የባሕር ሕጉ ምን ይላል? አተገባበሩስ?

0
73

ከ20በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም ዘይት እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል ያልፋል:: ይህ ጠባብ የውኃ መንገድ በዓለም አቀፍ የኢነርጂ ሥርዓት ውስጥ ካሉት ስትራቴጂካዊ አስፈላጊ የባሕር ማነቆ ነጥቦች መካከል  አንዱ ነው::

የውኃ መተላለፊያው በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ ካለው ወሳኝ ሚና የተነሳ ዓለም አቀፍ የሕግ እና የዲፕሎማሲ ማዕቀፎች የመሳሰሉ አዳዲስ ፈተናዎች እየገጠሙት ነው:: አሁን ባለው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ምክንያት ሰርጡን ኢራን በመዝጋቷ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች እንደበፊቱ መንቀሳቀስ አልቻሉም:: ይህም የዓለም ኢኮኖሚ ላይ ጫና በመፍጠሩ የመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎችን ጨምሮ ማንኛውም ቁሳቁስ ላይ የዋጋ ጭማሪ አስከትሏል:: ይህ ሁኔታ በተለይም እንደ አፍሪካ ባሉ በርካታ ታዳጊ ኢኮኖሚ ባላቸው አህጉራት ላይ ጫናው የበረታ ሆኗል::

ኢራን በኢኮኖሚ እራስን መከላከል እና ሉዓላዊነት ላይ የተመሠረተ ስልታዊ እና ሕጋዊ ማረጋገጫዎችን ብታቀርብም መሰል ድርጊቶች ለዓለም አቀፍ የባሕር ጉዞ አስፈላጊ የሆነውን የማይታገድ የመተላለፊያ መብትን ሊጥሱ እንደሚችሉ ይነገራል:: በተጨማሪም የባሕር መንገዱን ለመዝጋት የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ወደ ከባድ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት፣ ከፍተኛ የገንዘብ ወጪዎች እና ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ወታደራዊ ምላሽ ሊሰጥ ይችላል::

እ.አ.አ በ1982 የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ስምምነት (UNCLOS) ስር እንደተመላከተው ዓለም አቀፍ ንግድ እና መሰል ተግባራት የሚከናወንባቸውን የባሕር መስመሮችን በተመለከተ በርካታ ነጥቦችን አስፍሯል፤ በዚሁ ስምምነት መሠረትም የሆርሙዝ ሰርጥ በአንቀጽ 38 ስር “የመተላለፊያ መንገድ” የሚለውን መስፈርት አሟልቷል:: ይህም ለሁሉም መርከቦች እና አውሮፕላኖች ያለ እገዳ እና የባሕር ዳርቻ ጣልቃ ገብነት ለዓለም አቀፍ የባሕር ጉዞ በሚጠቀሙት የባሕር ዳርቻዎች ውስጥ የመንቀሳቀስ መብትን ይሰጣል:: ሆኖም ኢራን ምንም እንኳን የስምምነቱ ፈራሚ ብትሆንም (United Nations Convention on the Law of the Sea/UNCLOS) ስላላጸደቀችው ስጋት ገባኝ ባለች ቁጥር ሰርጡን እየዘጋችው ነው፤ ከሰሞኑም ሙሉ ለሙሉ በመዘጋቱ ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖው ከፍተኛ ሆኗል::

ማንኛውም የኢራን ጥረት የባሕርን ዳርቻ ለመከልከል ወይም ለመገደብ በተለይም የገለልተኛ ሀገራትን መብት የሚገታ ከሆነ ወይም ዓለም አቀፋዊ የኃይል አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር ከሆነ ዓለም አቀፍ ሕግን ይጥሳል:: የኢነርጂ ተንታኝ የሆኑት ቫንዳና ሃሪ እንደተናገሩት እንዲህ ያለው እርምጃ ኢራንን በኢኮኖሚ የሚያጠፋ ብቻ ሳይሆን እንደ ቻይና እና ሕንድ ያሉ ወሳኝ የንግድ አጋሮቿን በማራቅ የኢራን የረዥም ጊዜ ጂኦፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ይጎዳል::

