶች አቅርቦት እጥረት አለ” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሌላዋ ሸማች ወይዘሮ ምሕረት ሲሳይ በበኩላቸው የተለያዩ የምርት አይነቶች  በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸው አስደስቷቸዋል፡፡    “በብዛት በካርቶንና በኩንታል ታሽገው መቅረባቸው ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማኅበረሰብ አቅም ቢፈትኑም እኛ ተረዳድተን በጋራ ገዝተን ነው የተካፈልነው፤ ደስ ብሎናል፡፡  ምርቶች በችርቻሮ ቢቀርቡ ደግሞ ለሁሉም ተደራሽ ይሆናል” የሚል ገንቢ አስተያየትም ሰጥተዋል።

እኔም እግረ መንገዴን በማዕከሉ  ተዘዋውሬ የተለያዩ ምርቶችን አይቻለሁ፡፡ከነዚህም መካከል  ሽንኩርት  ከ40 – 55 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት ከ85 – 100 ብር፣ ፍርኖ ዱቄት ከ106 – 108 ብር፣ ዘይት (5 ሊትር) 1ሺህ 750 ብር፣  ቅቤ አንድ ሺህ ብር፣ እንቁላል 15 ብር እየተሸጠ መሆንን መታዘብ ችያለሁ፡፡ የእንዳንድ ምርቶች ዋጋ ደግሞ ከውጭ ካለው ገበያ ጋር ሲነጻጸር ብዙም  ልዩነት አይታይበትም፤ እንዲያውም ተመሳሳይ ዋጋ ነው ያለው፡፡

የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም በሚደረገው ጥረት በርካታ ፋብሪካዎች እና አምራቾችም ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ በማቅረባቸው ደስተኛ ናቸው። ይህ አሠራር ምርቶቹ ከደላላ ጣልቃ ገብነት ውጭ  በቀጥታ ለተጠቃሚው እንዲደርሱም  አስችሏል።

ለሸማቾች እርካታ ቅድሚያ በመስጠት በባለ አምስት ፣ባለ ሦስት እና ባለ አንድ ሊትር ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆናቸውንም በባዛሩ ላይ ያገኘናቸው  አንዳንድ ዘይት አምራቾች  ተናግረዋል። ፋብሪካው የሚቀጥለው ተጠቃሚው ሲደሰት እንደሆነ የጠቆሙት አቅራቢዎቾ በቀጣይም በሚዘጋጁ ባዛሮች በመሳተፍ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እንቁላል ሲሸጡ ያገኘናቸው አቶ ምህረት ታምሩ በበኩላቸው ኅብረተሰቡ አንድ እንቁላል ከውጭ እስከ 19 ብር ድረስ እንደሚገዛ እና እርሳች በ15 ብር ሂሳብ እየሸጡ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ለአብዛኛው ማኅበረሰብም በቀጥታ ተደራሽ ለማድረግ እና በመካከል ነጋዴ ገብቶ ምርቱን ጠራርጎ እንዳይወስድ ለአንድ ሸማች ከሀምሳ እስከ አንድ መቶ እንቁላል ብቻ በመሸጥ ለገበያው መረጋጋት የበኩላቸውን አስተዋጾ ማበርከታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ  ገነት አሰፋ በበኩላቸው በምርቶች ያልተገባ የዋጋ ንረት ምክንያት የሚፈጠረውን የኑሮ ውድነት ለመከላከል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም አምራች እና ተጠቃሚን በቀጥታ የሚያገናኙ ቋሚ  የገበያ ማዕከላት  ገንብቶ ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን ጠቁመዋል።

ማዕከላቱ በዋነኛነት የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር እና ለሕዝቡ አማራጭ የገበያ ስፍራ ለመሆን ያለሙ ናቸው ብለዋል። በእነዚህ ማዕከላት 48 አምራቾች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለተጠቃሚው እያደረሱ ናቸው፡፡ የምርቶች ዋጋም የ15 በመቶ ቅናሽን ታሳቢ ያደረገ ነው።

የአማራ ክልል ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሒም ሙሐመድ (ዶ.ር) ማዕከሉ ማንኛውም ዓይነት ምርት የሚገኝበት እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። መሰል የገበያ ማዕከላትን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ለማስፋፋት በትኩረት እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል። ይህም በክልል ደረጃ የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ  ነው የተናገሩት።

መረጃ

የነጻ ገበያ ዋና ጥቅሞች

ነጻ ገበያ ውጤታማ ውድድር በመፍጠር ለሸማቾች የተሻለ ምርጫና ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡ ነው።

ሥርዓቱ፦

 

  • የሸማቾች ምርጫ እና ጥራት፡ የንግድ ተቋማት ተወዳዳሪ ለመሆን ጥራቱን የጠበቀ ምርት እና አገልግሎት በተሻለ ዋጋ ያቀርባሉ፣ ሸማቾችም የሚመቻቸውን የመምረጥ እድል ያገኛሉ።

 

  • የፈጠራ እና ምርታማነት እድገት፦ በገበያው ውስጥ ያለው ውድድር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የተሻሻሉ አሠራሮችን ለማስተዋወቅ ኩባንያዎችን ያነሳሳል።
  • የሀብት ውጤታማ አጠቃቀም፦ ገበያው በጥያቄ እና አቅርቦት ስለሚመራ ሀብት ወደሚያስፈልገውና ውጤታማ ወደሆነው ዘርፍ ይፈስሳል።
  • የግሉ ዘርፍ መስፋፋት፦ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት በመቀነሱ የግል ድርጅቶች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱና የኢኮኖሚውን እድገት እንዲመሩ እድል ይሰጣል።

በአጠቃላይ፣ የነጻ ገበያ ተወዳዳሪነትን በመጨመር የኢኮኖሚ ቅልጥፍናን የሚያረጋግጥ ሥርዓት ነው።

የነጻ ገበያ ጥቅሞች፡-

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር  የሚያዚያ 5  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here