ጫናዎችን ተቋቁሞ የሕግ የበላይነትን አስከብሯል፤ የሙስና እና የማባበያ ገንዘቦችን ወደ ጎን በመተው ለሀገር እና ለሙያው ታምኗል፤ በሽጉጥ እና በዛቻ ሳይበገር ሜዳ ላይ ፍትህን አንግሷል፤ ሀገሩን ወክሎ በዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ መድረኮች ከ34 በላይ ሀገራት ተጉዟል፤ በኢትዮጵያ የዳኝነት ሙያ ሦስት ጊዜ ኮከብ ዳኛ የሆነ ብቸኛው ባለ ክብረወሰን ነው፡፡ በተጫዋቾች እና አሰልጣኞች የተከበረ፤ የተወደደ፣ ለሙያው የታመነ እና ያደረም ነው፡፡ ጨዋታዎችን በመምራት አቅሙ ሳቢያ እርሱ እንዲመራችው በክለቦች ከሚፈለጉ ቀዳሚ ዓለም አቀፍ ዳኞች አንዱ ነው፡፡ በስፖርት ሳይንስ በእግር ኳስ አሰልጣኝነት የሁለተኛ እና የሶስተኛ ዲግሪ (PhD) ባለቤትም ነው- ዓለም አቀፉ ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው (ዶክተር)፡፡
ዓለም አቀፉ ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው (ዶክተር) ባለፉት 25 ዓመታት እግር ኳሱን በዳኝነት አገልግሏል፡፡ ገና በሙሉ አቅሙ ላይ እያለ በድንገት ከዳኝነት ዓለም ራሱን ማግለሉን በቅርቡ አሳውቋል፡፡ የዓለም አቀፉ ዳኛ የስፖርት ህይወት የሚጀምረው በተወለደበት እና ባደገበት ባሕር ዳር ከተማ ነው፡፡ በልጅነቱ በሁሉም የስፖርት እንቅስቃሴዎች ላይ በንቃት ይሳተፍ እንደነበር ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ የስፖርት ክፍል ዝግጅት ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል፡፡
ትልቁ ህልሙም ስመጥር የእግር ኳስ ተጫዋች መሆን እንደነበር አስታውሶናል፡፡ ይህንን ህልሙን እውን ለማድረግ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ከ15 ዓመት በታች ቡድን ወስጥ ስልጠና ቢጀምርም ከቤተሰቦቹ ይሁንታን ባለማግኘቱ ከአንድ ዓመት በላይ መዝለቅ አልቻለም፡፡ ታዳጊው ኃይለየሱስ አንደኛው በር ሲዘገባት ሌላ በር ማንኳኳቱን ቀጠለ፡፡ በ1993 ዓ.ም በ16 ዓመቱ (የ10ኛ ክፍል ተማሪ እያለ) በባሕር ዳር ከተማ ሁለተኛ ደረጃ የዳኝነት ስልጠና በመውሰድ ማርሽ ቀያሪውን የዳኝነት ጉዞውን ጀመረ፡፡
በ1994 ዓ.ም ሕጋዊ ዳኛ በመሆን በባሕር ዳር ከተማ የ”ቢ” ቡድኖችን በማጫወት ሥራውን ጀምሯል፡፡ ሜዳ ላይ የነበረው አስደናቂ ብቃት በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልልቅ ቡድኖችን ለመምራት አስችሎታል፡፡ በ1998 ዓ.ም ደግሞ የፌደራል ዳኝነት ስልጠና ወስዷል፡፡ የፌዴራል ዳኛ ከሆነ በኋላ በድሬዳዋ በተካሄደው የመላው ኢትዮጵያ የፕሮጀክት ውድድር ላይ ረዳት ዳኛ ሆኖ ጨዋታዎችን መርቷል፡፡