ዘመናዊው የባሕር ሕግ በአብዛኛው የተመሠረተው እ.አ.አ በ1982 በተፈረመውና በ1994 ሥራ ላይ በዋለው የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ኮንቬንሽን (United Nations Convention on the Law of the Sea – UNCLOS) ላይ ነው:: ስምምነቱም የባሕር ላይ ሕጎች “ሕገ-መንግሥት” ተደርጎ ይወሰዳል::

በሕጉ ላይ 170 የዓለም ሀገሮች ፈርመዋል፤ የዓለም ሀገሮች የባሕር ክልልና ወሰንን በምን መንገድ መጠቀም እንደሚገባቸው መሠረታዊ መርሆዎችን አስቀምጧል:: ሕጉ የዓለም ውቅያኖሶችንና ባሕሮችን አጠቃቀም፣ የሀገራትን የባሕር ወሰን፣ የባሕር ሀብት አጠቃቀምና ጥበቃ የሚገዛ፣ በባሕር ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ሥርዓት የሚያስይዝ የሕግ ማዕቀፍ ነው::

የአንድ ሀገር የውኃ ክልል ከባሕር ጠረፍ (ከየብስ) እስከ 22 ኪሎ ሜትር ድረስ ያለውን የውኃ አካል እንደሚያጠቃልል ሕጉ ያስረዳል:: በዚህም የሉዓላዊ ሀገሮች የባሕር ክልል ላይ የትኛውም ሀገር ለሰላማዊ ጉዳይ እስከሆነ ድረስ መተላለፊያ ሊከለከል እንደማይችል ተመልክቷል:: ከአንድ ሀገር የየብስ ወይም የባሕር ጠረፍ ተነስቶ እስከ 370 ኪሎ ሜትር በሚረዝመው የባሕር አካል ላይ ደግሞ አንድ የባሕር በር ያለው ሀገር የራሱን የኢኮኖሚ ዞን (exclusive economic zone-EEZ) መመሥረት እንደሚችል ተገልጿል::

በዓለም አቀፍ የባሕር ሕጉ ከአንቀጽ 24 እስከ 26 ባለው ክፍል እንደተመላከተው የባሕር በር ያላቸው ሀገሮች መብትንና ዓለም አቀፍ ግዴታን በግልጽ የሚያስቀምጥ በተለይ ‘የባሕር በር ባለቤት ነኝ’ በሚል ብቻ ሀገሮች እንደፈለጉት የመሆን  መብት የላቸውም:: የባሕር ወሰናቸውን ለሰላማዊ እንቅስቃሴ እስከሆነ ድረስ ለሌሎች ሀገሮች ዝግ ማድረግም አይችሉም:: የባሕር ክልላቸው ለባሕር እንቅስቃሴው ሰላማዊና ምቹ ስለመሆኑ ለመላው ዓለም መረጃ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸውም ተመላክቷል::

በሌላ በኩል በባሕር ድንበራቸው ላይ ነዳጅ መሙላትን ጨምሮ የወደብና የትራንዚት አገልግሎት ለሚፈልግ መርከብ ያለ ልዩነትና ያለ አድልኦ ባወጡት ተመን ምክንያታዊ ክፍያ በመሰብሰብ አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ ይፈቅዳል:: በአጠቃላይ ሀገሮች የባሕር በር ባለቤት ነን በሚል ብቻ በሌሎች ሀገሮች ላይ ጫና እንዳያሳድሩ ሕጉ ያስገነዝባል::

ዓለም አቀፉ የባሕር ሕግ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት (እንደ ኢትዮጵያ ያሉ) የባሕር በር የመጠቀም፣ እና የባሕር ሀብት ተጠቃሚ የመሆን መብታቸውን ይደነግጋል:: በተጨማሪም የባሕር ላይ ክርክሮች ሲነሱ ችግሩን ለመፍታት የባሕር ሕግ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት (International Tribunal for the Law of the Sea – ITLOS) እና ሌሎች የፍትሕ አካላትን ይጠቀማሉ:: ይህ ሕግ የባሕር አካባቢን ከብክለት መከላከልና የተፈጥሮ ሀብትን ዘላቂ በሆነ መንገድ መጠቀም ላይ ትኩረት ያደርጋል:: ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር 60 ኪሎ ሜትር ባልበለጠ ርቀት ላይ መገኘቷን ልብ ይሏል::

