የጦርነት መዘዞች እና መውጫ መንገዶች

0
92

በዓለም ዙሪያ ጦርነት ሲነሳ ብዙ ጊዜ የምንሰማው ቁጥሮችን ነው:: ሺዎች ሞቱ፣ ሚሊዮኖች ተፈናቀሉ ወይም ተጎዱ  የሚለውን ነው:: በመሆኑም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከ30 እስከ 50 የሚደርሱ ግጭቶች እና ጦርነቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ:: በየዓመቱም በዓለም ላይ ከአንድ መቶ ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ያህል ሰዎች ውጊያ ላይ እያሉ ይሞታሉ::  ይህ ቁጥር በጦርነቱ ምክንያት በረሃብ፣ በበሽታ እና በሕክምና እጥረት የሚፈጠሩ የሞት ክስተቶችን ሳይጨምር ማለት ነው::

ይህንን እውነት በግልጽ ለማየት በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ያሉ ግጭቶችን እና ጦርነቶችን መመልከት በቂ ነው::

በአሁኑ ወቅት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት፣ የእስራኤል-ሃማስ ጦርነት፣ በሱዳን እና  በየመን እየተካሄዱ የሚገኙት የእርስ በእርስ ግጭቶች እና ጦርነቶች እንዲሁም  አሁን ላይ በሰፊው የዓለምን ትኩረት የሳበው እስራኤል እና አሜሪካ ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት በዋነኛነት ይጠቀሳሉ:: ታዲያ በእነዚህ ጦርነቶች እና ግጭቶች በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል:: ሚሊዮኖች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል:: የሀገራት ኢኮኖሚም ክፉኛ ደቋል::

የጎረቤት ሀገር የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በዓለም ላይ ትልቁን የሰብአዊ ቀውስ አስከትሏል:: ከሦስት ዓመት በፊት (እ.አ.አ በሚያዚያ 15፣ 2023) በሀገሪቱ ጦር ኃይሎች አዛዥ በጄኔራል አብዱል ፈታሕ ኣል-ቡርሃን  እና በሀገሪቱ ፈጥኖ ደራሽ  ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች መሪ መሀመድ ሐምዳን ደጋሎ (ሄመቲ) መካከል የተጀመረው ውጊያ አሁንም አልረገበም:: በጦርነቱ ሌሎች ሀገራት ጣልቃ በመግባት ለሁለቱም ወገኖች የገንዘብ እና ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጋቸው የንጹኃን ሱዳናዊያንን ሕይወት ማመሰቃቀሉን ቀጥሏል:: የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀው ጦርነቱ በዓለማችን የከፋ የተባለውን የሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል::

በጦርነቱ ምክንያት ስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሱዳናዊያን ተፈናቅለዋል:: ከአራት ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል:: 33 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች (ከጠቅላላው የሀገሪቱ ሕዝብ ሁለት ሦስተኛ ያህሉ) የሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል:: ከ21 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ለከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት ተዳርገዋል::

ዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ  የአደጋ ጊዜ ክትትል ከሰሞኑ ይፋ እንዳደረገው ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የቀጠለው ጦርነት ሱዳንን ለከፋ ሰብአዊ ቀውሶች በጣም የተጋለጠች ሀገር አድርጓታል:: በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ባደረሰው አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የሱዳን ውድቀት እየተፋጠነ መሆኑን ነው ያመላከተው::

እ.አ.አ በ2023 የሱዳን ጦርነት ከማገርሸቱ በፊትም ሀገሪቱ 15 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሕዝብ ለሰብዓዊ እርዳታ በመጋለጥ ከባድ ሰብአዊ ቀውስን ስታስተናግድ ነበር::  የሦስት ዓመታት ጦርነቱም  እነዚህን ሁኔታዎች በከፍተኛ ሁኔታ አባብሷል::

መረጃው እንዳመላከተው በጦርነቱ  ንጹሃን የግጭቱ ዋና ገፈት ቀማሽ ሆነዋል:: ጾታዊ ጥቃት በስፋት እየተስፋፋ ነው፤ የሁለቱም ወገኖች ተዋጊዎች በሲቪሎች እና በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ አዘውትረው ዒላማ ያደርጋሉ:: የሕጻናትን ለውጊያ  መመልመልም የተለመደ ሆኗል:: በጦርነቱ ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ሲገደሉ በሰላማዊ ሰዎች ላይ አሰቃቂ ጥቃቶች ተፈጽመዋል::

