አርቆ  ማስቀመጥ

0
94

በሰውነታችን ውስጥ ገብቶ ውስጣችንን እንደ ሚቦረቡር በሽታ ሳይሆን በፈገግታ ታጅቦ ነፍሳችንን የሚመጠው የሰው ‘ቫይረስ’ ገጥሟችሁ ያውቃል? አንዳንዴ ገዳዩ መርዝ በባለቀለም ጠርሙስ እንደሚቀመጥ ሁሉ አውዳሚው ጭንቀትና የአእምሮ ጠላትም ‘አስብልሃለሁ’ በሚሉ የቅርብ ሰዎች ካባ ተጠቅልሎ ይመጣል:: በዙሪያችን ያሉ ሰዎች የደስታችን ምንጭ ወይም የሰላማችን መጋቢ መሆን ሲገባቸው ይልቁንም የአእምሯችንን ሕዋሳት የሚገድሉና ማንነታችንን የሚያኮማትሩ ‘መርዛማ’ ፈንጂዎች ከሆኑስ?

ሳይኮሎጂ ቱዴይ ድረ ገጽ እንዳሰፈረው መርዛማ ሰዎች ራስ ወዳድ፣ አታላይ፣ በዳይ እና የሌሎችን ስሜት የማይረዱ (ርኅራኄ የሌላቸው) ሊሆኑ ይችላሉ:: መርዛማ ሰዎች ሁልጊዜ ትኩረትን፣ ርኅራኄን ወይም እውቅናን በመሻት የሌሎችን አቅም ያሟጥጣሉ:: መርዛማ ሰዎች ስሜታዊ እና አካላዊ ድንበሮችን አያከብሩም::

አንዳንዶች አዎንታዊነትን የሚያንጸባርቁ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ስሜታችንን አሟጥጠው እና አታለው ባዶነት እንዲሰማን ያደርጋሉ:: መርዛማ (Toxic) ሰዎች በአእምሯዊ እና ስሜታዊ ደህንነታችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደር ለድካምና ለጭንቀት ይዳርጉናል:: እነዚህ ሰዎች እንዴት ኃይላችንን አሟጥጠው የቀድሞ ማንነታችን ቀፎ ብቻ እንዲሆን  ያደርጉናል? አንድን ሰው መርዛማ የሚያደርገው ምንድን ነው?  ለምን እና እንዴት ደህንነታችንን ያውካሉ?

መርዛማ ሰው መሆን ማለት ምን ማለት ነው?

መርዛማ ሰዎች በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች ላይ ዘላቂ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ አደገኛ ባህሪያት አሏቸው:: አብዛኛውን ጊዜ ራስ ወዳድ፣ አታላይ፣ በዳይ እና የሌሎችን ስሜት የማይረዱ ናቸው:: የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያሳድዱ (ናርሲሲስት)፣ ስግብግብ ወይም ፀረ-ማህበረሰብ (ሶሺዮፓዝ) ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ:: አሉታዊ ባህሪያቸውን ማራኪ ወይም ተወዳጅ በመምሰል ሊደብቁት ይችላሉ::

መርዛማ ሰዎች የቤተሰብ አባላት፣ ጓደኞች፣ የስራ ባልደረቦች፣ አሠሪዎች፣ ጎረቤቶች ወይም የድርጅት መሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ::

ብዙዎቻችን  በጓደኝነት፣ በዝምድና፣ በሥራ ቦታ፣ አሊያም በፍቅር ግንኙነት ስም ራሳችንን ለመርዛማ ሰዎች አሳልፈን ሰጥተን የራሳችንን ህይወት ሲኦል እናደርጋለን:: እነዚህ ሰዎች ቀንዶችን ያበቀሉ አጋንንት አይደሉም፤ ይልቁንም ፈገግታን የተላበሱ “አስብልሃለሁ” የሚሉ ነገር ግን ውስጣችንን እንደ ምስጥ የሚቦረቡሩ የኃይል መጣጮች (Energy Vampires) ናቸው::