ይህ በእንዲህ እያለ ዓለም አቀፉ የባሕር ሕጉ ፈተና እያጋጠመው መሆኑ ተገልጿል:: የሬውተርስ ዘገባ እንዳመላከተው በሆርሙዝ ሰርጥ ዙሪያ በቅርቡ ኢራን በዚህ ዋና የነዳጅ መተላለፊያ  መንገድ ላይ ከፍተኛ ክፍያ መጠየቋ እና ገደብ መጣሏን እየተቹ ይገኛሉ:: የባሕር ሕግ ባለሙያዎችም ይህን እርምጃ ከተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ኮንቬንሽን ጋር የሚጋጭ መሆኑን ይገልጻሉ::

በባሕር ሕጉ መሠረት ትራንዚት ፓሴጅ (Transit Passage) የተባለው መብት መርከቦች በዓለም አቀፍ ሰርጦች በነፃ እንዲጓጓዙ ይፈቅዳል:: ስለዚህ መንገዱን መዝጋት ወይም ከፍተኛ ክፍያ መጣል ሕጉን የሚጻረር ነው:: ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ብዙ ሀገራት ይህን እንደ አደገኛ ተምሳሌት በመግለጽ መተላለፊያ መንገዱ እንዲከፈት  ጠይቀዋል:: ይህ ካልሆነ ግን የኢራንን ተሞክሮ ሌሎችም በባሕር ጠረፍ ዙሪያ የሚገኙ ሀገራት ሊከተሉ ይችላሉ የሚል ስጋት መፍጠሩን ሬውተርስ ዘግቧል::

የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ኮንቬንሽን (United Nations Convention on the Law of the Sea UNCLOS) የባሕር መተላለፊያ መንገዶች ክፍት እንዲሆኑ ይጠይቃል:: ነገር ግን የአሁኑ ውጥረት ዓለም በሕግ ይመራል ወይስ በኃይል? የሚለውን ጥያቄ ሰዎች እንዲጠይቁ አስገድዷል::

በተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ስምምነት (UNCLOS) መሠረት መርከቦች በእንደዚህ ዓይነት የውኃ መስመሮች ውስጥ የመጓጓዣ መብት አላቸው:: ይህ ማለት  የባሕር ዳርቻዎችን የሚያዋስኑ ሀገሮች መርከቦች ያለማቋረጥ እና ያለምንም እንቅፋት እንዲያልፉ መፍቀድ ይኖርባቸዋል ማለት ነው:: ይሁንና እነዚህን የባሕር ዳርቻዎች የሚያዋስኑ ሀገሮች ለደኅንነት ወይም ለአካባቢ ጥበቃ ሲባል ትራፊክን መቆጣጠር ይችላሉ:: ነገር ግን መተላለፊያን ማገድ ወይም መጓጓዣን በመፍቀድ ብቻ ክፍያ ሊጥሉ አይችሉም:: ይህ መርህ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ክፍት ሆነው እንዲቆዩ እና በማንኛውም ሀገር ቁጥጥር ስር እንዳይሆኑ ለማድረግ ነው::

ዓለም አቀፍ የመርከብ መተላለፊያ መንገዶች

ዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት (WTO) እንዳስታወቀው ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የዓለም ንግድ በመርከብ ይጓጓዛል:: ነገር ግን ይህ ትልቅ እንቅስቃሴ በማንኛውም ቦታ አይደለም የሚያልፈው፤ በጣም ጥቂት ነገር ግን ወሳኝ የሆኑ የመርከብ መተላለፊያ መንገዶች ላይ ተመሥርቶ ነው:: ከእነዚህ የውኃ መተላለፊያ መንገዶች መካከል አንዱ ብቻ ከተዘጋ የዓለም ንግድ በአጭር ጊዜ ሊታወክ ይችላል:: ለምሳሌ የሱዊዝ ካናል (ቦይ) መዘጋት እ.አ.አ በ2021 የዓለምን ንግድ ለአጭር ጊዜ ቢሆንም አውኮ ነበር::

