ማራቶን ከሁለት ሰዓት በታች!

0
55

የ2026 የለንደን ማራቶን የሰው ልጅ በአካል ብቃት ሊደርስበት የሚችለውን ጣሪያ የፈተነ፣ የሽርፍራፊ ሴኮንዶችን ዋጋ በወርቅ ሚዛን ያስቀመጠ እና በታሪክ መዝገብ በደማቅ ቀለም የተጻፈበት ሆኖ አልፏል፡፡ በታላላቅ አትሌቶች ትንቅንቅ የታጀበው የ2026 የለንደን ማራቶን የምሥራቅ አፍሪካውያን እልህ አስጨራሽ ትግል የታየበት ልዩ ክስተት ነበር፡፡

የፕላቲኒየም ደረጃ በተሰጠው በዚህ ግዙፍ የማራቶን ውድድር ኬኒያዊው አትሌት ሰባስቲያን ሳዌ፣  ኢትዮጵያዊው ዮሚፍ ቀጀልቻ እና ኡጋንዳዊው ያቆብ ኪፕሊም ተከታትለው በመግባት በወንዶች ማራቶን የዓለም ክብረወሰንን ሰብረዋል፡፡ ሳዌ እና ዮሚፍ  የማራቶን ውድድርን ከሁለት ሰዓት በታች በመግባት በዘርፉ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል፡፡ ውድድሩን በበላይነት ያጠናቀቀው ሳዌ 42 ኪሎ ሜትሩን ለመጨረስ የፈጀበት ጊዜ አንድ ሰዓት ከ59 ደቂቃ ከ30 ሴኮንድ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊው ዮሚፍ ደግሞ ከኬኒያዊው አትሌት በ11 ሴኮንዶች ብቻ በመዘግየት በማራቶን ታሪክ የዓለም ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝግብ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል፡፡ ኡጋንዳዊው ያቆብ ኪፕሊሞ ሁለት ሰዓት ከ28 ሴኮንድ በመጨረስ የዓለም ሦስተኛውን ፈጣን ሰዓት አስመዝግቧል፡፡ የወንዶች ማራቶን ክብረወሰን በኬኒያዊው አትሌት ኬልቪን ኪፕተም ተይዞ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ ኪልቪን በ2023 እ.አ.አ በቺካጎ ማራቶን ርቀቱን ለመጨረስ ሁለት ሰዓት ከ35 ሴኮንድ የፈጀበት ጊዜ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በዘንድሮው የለንደን ማራቶን በወንዶች ፉክክር  ሁለት አትሌቶች ከሁለት ሰዓት በታች መጨረሳቸው በአትሌቲክስ አፍቃሪዎች እና የስፖርት መገናኛ ብዙኃን ዘንድ የሠርክ ወግ  ሆኖ ሰንብቷል፡፡ የዓለም አትሌቲክስም በሩጫው ዓለም አዲስ ምዕራፍ መከፈቱን አብስሯል፡፡

በስፖርት ታሪክ ውስጥ ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች መሮጥ ከሰውነት አቅም በላይ የሆነ ፈፅሞ የማይታሰብ እና የማይቻል ነገር እንደሆነ ተቆጥሮ ነበር የቆየው፡፡ የረጅም ርቀት ሩጫ ባለሙያዎች እና የህክምና ሳይንቲስቶች ሳይቀሩ የሰው ልጅ የልብ ምት እና የጡንቻ ጥንካሬ ይህንን ታላቅ የፍጥነት እና የፅናት ፈተና ሊቋቋም እንደማይችል ለዓመታት ሲሞግቱ ኖረዋል::

ይህ ጠንካራ አስተሳሰብ ግን በዘመናዊ የስፖርት ልማት፣ በሳይንስ አስደናቂ እድገት እና በቴክኖሎጂ ድጋፍ ቀስ በቀስ ተሰብሯል፡፡ ኬንያዊው አትሌት ኤሊውድ ኪፕቾጌ ርቀቱን ከሁለት ሰዓት በታች ሲያጠናቅቅ የሰው ልጅ አቅም ገደብ እኛ የምናስበውን ያህል ውስን እንዳልሆነ ለዓለም በተግባር አሳይቷል፡፡ ይህ ሁሉ ግን በአንድ ጀንበር ወይም በአንድ ግለሰብ ተሰጥኦ ብቻ የተገኘ አልነበረም፤ ይልቁንም የበርካታ ውስብስብ ነገሮች ጥምረት መሆኑን የዓለም አትሌቲክስ አስገነዝቧል፡፡ የስፖርቱ ዓለም ይህንን ድንበር ለመሻገር የወሰደበት መንገድ እጅግ አስደናቂ እና የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ አቅም የሚፈትሽ ሆኖ እንዳለፈ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኢትዮጵያውያን፣ ኬኒያውያን እና ኡጋንዳውያን አትሌቶች ልምምዳቸውን በከፍተኛ ቦታዎች የሚያደርጉ መሆናቸው በማራቶን ስኬታማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዘመናዊ የሩጫ ጫማዎችም በማራቶን ውድድር አዲስ አብዮት ፈጥረዋል፤ እንደ ናይኪ ቫፖርፍላይ (Nike Vaporfly) ያሉ ጫማዎች ጉልበትን በመቆጠብ እና እርምጃን በመቀነስ አትሌቶች ፍጥነታቸውን እንዲጨምሩ ያደርጋቸዋል፡፡

ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች ለመጨረስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው ዘመናዊ የስፖርት ጫማዎች መፈብረክ እንደሆነ የዓለም አትሌቲክስ ያስነብባል፡፡ በተለይም በውስጣቸው የካርቦን ፕሌት እና ልዩ የሆነ ፎም የተገጠመላቸው ጫማዎች አትሌቱ መሬትን ረግጦ በሚነሳበት ጊዜ የሚያባክነውን ኃይል በመቆጠብ የእርምጃ ብቃትን በከፍተኛ ደረጃ ያሻሽላሉ፡፡

ይህ ቴክኖሎጂ አትሌቱ በእያንዳንዱ እርምጃ የሚያወጣውን ጉልበት በመቀነስ በተመሳሳይ ኃይል የበለጠ ፍጥነት እንዲያገኝ እና በጡንቻዎቹ ላይ የሚደርሰውን የጉዳት አደጋ በመቀነስ በሴኮንዶች ብቻ ሳይሆን በደቂቃዎች እንዲሻሻል አድርጎታል፡፡ ቴክኖሎጂው የአትሌቱን አቅም ባይተካውም ያለውን ኃይል ግን ያለብክነት እንዲጠቀም በማድረግ የሰው ልጅ የፍጥነት ገደብ  እንዲሰበር ትልቅ አሰተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ይሁን እንጂ ፍፁም የሆነ የሠውነት አቋም፣ በሳይንስ የታገዘ ልምምድ እና ዘመናዊ ጫማ ብቻውን አርባ ሁለት ኪሎ ሜትሮችን ሊያሸንፉ አይችሉም፡፡ እናም ማራቶን ከአካላዊ ጉልበት ባሻገር እጅግ ፈታኝ የሆነ ስነ ልቦና ውጊያ ያለበት ውድድር ጭምር ነው፡፡ ከሰላሳ እና አርባ ኪሎ ሜትሮች በኋላ የሠውነት የኃይል ክምችት ሲሟጠጥ ጡንቻዎች በህመም ሲተጣጠፉ እና አዕምሮ አቁም ብሎ ሲያዝ ያንን ለማሸነፍ የማይታይ ኃይል የሆነው የአእምሮ ጽናት ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ጊዜ በውድድሮች ላይ ሁለት ተመሳሳይ የአካል ብቃት ያላቸው አትሌቶች ሲገናኙ አሸናፊውን የሚወስነው  የውስጥ ጥንካሬ እና የአእምሮ ጽናት ነው፡፡

ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች መሮጥ የሰው ልጅ ብቻውን ያስመዘገበው ተአምር ቢመስልም ከጀርባው ግን ጥልቅ የሆኑ በርካታ ነገሮች  ይገኛሉ፡፡ የተፈጥሮ ዘረመል፣ ለአትሌቲክስ ምቹ የሆነ ሥፍራ፣ እጅግ የረቀቀ ስልጠና፣  አብዮት የፈጠሩ ዘመናዊ ጫማዎች፣ እንደ አለት የጠነከረ የአዕምሮ ጽናት እና ምቹ  የአየር ንብርት ሊኖር ይገባል፡፡  ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች መሮጥ የሰው ልጅ የችሎታ ማሳያ ብቻ ሳይሆን ስፖርት ከህክምና፣ ከምህንድስና እና ከስነ ልቦና ጋር ሲቀናጅ የማይቻል የሚመስለውን ገደብ እንዴት መሻገር እንደሚቻል ለዓለም ያረጋገጠበት ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡ የሰው ልጅ ድንበር የት ነው? የሚለው ጥያቄ ምናልባትም መቼም መልስ የማያገኝ እና እየሰፋ የሚሄድ መሆኑን የ2026ቱ የለንደን የወንዶች ማራቶን አስተምሮናል፡፡

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሚያዚያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here