የስነ ልቦና ባለሙያዋ ሊሊያን ግላስ (ዶ/ር)  እ.ኤ.አ በ1995 ባሳተሙት “Toxic People” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ መርዛማ ሰዎችን እንዲህ ሲሉ ይገልጿቸዋል “አብረሃቸው ስትሆን ራስህን እንድትጠላ የሚያደርጉህ፣ ጉልበትህን የሚመጡ እና ሁልጊዜም በግንኙነታችሁ ውስጥ አንተን ዝቅ አድርገው ራሳቸውን ከፍ የሚያደርጉ ናቸው::”

መርዛማ ሰዎች በአብዛኛው የሚጠቀሙት እጅግ አደገኛ የሆነ የስነ ልቦና ማጭበርበርን ነው:: ለምሳሌ “ጋስላይቲንግ” (Gaslighting) የተሰኘውን እውነታን የማዛባት ስልት ይጠቀማሉ:: ጥፋት አጥፍተው ሲያበቁ “አንተ ነህ እንጂ ስሜታዊ የሆንከው  እኔ እንደዚህ አላልኩም” በማለት የገዛ አእምሯችሁን እና የማስታወስ ችሎታችሁን እንድትጠራጠሩ ያደርጓችኋል:: ሁልጊዜም ራሳቸውን እንደ ተበዳይ (Victim) ያቀርባሉ፤ እናንተ ግን ሳታጠፉ ይቅርታ እንድትጠይቁ ትገደዳላችሁ::

የዚህ ችግር አሳሳቢነት በስሜት መጎዳት ብቻ አያበቃም:: በጀርመን የሚገኘው ፍሬድሪክ ሺለር ዩኒቨርሲቲ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ለመርዛማ ሰዎች መጋለጥ በአእምሯችን ላይ እጅግ ከፍተኛ የሆነ የጭንቀት ሆርሞን (Cortisol) እንዲመነጭ ያደርጋል:: ይህ በተከታታይ የሚረጭ የጭንቀት ሆርሞን ውሳኔ የመወሰን እና የማስታወስ ሥራን የሚሠራውን የአእምሯችንን ክፍል (Hippocampus) ሴሎች እንደሚገድል እና አእምሮን እንደሚያኮማትር ጥናቱ አረጋግጧል:: በሌላ አገላለጽ መርዛማ ሰዎችን በህይወታችን ባቆየን ጊዜ ሁሉ ቃል በቃል አእምሯችንን እያጠፋነው ነው::

ይህንን ባህሪያቸውን ጠቅሰን ብንነግራቸው በእነሱ ባህሪ ላይ ችግር እንደሌለ አስበው መልሰው ይተቹናል:: ከዚያም ራሳቸውን እንደ ተበዳይ  እኛን ደግሞ እንደ በዳይ አድርገው በሀሰት ያቀርባሉ::

በመርዛማ ሰዎች መጎዳት እንዳለ ሁሉ ከእስራት መላቀቅ እና ራስን ማዳንም አለ:: ከዚህ አዘቅት ውስጥ ለመውጣት በስሜት ሳይሆን በስልት መጓዝን ይጠይቃል:: የስነልቦና ምሁራን የሚያስቀምጧቸው ተግባራዊ መፍትሔዎች የሚከተሉት ናቸው::

ከንቱ ተስፋን መቁረጥ

የናርሲሲዝም  እና መርዛማ ባህሪያት ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ራማኒ ዱርቫሱላ ትልቁ የመፍትሔ እርምጃ “ሰውዬው ይለወጣል ብሎ ማሰብን ማቆም ነው” ይላሉ:: መርዛማ ሰዎች አይለወጡም፤ ምክንያቱም ችግር እንዳለባቸው አያምኑምና:: በመሆኑም እውነታውን እንዳለ መቀበል  የመዳን የመጀመሪያው እርምጃ ነው:: የማይለወጥን ሰው ለመለወጥ ከመሞከር ይልቅ ራስን መለወጥ ቀዳሚ መፍትሔው ነው::

