የበልግ ሰብል ልማት

0
95

የአማራ ክልል የመኸር፣ የበጋ መስኖ ስንዴ እና የበልግ የሰብል ልማት የሚካሄድበት ዕምቅ ፀጋዎች አሉት። በክልሉ የሚከናወነው የመኸር ወቅት ሰብል ልማት ግንባር ቀደሙ ሲሆን ሌላው ደግሞ የበልግ ልማት ነው:: ወቅቱ የበልግ ሰብል የሚለማበት ነው፤ በክልሉ በምሥራቅ አማራ ደቡብ እና ሰሜን ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና ሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢዎች ደግሞ ዋና ዋናዎቹ የበልግ ልማት ተጠቃሚዎች ናቸው።

የበልግ ወቅት የግብርና ሥራ እንቅስቃሴን በተመለከተም በኵር ጋዜጣ አርሶ አደሮችን እና ባለሙያዎችን አነጋግራለች። አርሶ አደር አህመድ መሐመድ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር አርጡማ ፉርሲ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። አርሶ አደሩ በስልክ እንደነገሩን በመኸር፣ በበጋ መስኖ ስንዴ እና በበልግ ወራት የተለያዩ ሰብሎችን በማምረት ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ።

አርሶ አደሩ አትክልት እና ፍራፍሬ በማምረት ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ነግረውናል። ለአብነትም አፕል፣ ማንጎ፣  ሙዝ እና ሎሚ በስፋት በማምረት ገቢያቸውን ማሳደግ ችለዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በመጠቀማቸው ምርቱ እየተሻሻለ መምጣቱንም ያስረዳሉ። በተያዘው የበጋ እርሻ የተፈጥሮ ማዳበሪያን (ኮምፖስት) በብዛት አዘጋጅተው በመጠቀም በወቅቱ ዘርተዋል። ይህም የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ለመቀነስ እንዳስቻላቸው ነው የተናገሩት።

በ2018 ዓ.ም የበልግ ወቅትም በአንድ ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ እና ማሾ ዘርተው አብቅለዋል። አሁን ላይ ሰብሉ በአረም እንዳይጠቃ እና በጎርፍ ጉዳት እንዳይደርስበት ጥበቃ እና እንክብካቤ እያደረጉ መሆኑን ነው የተናገሩት። ከዚህ ጎን ለጎን ለመጭው የክረምት ወራት በዘር የሚሸፍኑትን ማሳ እየለዩ መሆኑን ነግረውናል።

ሌላው በስልክ ያነጋገርናቸው የሰሜን ወሎ ዞን አንጎት ወረዳ 05 ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ፀጋው ባሕሩ ናቸው። የሚዘንበውን የበልግ ዝናብ በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ ምርት ማግኘት የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። አርሶ አደሩ በሦስት አራተኛ (ሦስት ጥማድ) መሬታቸውን ደጋግመው በማረስ ገብስ እና ስንዴ በበልግ ዘር እንደሸፈኑ ነግረውናል።

እንደ አርሶ አደሩ ማብራሪያ የግብርና ባለሙያዎች ዘመናዊ አሠራርን እንዲከተሉ እገዛ ያደርጉላቸዋል። ለብዙ ዓመታትም የተፈጥሮ ማዳበሪያን ተጠቅመዋል። ይህም የአፈር ለምነቱን ከመጠበቅ ባለፈ የተሻለ ምርት እንዲያገኙ እና ለሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የሚያወጡትን ገንዘብ እንደቀነሰላቸው ያስረዳሉ።

የዘንድሮው የዝናብ ስርጭት በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን የጠቆሙት አርሶ አደሩ ይህም የተሻለ ምርት ለማግኘት ተስፋ ሰጭ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዞን ዘንድሮ በተከናወነው የበልግ እርሻ ልማት ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል:: ከዚህም ከ100 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ ግብርና መምሪያ ገልጿል። አርሶ አደሩ የግብርና ሥራውን ለማዘመን የእርሻ ትራክተሮችን በስፋት እየተጠቀመ መሆኑም የመምሪያው የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ደጀኔ ከበደ ለበኵር በስልክ አብራርተዋል::