በዚህ መድረክ በድፍረት “ዋና ዳኛ መሆን እፈልጋለሁ” ብሎ በመጠየቅ ውጥረት የበዛበትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት በመምራት በብቃት መወጣት ችሏል፡፡ ኃይለኢየሱስ (ዶክተር) ሕግን አጥብቆ የሚያከብር፣ በማንም የውጭ ጣልቃ ገብነት የማይመራ በመሆኑ በባሕር ዳር ከተማ ከነበሩት የወቅቱ የስፖርት አመራሮች ጋር ሊግባባ አልቻለም። በዚህም “ጉዳያችንን አያስፈጽምም”በሚል ቂም ተይዞበት ከየትኛውም ስፖርት ለአንድ ዓመት ታግዷል፡፡ አሻጥሩ ያንገሸገሸው ኃይለኢየሱስ (ዶክተር) በ1999 ዓ.ም መረጃውን ከባሕር ዳር ወደ ምዕራብ ጎጃም ዞን አዙሮ በመስራት ፈተናውን በጽናት አልፎታል፡፡ ይህ ጽናት እና ጥረት በመጨረሻ ዓለም አቀፍ ዳኛ እንዲሆኑ ምክንያት ሆኗል፡፡
በወቅቱ ረዳት ዳኛ ብቻ ሆኖ ይመደብ የነበረው ኃይለኢየሱስ (ዶክተር) ዋና ዳኛ ሆኖ የመስራት ፍላጎቱን ለኮሚቴዎች በድፍረት በመጠየቅ እድሉን አግኝቷል፡፡ ዋና ዳኛ ሆኖ ወደ ሜዳ በገባበት የመጀመርያው ወሳኝ ጨዋታም ብሄርን መሰረት ያደረገ ትንኮሳ የፈጠሩ ተጫዋቾች ያለምንም ፍርሃት በካርድ በመቅጣት ጨዋታውን በሰላም ማጠናቀቁን ያስታውሳል፡፡ በ1999 ዓ.ም አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ኦሜድላ ከመቻሬ ያደረጉትን ጨዋታ በመምራት ወደ ብሄራዊ ሊጉ የፕሮፌሽናል ዳኝነት ሥራን መጀመሩን ያስታውሳል፡፡
በ2003 ዓ.ም ኢትዮጵያ ቡና ዋንጫ የወሰደበትን የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ በብቃት መምራቱን ተከትሎ እና የፊፋን መስፈርቶች አሟልቶ በመገኘቱ በ2004 ዓ.ም የዓለም አቀፍ ዳኝነት ባጅን አግኝቷል፡፡ በዚሁ ዓመትም ረዳት ዳኛ በመሆን ወደ ሩዋንዳ አምርቷል፡፡ በውጭ ሀገራት ከመራቸው ጨዋታዎች መካከል በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ያንግ አፍሪካ ከግብፁ አልሃሊ ያደረጉትን ጨዋታ 60 ሺህ ሕዝብ በታደመበት ስታዲየም በሚያስደንቅ ብቃት መርቶታል፡፡
ይህን ጨዋታ ፈጽሞ እንደማይዘነጋው ዓለማቀፉ ዳኛ ይናገራል፡፡ በወቅቱ የጨዋታው ኮሚሽነር ውጤት ለማስቀየር ያቀረቡላቸውን ዐስር ሺህ ዶላር ጉቦ ወደ ጎን በመተው እና ገንዘቡን በመናቅ ጨዋታውን በፍትሀዊነት በመምራት የሀገራችንን ስም አስጠርቷል፡፡ በሀገር ውስጥም ቢሆን መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ለዋንጫ ሲጫወቱ ኮከብ ተጫዋቾችን በቀይ ካርድ ሲያስወጣ በሽጉጥ የታጀበ የሞት ዛቻ ቢሰነዘርበትም ሕግን ከማስከበር ወደ ኋላ አላለም፡፡ ዓለማቀፉ ዳኛ ኃይለኢየሱስ ባዘዘው (ዶክተር) የሸገር ደርቢዎችንም ሆነ ሌሎች ከባድ ደርቢዎችን (እንደ አዋሳ ከሲዳማ፣ ወላይታ ከአርባምንጭ) ያለአንዳች ፍርሃት በተረጋጋ ስነልቦና መምራቱ አይዘነጋም፡፡
በሀገር ውስጥ ፕሪሚየር ሊጉ በዲኤስቲቪ መተላለፍ ከጀመረ ወዲህ 75 ጨዋታዎችን በአጠቃላይ ደግሞ እስከ 300 ጨዋታዎችን መርቷል፡፡ አጠቃላይ ከሀገር ውጪ ከ34 በላይ ሀገራትን በማዳረስ ከ16 በላይ ዓለም አቀፍ የካፍ ጨዋታዎችን እንዲሁም በአራት የተለያዩ የሴካፋ ውድድሮች ላይ 16 ጨዋታዎችን በዋና ዳኝነት መርቷል፡፡