ዓለም አቀፍ የመርከብ መተላለፊያ መንገዶች (major global shipping routes/ chokepoints) ቁጥራቸው በትክክል እንዲህ ነው ተብሎ የሚወሰን አይደለም:: ምክንያቱም ዓለም አቀፍ ንግድ መስመሮች ብዙ ሲሆኑ ከእነሱ ውስጥ ግን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ዋና መተላለፊያ ቦታዎች ዘጠኝ እንደሆኑ በዓለም ንግድ ድርጅት የተደረጉ ጥናቶች ይገልጻሉ::

ከእነዚህ ዓለም አቀፍ የመርከብ መተላለፊያ መንገዶች መካከል አንድ አምስተኛው (ሃያ በመቶው) የዓለም ነዳጅ ዘይት የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ሰርጥ (Strait of Hormuz) አንደኛው ነው፤ እስያን ከአውሮፓ የሚያገናኘው የማላካ ሰርጥ (Strait of Malacca) ቻይና፣ ጃፓን እና አንዳንድ የእስያ  ሀገራት ይጠቀሙበታል:: የሱዊዝ ካናልን (Suez Canal) ከአውሮፓ ወደ እስያ የሚወስድ አጭር የውኃ ላይ መንገድ ስለሆነ በርካታ የንግድ መርከቦች ይጠቀሙበታል:: አትላንቲክና የፓሲፊክ ውቅያኖሶችን የሚያገናኘው የፓናማ ካናል (Panama Canal) ደግሞ ፓናማ ውስጥ የተሠራ ሰው ሠራሽ የውኃ መንገድ ነው:: መስመሩን መርከቦች በደቡብ አሜሪካ መዞር ሳይጠበቅባቸው የመተላለፉበት ነው::

ቀይ ባሕርን ከሕንድ ውቅያኖስ የሚያገናኘው የባብ ኤል-ማንዴብ (Bab el-Mandeb) መስመርን ደግሞ መርከቦች ወደ አውሮፓ ለመድረስ ይጠቀሙበታል:: ይሁንና ብዙ ጊዜ ከየመኑ የሃውቲ ታጣቂ ቡድኖች ምክንያት የደኅንነት አደጋ ያንዣብበታል:: ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ(cape of good hope) እጅግ ረዥም መንገድ ሲሆን የነዳጅ ክፍያ እና የሚወስደው ጊዜ ከሌሎቹ ከፍተኛ ነው:: ከዚህ በተጨማሪም  አትላንቲክን ከሜዲትራኒያን የሚያገናኝ የጂብራልታር ሰርጥ (Strait of Gibraltar) እና ጥቁር ባሕርን ከሜዲትራኒያን የሚያገናኘው የቦስፎረስ ሰርጥ (Bosporus Strait) ይጠቀሳሉ::

ከላይ የተጠቀሱት መስመሮች ታዲያ የዓለም የውኃ ላይ ንግድ የሚሳለጥባቸው ነው፤ የአንዱ መስመር መዘጋትም አሉታዊ ተጽዕኖው ዓለም አቀፋዊ ነው:: ለአብነትም የዓለማችን እስከ 14 በመቶ የሚደርሰው የንግድ ልውውጥ የሚካሄድበት የቀይ ባሕር መስመር በየመኑ ታጣቂ ሃውቲ ጥቃት ምክንያት ልብዙ ጊዜ ተስተጓጉሏል፤ መርከቦችም ከመደበኛው በተጨማሪ እስከ 17 ሰዓታትን እንዲጓዙ አስገድዷል:: በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ምክንያት ችግር ላይ የወደቀውና 20 በመቶ ያህሉ የዓለማችን ነዳጅ የሚተላፍበት የሆርሙዝ ሰርጥ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ መዛባትን አስከትሏል::

 

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሚያዚያ  12 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here