የአውሮፓ ሕብረት እና አባል ሀገራቱ ለሱዳን ከፍተኛ ሰብአዊ እርዳታ ለጋሽ ሲሆኑ በምግብ ስርጭት፣ በአመጋገብ፣ በጤና፣ በውኃ እና በሌሎች ችግር ባለባቸው አካባቢዎች እገዛ እያደረገ ነው:: ይሁን እንጂ የእርዳታ አቅርቦቱ በእርዳታ ሠራተኞች ላይ በሚደርሰው ጥቃት እና አስተዳደራዊ መሰናክሎች ምክንያት ሰብዓዊ አቅርቦቱ ተግዳሮት አጋጥሞታል::

በተመሳሳይ በየካቲት መጨረሻ (ዘንድሮ) እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ የጀመሩት ጥቃት ከመካከለኛው ምሥራቅ ባለፈ የመላውን ዓለም ኢኮኖሚ እያናጋው የሚገኘው ግጭት በአሁኑ ወቅት ዓለማችንን አጣብቂኝ ውስጥ ካስገቧት ፈተናዎች መካከል አንዱ ነው:: እስራኤል እና አሜሪካ  በመጀመሪያው ዙር ጥቃት የኢራን የበላይ መሪ የነበሩትን አያቶላ አሊ ኻሜኒን ጨምሮ ከ40 በላይ የኢራን ከፍተኛ መሪዎች እና የጦር መኮንኖች ተገድለዋል:: ኢራን በወሰደችው አጸፋዊ እርምጃም በእስራኤል እና  በባሕሬን፣ በኳታር እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶችን ሰንዝራለች:: በተጨማሪም ኢራን የዓለም ነዳጅ ንግድ ቁልፍ መተላለፊያ የሆነውን የሆርሙዝ ሰርጥን በመዝጋቷ እና አሜሪካም የባሕር ላይ እገዳ በመጣሏ በመላው ዓለም  የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል:: ይህም በአካባቢው ከተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ባለፈ በተለይ ታዳጊ ሀገራትን ክፉኛ እየፈተነ ነው::

የተኩስ አቁም ስምምነት፦ በፓኪስታን አደራዳሪነት እ.አ.አ ከሚያዝያ 8 ቀን 2026 ጀምሮ የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ ነበር:: የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሚያዝያ 21(2026) ተኩስ አቁሙ እንዲራዘም መወሰናቸውን አስታውቀዋል:: በተመሳሳይ በእስራኤል እና በኢራን በሚደገፈው ሄዝቦላህ መካከል የተጀመረው ግጭት ተባብሶ ቀጥሎ ነበር:: ችግሩን ለጊዜውም ቢሆን ለማቆም ታዲያ በአሜሪካ አደራዳሪነት ለ10 ቀናት የሚቆይ የተለዬ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጓል:: ቢሆንም ግን ጥቃቶች አልፎ አልፎ እየተስተዋሉ ነው::

ይህ የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት  ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ እያስከተለ ነው:: በኢራን ብቻ ከሦስት ሺህ 600 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ በሊባኖስ ደግሞ ከሁለት ሺህ 400 በላይ ሰዎች መሞታቸውን አልጀዚራ ዘግቧል:: በዘገባው እንደተመላከተው በሊባኖስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል:: ጦርነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ እና የጋዝ ዋጋ እንዲንር ያደረገ ሲሆን በኢራን ውስጥም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራቸውን እንዲያጡ አድርጓል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሁኑ ወቅት በፓኪስታን አደራዳሪነት በኢስላማባድ የሰላም ንግግር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም አሜሪካ የባሕር ላይ እገዳውን ለማንሳት ፈቃደኛ አለመሆኗ እና ኢራን በእገዳ ስር ንግግር ላለማድረግ መወሰኗ ሂደቱን አዝጋሚ አድርጎታል::

ሌላው ከፍተኛ ውድመት እና የሰብዓዊ ቀውስ እያደረሱ ከሚገኙ ጦርነቶች መካከል የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት አንዱ ነው:: ግምቶች እንደሚያመለክቱት በሩሲያ ከየካቲት 2022 (እ.አ.አ) ጀምሮ ወደ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የጦር ሜዳ ሰለባ ሆነዋል፤ ማለትም ተገድለዋል፣ ቆስለዋል ወይም ጠፍተዋል:: በ2026 መጀመሪያ ላይ የወጡ ሪፖርቶች ሩሲያ ለወታደራራዊ ተልዕኮ ለመመልመል ከምትችለው በላይ ብዙ ወታደሮችን እያጣች እንደሆነ ይጠቁማሉ:: በዩክሬን ደግሞ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የወታደራዊ ሰለባዎች ግምት እንደሚያሳየው በ2026 መጀመሪያ ላይ ብቻ ከአምስት መቶ ሺህ እስከ ስድስት መቶ ሺህ ሰዎች ሞተዋል፣ ቆስለዋል ወይም ጠፍተዋል::

