ተስፋ እና ያልተሠሩ የቤት ሥራዎች

0
76

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ከ18 ዓመት በታች የሴቶች ወዳጅነት ዋንጫ በተረኪዬ በቅርቡ ተደርጎ ተጠናቋል:: ይህ ውድድር ከአውሮፓ፣ ከሰሜን አሜሪካ፣ ከደቡብ አሜሪካ እና ከአፍሪካ የተውጣጡ ስምንት ሀገራትን አሳትፏል:: አፍሪካን ወክለው ከተገኙት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ ይገኙበታል:: የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን በዚህ ትልቅ መድረክ ላይ ደማቅ ታሪክ አስመዝግቦ ተመልሷል::

ቡድኑ የላቲን አሜሪካ ጠንካራ የኳስ ባህል ያላቸውን ኮስታሪካን እና ኡራጋይን አሸንፏል:: የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ደግሞ ከአውሮፓዊቷ ሀገር ኖርዌይ ጋር ተጫውቶ አንድ ለባዶ ተሸንፎ ማጠናቀቁ አይዘነጋም::  የኢትዮጵያ ታዳጊዎች ሜዳ ላይ ያሳዩት ብቃት ሀገሪቱ በእግር ኳሱ ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ቁልጭ አድርጎ ያሳየ መሆኑን የእግር ኳስ ባለሙያዎች መስክረዋል::

ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ ታዳጊዎችን ለዓለም አቀፍ ፉክክር ከማዘጋጀቱም ባሻገር ለሀገር ውስጥ እግር ኳስ እድገት ትልቅ ትርጉም እንዳለው ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ተናግረዋል:: በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ የኢትዮጵያ ታዳጊ ቡድኖች ከአህጉር ውጭ የመወዳደር እድል ሲያገኙ ብዙ ጊዜ አይታይም:: ታዳጊዎች በዚህ መድረክ እንዲሳተፉ መደረጉ ለሀገራችን የሴቶች እግር ኳስ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አሰልጣኝ ብርሃኑ ይናገራሉ::

“እንዲህ አይነት እድሎች ብዙ ጊዜ ለኛ ሀገር በሄራዊ ቡድን ሲሰጥ አንመለከትም:: እናም በዚህ መድረክ ግለሰቦች እና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ እጅግ በጣም መመስገን አለባቸው” ብለዋል::  ወደ አውሮፓ  ተጉዞ መጫወት ትልቅ ትርጉም አለው:: በምሥራቅ አፍሪካ ያለው የጨዋታ ዘይቤ ብዙ ጊዜ መከላከል ላይ ያመዘነ ነው፤ ይህ ውድድር ታዳጊዎቹን ከዚህ አጥር እንዲወጡ እንደሚረዳቸው አሰልጣኝ ብርሃኑ ይጠቁማሉ:: “ኬንያ እና ኡጋንዳ ብትሄድ በጥብቅ የመከላከል ባህሪዎች አሉ:: እንዲህ ክፍት ጨዋታ መጀመሩ ወጣቶችን ያነቃቃል” ብለዋል አሰልጣኙ::

አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ተሳታፊው ብሄራዊ ቡድን ከመከላከል ባህል ወጥቶ ማጥቃትን መሰረት ካደረጉ የዓለም ሀገራት ጋር መጫወቱ የታዳጊ ተጫዋቾችን አቅም እንደሚሳድገው ያስረዳሉ:: የጨዋታ አረዳዳቸውን እና የሜዳ ላይ ውሳኔ አሰጣጣቸውንም እንደሚያሻሽለው አልሸሸጉም:: ታዳጊዎች ኮስታሪካን እና ኡራጋይን የመሳሰሉ በእግር ኳስ ጠንካራ ሀገራትን ማሸነፍ መቻሉ የተጫዋቾችን ስነልቦና በእጅጉ ይገነባል፤ ትልቅ መነቃቃትም ይፈጥርላቸዋል::