ኃይለኢየሱስ (ዶክተር) በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ውስጥ ሦስት ጊዜ የዓመቱ ኮከብ ዋና ዳኛ ተብሎ የተሸለመ ብቸኛው ዳኛ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የኮከብ ዳኛ ሽልማትን በ2004 ዓ.ም አግኝቷል፡፡ በ2007 ዓ.ም እና በ2015 ዓ.ም የፕሪሚየር ሊጉ የዓመቱ ኮከብ ዳኛ በመሆን ሽልማት አግኝቷል፡፡ ከሚዲያ አካላት እና ከከተማ አስተዳደር አጠቃላይ አምስት የዋንጫ ሽልማቶችን ሰብስቧል፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃም ስኬታማ እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሚባሉ ዳኞች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይቀመጣል፡፡
በእግር ኳስ አሰልጣኝነት (Football Coaching) የሁለተኛ እና የሶስተኛ ዲግሪ (PhD) ባለቤት መሆኑ እግር ኳስ የሚፈልገውን የፊዚካል፣ ታክቲካል እና ሳይኮሎጂካል ፍላጎት ጠንቅቆ እንዲያውቅ ረድቶታል፡፡ የተጋጣሚዎችን አሰላለፍ ለማንበብ፣ የጥፋት ዞኖችን ለመገመት እና ራሱን በስነ ልቦና ለማዘጋጀት ትምህርቱ ትልቅ ድልድይ ሆኖለታል፡፡ የእግር ኳስ አካላዊ ንክኪን በሕጉ መሰረት የሚፈቅደው ዓለም አቀፉ ዳኛ የስነ ልቦና እውቀቱ በሜዳ ላይ ከማንም ተጫዋች ጋር እንዳይጋጭ ረድቶታል፡፡ በ25 ዓመታት የዳኝነት ዘመኑ ከአንድ ተጫዋች በስተቀር አላስፈላጊ የቃላት ልውውጥ አድርጎ አያውቅም፡፡ ይህ የተረጋጋ እና የሰለጠነ ስብዕናው ለስኬቱ ትልቅ መሰረት ሆኖታል፡፡
ለስፖርቱ ያደረ፣ ታታሪ፣ እና ለሙያው ያለው ፍላጎት እና ፍቅር ለወጣት ዳኞች አርአያ እንደሚሆንም በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ይሁን እንጂ ተገቢውን ጤናማ የሥራ አካባቢ ማግኘት ባለመቻሉ አሁን ላይ ከእግር ኳስ ዳኝነት ስራው ራሱን አግልሏል፡፡ እግር ኳሱን ከሚመሩ አካላት ጋር በተፈጠረ ችግር እና ችግሩን በውይይት መፍታት ባልተቻለ የአሰራር አለመግባባት ገና በ41 ዓመቱ በድንገት የዳኝነት ፊሽካውን ለመስቀል ተገዷል፡፡ የሕግ ሂደትን ተከትሎ ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ የሕግ የበላይነትን አሳልፎ ላለመስጠት ሲል ሜዳውን በክብር ለቋል፡፡
[5/4/26 2:18 PM] ስንቄ አያሌዉ: ገና ብዙ መሥራት በሚያስችለው ዕድሜ ላይ የሚገኘው ዓለማቀፉ ዳኛ ዛሬም የማይደበዝዝ ተስፋ እና ዕቅድ አለው፡፡ ምንም እንኳ ዳግም ፊሽካ ይዞ ወደ ሜዳ ባይገባም ስፖርቱን ግን እንደማይተወው ለአሚኮ በኩር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ተናግሯል፡፡ በቀጣይ በካፍ እና በፊፋ የኢንስትራክተርነት (አሰልጣኝነት) ስልጠናዎችን በመውሰድ አዳዲስ እና ብቁ ዳኞችን ለማፍራት አልሟል፡፡ ልክ እንደ እርሱ ለሕግ የሚገዙ፣ የማይደራደሩ እና ብቃት ያላቸውን ዳኞች በማብቃት የሚጠበቅበትን እንደሚወጣም ተናሯል፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የሚያዚያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


