ለግብርና ኢንቨስትመንት የተሰጠው ትኩረት ተጠናክሮ ይቀጥል!

0
15

የግብርና ኢንቨስትመንት ምርታማነትን በማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ በማምረት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለማኑፋክቸሪንግ ግብዓት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

ገንዘብን፣ ዕውቀትን፣ ቴክኖሎጂን እና ጉልበትን ባግባቡ በግብርናው ዘርፍ ላይ ባግባቡ በመጠቀም ማምረት ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ይህን መሰሉ የማምረት ሂደት ተጠቃሚ የሚያደርገው ባለሀብቱን ብቻ አይደለም፡፡ አርሶ አደሩንም ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ እርሻ ለማሸጋገር ሁነኛ ሚና ይጫወታል፡፡ አርሶ አደሩ በትራክተር እንዲያረስ፣ የተፈጥሮ ጥበቃን እንዲያዳብር አርሶ አደሩ በማስተማር እና የግብዓት አጠቃቀምን በማሳየት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት አውቆ ከተንቀሳቀሰ በጋራ መለወጥ ይቻላል።

የግብርና ኢንቨስትመንት ሥራው በተሻሻለ አሠራር፣ በመተጋገዝ ስሜት ከተከናወነ፣ ምርቱ በወቅቱ ለተጠቃሚው ከቀረበ የኑሮ ደረጃን በማሻሻል ረገድ የሚጫወተው ሚናም ከፍተኛ ነው፡፡

ዘርፉ የሚያስገኘውን ከፍተኛ ጠቀሜታ መሠረት በማድረግም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው፡፡ ከአማራ ክልል መሬት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው በክልሉ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺህ 635 በላይ ባለሀብቶች በዘርፉ ተሰማርተዋል፡፡ ከሁለት መቶ ሺህ ሄክታር በላይ መሬትም እየለማ ይገኛል።

ከግብርና ኢንቨስትመንት ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የተመረተውን ምርት በወቅቱ እና በፍጥነት አጓጉዞ ለገበያ የማቅረብ ጉዳይም በሚመለከተው አካል ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው፡፡

የገንዘብ ተቋማት በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች እና አርሶ አደሮች እያደረጉት ያሉትን የብድር ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል፣ ተበዳሪዎችም ሠርተው መክፈል ይኖርባቸዋል፡፡
የግብርና ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቅ እንደመሆኑ መጠን የባንኮች ድጋፍም ወሳኝ ነው።

ከተለያዩ አካላት ጋር የግብርና ኢንቨስትመንቱን እንዴት እናሻሸለው? ምን ችግሮች አሉ?፣ ከማን ምን ይጠበቃል? በሚሉ ጉዳዮች ላይ እየተደረጉ ያሉ ምክክሮችም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡
የግብርና ኢንቨስትመንትን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የመንግሥት ጠንካራ ድጋፍ እና ቁጥጥር አስፈላጊ ነው፡፡

መሬትን በተሰጠው ውል እና ግዴታ መሰረት አለማልማት፣ በተማረ የሰው ኀይል (ባለሙያ) እና በሰለጠነ መንገድ አለመመራት፣ ሕግ አለማክበር፣ ውል በወሰደበት አግባብ የተፈጥሮ ሀብትን አለመንከባከብ፣ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂን እና የግብርና ግብዓቶችን በስፋት እና በአግባቡ አለመጠቀም፣ መሬትን ለሦስኛ ወገን አሳልፎ መስጠት (ማከራየት)፣ ብድርን በወቅቱ አለመክፈል በባለሀብቶች በኩል የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች ስለሆኑ እነዚህን ችግሮች መፍታት ያስፈልጋል፡፡

በአንጻሩ ለአካባቢው አርሶ አደር የምርጥ ዘር እና የትራክተር ድጋፍ የሚያደርጉ፣ ምርታቸውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ እና ቴክኖሎጂ የሚያሸጋግሩ እጅግ አርአያ የሆኑ ባለሀብቶችም ይህን ጥረታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

መንግሥትም የመሰረተ ልማት (መንገድ፣ መብራት፣ ውኃ) ለማሟላት፣ የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ፣ (የፀጥታ) ችግሮችን ለመፍታት፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ ግብዓት እና ብድር ለማቅረብ የሚያደርገውን ጥረት የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል፡፡

በኲር የሚያዚያ 5 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here