ውድድሩ በአውሮፓ እግር ኳስ የዩቲዩብ ገፅ በቀጥታ ተላልፏል:: በተለያዩ ዓለም አቀፍ የተጫዋች መልማዮች ክትትል የሚደረግበት በመሆኑ  በተለይም ግቦችን በማስቆጠር እና ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በማድረግ እይታ ውስጥ የገቡት ተጫዋቾች በአውሮፓ እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ክለቦች ዐይን ውስጥ እንዲገቡ ሰፊ ዕድል ይፈጥርላቸዋል:: “ውድድሩ ላይ ወኪሎች ይኖራሉ እና ታዳጊዎቹ ወደ ተሻለ የውጭ ሀገር ሊግ የማምራት እና የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ህይወትን የመጀመር ሰፊ እድል ይኖራቸዋል” ሲሉ አሰልጣኝ ብርሃኑ ይደመጣሉ::

ይህ ደግሞ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋችነት በሮችን በመክፈት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እና ስፖርታዊ አቅም እንደሚያሳድግ ይጠበቃል::

እንዲሁም የእነዚህ ታዳጊዎች ስኬት  በሀገር ውስጥ ለሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሴት ታዳጊዎች ትልቅ መነሳሳት እንደሚፈጥር ይገመታል:: “እነሱ በዓለም አቀፍ መድረክ ከቻሉ እኔም እችላለሁ” የሚል ስሜት በመፍጠር በየሰፈሩ፣ በየማሰልጠኛ ጣቢያው እና በየፕሮጀክቱ የሚገኙ ታዳጊዎች ወደ ስፖርቱ  እንዲገቡ ያደርጋል ብለዋል አሰልጣኙ:: ይህ የተርኪዬ ጉዞ ክለቦችም ሆኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለታዳጊ ሴቶች ፕሮጀክት የሚሰጡትን ትኩረት እና በጀት እንዲጨምሩ አስገዳጅ ምክንያት ይሆናል ተብሎም ይገመታል::

ይህ መድረክ ከእግር ኳስ ፉክክር ባሻገር ታዳጊዎቹ ከሌሎች ሀገራት አቻዎቻቸው ጋር ጓደኝነት እንዲመሰርቱ፣ ባህል እንዲለዋወጡ እና አድማሳቸውን እንዲያሰፉ ረድቷል:: በስፖርቱ ዓለም የኢትዮጵያን ስም በበጎ ገጽታ ከማስተዋወቅ አኳያም የተጫወተው ሚና ቀላል አይደለም::

እነዚህ ድንቅ ታዳጊ ተጫዋቾች በቀጣይ እንዳይጠፉ እና ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ብቁ እንዲሆኑ ጠንካራ ክትትል እና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል:: የዚህ ውድድር ተሳታፊዎች በትክክለኛ እድሜያቸው የተመረጡ በመሆናቸው ለሀገር ትልቅ ተስፋ እንደሚሆኑ አሰልጣኙ አስታውሰዋል::

ከዚህ በፊት የነበረው የሴቶች ዋና ብሄራዊ ቡድን ተተኪ አጥቶ እንደነበር ይታወሳል::  “ብሄራዊ ቡድኑ ደርቋል ማለት ይቻላል፤ ተተኪ አጥቷል:: እነዚህ ታዳጊዎች ለብሄራዊ ቡድኑ ትልቅ ግብአት ይሆናሉ:: በእድሜ እርከን በእንደዚህ አይነት ነገር እያሳተፍን የምንሄድ ከሆነ ብሄራዊ ቡድኑ ላይ ከፍ ያለ ነገር እንደምናመጣ ምንም ጥርጥር የለውም” ብለዋል::

ይህ ጤናማ የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲቀጥል ፌዴሬሽኑ እና ክለቦች ልጆቹን በትኩረት ሊከታተሏቸው እንደሚገባም አሰልጣኙ ያብራራሉ:: ከውድድር ሲመለሱ ክለቦቻቸው ቋሚ የጨዋታ ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ይጠቁማሉ:: የጨዋታ እድል ካላገኙ ተሰጥኦዋቸው ስለሚባክን እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የእያንዳንዱን ታዳጊ የእድገት ደረጃ የሚከታተልበት ስርዓት ሊኖረው ይገባልም ነው ያሉት አሰልጣኙ::