የ”ግራጫ ድንጋይ” ስልት

በተለያዩ ምክንያቶች (ለምሳሌ የሥራ ባልደረባ ወይም የቅርብ ቤተሰብ በመሆናቸው) ሙሉ ለሙሉ ከህይወታችሁ ማውጣት የማትችሏቸው መርዛማ ሰዎች ካሉ ይህ ስልት ወርቃማ ነው:: ግራጫ ድንጋይ ትኩረት አይስብም:: አሰልቺ ነው:: እናንተም ለመርዛማው ሰው ምንም ዓይነት ስሜታዊ ምላሽ አለመስጠትን ልመዱ:: ትኩረት አትስጡ:: ሲቆጡ አትቆጡ:: ሲያለቅሱ አትደናገጡ:: ጥያቄ ሲጠይቁ አጫጭር እና ደረቅ መልስ (አዎ፣ አይ፣ አላውቅም) ብቻ  ብላችሁ መልስ ስጡ:: መርዛማ ሰዎች የሚፈልጉት የእናንተን ስሜታዊ መረበሽ ስለሆነ ያንን ሲያጡ ራሳቸው ሰልችቷቸው ይርቋችኋል:: መልስ መስጠት ወደ እነሱ ወጥመድ እና የጥቃት ኢላማ መግባት ነው::

የማይታጠፍ የብረት ድንበር ማበጀት

ሄንሪ ክላውድ እና  ጆን ታውንሴንድ (ዶክተሮች)  ድንበሮች (Boundaries) በተሰኘው መጽሐፋቸው ድንበር ማለት የትኛው የእኔ ነው፤ የትኛው የሌላው ነው የሚለውን የምንለይበት አጥር መሆኑን ያስተምራሉ:: መርዛማ ሰዎች ድንበርን ይጠላሉ:: ነገር ግን ማንን እንደምታነጋግሩ፣ ምን ያህል ጊዜ እንደምታጠፉ እና ምን ዓይነት ቃላት እንደምትታገሱ መወሰን መብታችሁ ነው:: እምቢ ማለትን ልመዱ:: እምቢ ሙሉ ዓረፍተ ነገር ነው፤ ማብራሪያ አይፈልግም:: ድንበራችሁን ሲጥሱ ያለምንም ይሉኝታ ርቀታችሁን ጠብቁ::

የዲጂታል እና አካላዊ  ማጽዳት

አንዴ ከወሰናችሁ በኋላ ወደ ኋላ መመለስ የለም:: ስልካቸውን ብሎክ አድርጉ፣ ከማህበራዊ ሚዲያ (ሶሻል ሚዲያ) አጥፏቸው:: የጋራ ጓደኞቻችሁን ሳይቀር ለተወሰነ ጊዜ አግልሉ:: በስሜት እስክትጠነክሩ ድረስ ምንም ዓይነት የመረጃ ልውውጥ እንዳይኖር ማድረግ አስፈላጊ ነው:: ይህ ምንም ዓይነት ግንኙነት አለማድረግ ተብሎ የሚጠራው ህግ አእምሯችሁ ካለበት ሱስ እንዲላቀቅ ጊዜ ይሰጠዋል::

የጥፋተኝነት ስሜትን አሽቀንጥሮ መጣል

መርዛማን ሰው ከህይወት ማስወጣት ክፋት አይደለም፤ ራስን የማዳን የህልውና ጉዳይ እንጂ:: ጀልባዋ ስትሰጥም ቀዳዳውን መድፈን እንጂ አብሮ መስጠም ጀግንነት አይደለም:: ራሱን የሚወድ ሰው፣ ክብሩን የሚያውቅ ሰው፣ መርዛማ ሰዎችን በአቅራቢያው አያስጠጋም:: ነፍሳችሁ ውድ ናት፤ ጊዜያችሁ የማይተካ ሀብት ነው::

በመጨረሻም ማስተዋል ያለብን ትልቁ እውነት የገዛ ሕይወትዎ የአትክልት ስፍራ መሆኑን ነው:: በዚህ ስፍራ ላይ የሚያማምሩ አበቦች እንዲበቅሉ ከተፈለገ አረሞችን ነቅሎ መጣል የጭካኔ ተግባር ሳይሆን የቅንነት መግለጫ ነው:: መርዛማ ሰዎችን ‘አርቆ ማስቀመጥ’ ማለት ጥላቻን ማርገዝ ሳይሆን ለራስህ ያለህን ፍቅር በተግባር ማሳየት ነው::

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here