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ በበልግ ወቅቱ 10 ሺህ 386 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል:: አርሶ አደሩም ባደረገው ርብርብ ከዕቅድ በላይ 12 ሺህ 610 ሄክታር መሬት ታርሷል። ከዚህ ውስጥ እስካሁን 10 ሺህ 748 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል።

በዞኑ በአብዛኛው ቆላማ የአየር ንብረት ባላቸው አካባቢዎች የበልግ ልማት የሚከናወን በመሆኑ ማሾ የተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሰብል ስምንት ሺህ 236 ሄክታሩን በመሸፈን ቀዳሚ ሆኗል:: ከማሾ በተጨማሪ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ማሽላ፣ ስንዴ፣ ባቄላ፣ አተር እና ምስር በዞኑ አርሶ አደሮች በበጋ በመልማት ላይ ይገኛሉ።

“በበልግ መጀመሪያ አካባቢ የዝናብ መዘግየት ቢያጋጥምም አሁን ላይ በመስተካከሉ የሰብሉ ቁመና በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል” ያሉት አቶ ደጀኔ በሰብል ከተሸፈነው መሬት አጠቃላይ 101 ሺህ 458 ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል::

በሌላ በኩል ዞኑ ለቀጣዩ የመኸር (ዋናው የዝናብ ወቅት) እርሻ  ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። ለመኸር እርሻ እስካሁን 35 ሺህ 578 ሄክታር መሬት የታረሰ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 11 ሺህ 359 ሄክታር የሚሆነው በዘመናዊ የእርሻ ትራክተር የታረሰ ነው። ይህ አሃዝ በዞኑ የግብርና ሜካናይዜሽን አጠቃቀም እያደገ መምጣቱን ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ቡድን መሪው ገልጸዋል።

አቶ ደጀኔ ለአርሶ አደሩ ባስተላለፉት መልዕክት አሁን ላይ የተዘሩ የበልግ ሰብሎችን አረም በማረም እና በመኮትኮት እንዲሁም ከተባይ በመጠበቅ ምርት እስከሚሰበሰብ ድረስ ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ለቀጣዩ የመኸር እርሻም ማሳን በጊዜ በማዘጋጀት፣ ጊዜውን ጠብቆ በመዝራት እና የሙሉ ፓኬጅ (ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር) ተጠቃሚ በመሆን የተሻለ ምርት ለማግኘት እንዲተጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን የአንጎት ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋ ጌታቸው ለበኵር ጋዜጣ በስልክ እንደተናገሩት በተያዘው የበልግ ወቅት 25 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በዘር ተሸፍኗል። ለበልግ ሰብል ልማት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን  አቶ ተስፋ ጠቁመዋል:: ለአብነትም የእርሻ ድግግሞሽ፣ ማሳን በተገቢው መንገድ ማዘጋጀት፣ የአፈር ማዳበሪያን ማቅረብ እና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ይገኙበታል።

እርጥበት አጠር አካባቢዎች ላይ ፈጥነው የሚደርሱ እንደ ማሾ ያሉ ከሁለት እስከ ሦስት ወር የሚፈጁ ሰብሎችን እንዲዘሩ መደረጉንም ገልጸዋል። በመሆኑም ቀድሞ የማሳ ዝግጅት (ደጋግሞ ማረስ) እና የግብዓት አቅርቦት ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል። ስንዴ፣ ምስር፣ ተልባ እና ገብስ በስፋት በዘር የተሸፈኑ ሰብሎች እንደሆኑ አመላክተዋል። አንድ ሺህ 200 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና 850 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘርን ጨምሮ ጥቅም ላይ ውሏል። ከዚህ በተጨማሪም 142 ሺህ ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) በማዘጋጀት ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ማሳውን በደንብ አዘጋጅቶ፣ ጊዜውን ጠብቆ እና ሙሉ የግብርና ፓኬጅ (ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር) ተጠቅሞ እንዲዘራ ግንዛቤ መፈጠሩንም ጠቁመዋል።