የአውሮፖ እግር ኳስ ማህበር ከ18 ዓመት በታች የሴቶች ወዳጅነት ዋንጫ ውድድር ለተጫዋቾች ብቻ ሳይሆን ለአሰልጣኞችም ትልቅ የልምድ መድረክ ነበር:: አሰልጣኞች እና ፌዴሬሽኑ ይህንን ልምድ ወደ ሀገር ውስጥ ክለቦች እና አካዳሚዎች በተገቢው መንገድ ሊያወርዱት እና ሊተገብሩት ይገባል:: ወደ ተርኪዬ ተጉዘው በውድድሩ የተካፈሉ አሰልጣኞች የአውሮፓን፣ የላቲን አሜሪካን እና የሌሎች ሀገራትን ዘመናዊ የእግር ኳስ ባህል በቅርበት በመመልከት እውቀት ያገኙ በመሆናቸው ይህን ትልቅ ልምድ በሀገር ውስጥ ሊጎች ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ይመክራሉ::

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም እነዚህን ልምድ ያገኙ አሰልጣኞች በመጠቀም ለሌሎች የሀገር ውስጥ አሰልጣኞች ስልጠና እንዲሰጡ ማድረግ አለበት ይላሉ:: ዘመናዊ የእግር ኳስ ፍልስፍና በሁሉም ክለቦች እና አካዳሚዎች እንዲሰርጽ ፌዴሬሽኑ መመሪያዎችንም  ማወጣት  እንዳለበት አሰልጣኝ ብርሀኑ አስተያየት ሰጥተዋል::

በአንድ ውድድር ላይ ብቻ መሳተፍ ዘላቂ ለውጥ አያመጣም:: ስለዚህ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን መልካም ጅምር አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት አሰልጣኙ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል::  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብዙ ጊዜ የገንዘብ ወጪን በመፍራት ትልልቅ እድሎችን ሲያጥፍ ቆይቷል:: ነገር ግን ታዳጊዎችን ወደ ውድድር መላክ እንደ ወጪ ሳይሆን የነገ ብሔራዊ ቡድንን ለመገንባት የሚደረግ ትልቅ ኢንቨስትመንት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ አሰልጣኙ ያስታውሳሉ::

በአንድ ውድድር ላይ ብቻ መሳተፍ ውጤታማ ሊያደርጋቸው አይችልም:: ስለዚህ ፌዴሬሽኑ ውድድሮችን በአካዳሚ ደረጃ ሳይቀር የመፍቀድ እና የማመቻቸት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው አስገንዝበዋል:: የዋናው የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ መድረክ  ከተሳተፈ ከአስራ አራት ዓመታት በላይ አልፎታል:: ይህን ታሪክ ለመቀየር ፌዴሬሽኑ መሰል የወዳጅነት ውድድሮችን አጥብቆ መፈለግ አለበት የሚል ሀሳብም ተነስቷል:: ፌዴሬሽኑ ከአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር፣ ከአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እና ከሌሎች ተቋማት ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማጠናከር የውድድር መድረኮችን ማምጣት ይጠበቅበታል::

በተርኪዬ የተካሄደው የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ከ18 ዓመት በታች የሴቶች ወዳጅነት ዋንጫ የኢትዮጵያን ሴቶች እግር ኳስ እውነተኛ አቅምን አሳይቷል፤ ታዳጊዎች ትክክለኛ መድረክ ካገኙ የትኛውንም ብሄራዊ ቡድን ማሸነፍ እንደሚችሉ በተግባር አረጋግጠዋል:: የተጀመረው ክትትል እና እንክብካቤ ተጠናክሮ ከቀጠለ እነዚህ ታዳጊዎች የነገ የሀገር ተስፋዎች እንደሚሆኑ አያጠራጥርም::

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here