የስትራቴጂክ እና የዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል (CSIS|) እንዳስታወቀው በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚደረገው የሰላም ድርድር ከሽፏል:: ሩሲያ የተኩስ አቁም ሐሳቦችን ውድቅ በማድረግ የዩክሬን ወታደሮች ከዶኔትስክ ግዛት እንዲወጡ ጠይቃለች::

ከጦርነት እና ግጭት እንዴት መውጣት ይቻላል?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላምን ጥሪ በማስመልከት በማሕበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ “ሰላም ለሰው ልጅ መልካም ራዕይ ብቻ ሳይሆን የተግባር ጥሪ ነው:: እያንዳንዳችን መለያየትን ማከም እና ሰላምን እና መግባባትን መቀበል እንችላለን:: ቤተሰቦቻችን እና ማሕበረሰባችን ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ልንጥር እንችላለን”፤ ይላል:: ታዲያ ድርጅቱ ግጭትን መከላከል፣ ሽምግልና፣ ሰላም ማስከበር፣ ሰላም ግንባታ እና ትጥቅ ማስፈታት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር መሠረታዊ ነጥቦች መሆናቸውን ይጠቅሳል::

ጦርነት በአብዛኛው ከፖለቲካ እና ከኃይል ፍላጎት የሚመነጭ በመሆኑ መፍትሄውም ከፖለቲካዊ ውይይት ይጀምራል:: በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረጉ የሰላም ንግግሮችም አስፈላጊ ናቸው::

ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው 70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ጦርነቶች በውይይት እና በስምምነት መንገድ እንጂ በጦር ኃይል አይቆሙም:: ነገር ግን ውይይቱ በእውነተኛ ፍላጎት ላይ ካልተመሠረተ ውጤት አያስገኝም::

ለስኬቱ ከወታደራዊ እርምጃ በዘለለ ዋና መንስኤዎችን ለመፍታት እና ሁሉንም የሚመለከታቸው አካላት በውይይት ውስጥ ማሳተፍን ያካትታል::

ሀገራት ተቃዋሚዎቻቸውን ከጠላትነት ወደ ተፎካካሪነት ማዋቀር የግጭቱን አዙሪት ለመስበር ይረዳል:: ይህ ከጸብ አጫሪነት መቆጠብን እና የተቃዋሚውን ወገን ባሕላዊ ዕሴቶች መረዳትን ይጨምራል::

ግፊት ወይም ጫና ማሳደርን ሌላው ሰላምን ለማስፈን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚያቀርበው ምክረ ሐሳብ ነው፤ ለአብነትም ሀገራት ላይ የሚጣል የኢኮኖሚ ገደብ (Sanctions) ወይም የፖለቲካ ግፊት አንዳንድ ጊዜ ጦርነትን ሊያቆም እንደሚችል ያነሳል:: በተመሳሳይ ፍትሕ እንዲኖር ማድረግ ድርጅቱ ያስቀመጠው የጦርነት ማቆሚያ ስልት ነው፤ ለምሳሌ የጦር ወንጀል ፈጻሚዎች ካልተጠየቁ ግፉ ይቀጥላል:: በመሆኑም ለዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግጋት ቁርጠኝነትን ማሳየት እና የጭካኔ ድርጊቶችን የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ አስፈላጊ ነው:: ፍትሕ መኖሩ ደግሞ ለሌሎች እንደ ማስጠንቀቂያ ይሆናል::

የኢኮኖሚ ሁኔታን ማሻሻል ሌላው መፍትሔ ነው፤ በአንድ ሀገር ውስጥ ድህነት፣ ሥራ አጥነት እና እኩልነት አለመኖር ግጭትን ያበረታታሉ:: በተቃራው ልማት ካለ ደግሞ ጦርነት እና ግጭት ይቀንሳል::

የድርጅቱ መረጃ እንደሚያመላክተው ጦርነትን ማቆም የሁሉንም ተሳትፎ ይጠይቃል፤ ከዚያ ባለፈም ከቃል ባሻገር ተግባራዊነት ወሳኝ ነው:: በመሆኑም ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ መንግሥታት እና ሕዝብ በአንድነት በመሥራት ለሰላም መስፈን ሊረባረቡ ይገባል::

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የሚያዚያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here