ኃላፊው እንዳሉት የግብርና ባለሙያዎች ለአርሶ አደሮች  ተገቢውን ድጋፍ እና ክትትል እያደረጉ ይገኛል። በተመሳሳይ ከበልግ ሰብል ልማት ጎን ለጎን የመኸር ሥራ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው። በበልግ ወቅት ከለማው ሰብልም 152 ሺህ 550 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጽ/ቤቱ መረጃ ያመላክታል። ይህን ዕቅድ ለማሳካትም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አቶ ተስፋ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የአየር ትንበያ መረጃ መሠረት በበልግ አብቃይ አካባቢዎች ለእርሻ ምቹ የሆነ ዝናብ እየዘነበ ነው። በመሆኑም በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተመላክቷል። በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት የበልግ ተጠቃሚ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ እንደሚያገኙ ኢንስቲትዩቱ ገለጿል።

በአብዛኛዎቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ እስከ ሚያዚያ የመጨረሻዎቹ አሥር ቀናት ቀጣይነት የሚኖረው ሲሆን በተጨማሪም ከሚጠናከሩት ሚቲዎሮሎጂ ክስተቶች ጋር ተያይዞ ወቅታዊው ዝናብ ቀስ በቀስ ወደ ምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ እንደሚስፋፋ ተገልጿል። በመሆኑም በልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ ተብሏል።

በአማራ ክልል የ2018 የበልግ እርሻ ወቅት በመጠቀም በዘር ለመሸፈን ተግባራዊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል። በክልሉ አሁን ላይ እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ እና በግብርናው ዘርፍ ያለውን አቅም ለመጠቀም ግብ በማድረግ አርሶ አደሩ የዘር ሥራውን እያከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመላክታል። በዚህም እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም 245 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ በተደረገ ጥረት እስካሁን ከ241 ሺህ  ሄክታር በላይ በገብስ፣ በስንዴ፣ በማሾ፣ በጤፍ እና በሌሎች ሰብሎች መሸፈኑን ገልጿል።

መረጃ

በኢትዮጵያ ውስጥ አራት ዋና ዋና ወቅቶች አሉ። እነሱም እንደ ኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር እና የአየር ንብረት ሁኔታ የየራሳቸው የሆነ የተለየ ባህሪ አላቸው።

  1. ክረምት (ከሰኔ 26 — መስከረም 25)

የክረምት ወቅት በኢትዮጵያ ዋናው የዝናብ ወቅት ነው። አብዛኛው የኢትዮጵያ አርሶ አደር መሬቱን አርሶ ዘር የሚዘራበት እና ተፈጥሮም አረንጓዴ ልብስ የምትለብስበት ወቅት ነው።

  1. መፀው /ፀደይ/ (ከመስከረም 26 — ታኅሣሥ 25)

የክረምት ዝናብ አብቅቶ ሰማዩ የሚጠራበት፣ ብሩህ ፀሐይ የሚወጣበት እና ምድር በልምላሜ እንዲሁም በአበቦች የምታሸበርቅበት ወቅት ነው።

  1. በጋ (ከታኅሣሥ 26 — መጋቢት 25)

በጋ ደረቅ እና ፀሐያማ ወቅት ነው። ገበሬው ሰብሉን ሰብስቦ የሚጨርስበት ወቅትም ነው።

  1. በልግ (ከመጋቢት 26 — ሰኔ 25)

ሙሉ በሙሉ እንደ ክረምት ዝናብ ባይዘንብም አልፎ አልፎ ዝናብ የሚጥልበት ወቅት ነዉ።

አርሶ አደሩ ለዋናው የክረምት እርሻ ዝግጅት የሚያደርግበት፣ ማሳውን የሚያለሰልስበት እና ፈጥነው የሚደርሱ አዝርዕት የሚዘራበት ጊዜ ነው።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የሚያዚያ  12  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here