አልበርት አንስታይን አንድ ድንቅ አባባል አለው። “በእውነታው ከሚደርስብን ይልቅ በምናብ የምንሰቃየው ይበልጣል” አለ።
አውቀንም ይሁን ሳናውቀው የተሸናፊነት እና ተሳዳጅነት ስሜት ውስጣችን ይፈጠራል። ይህ ስሜት ውሎ አድሮ ራሳችንን ከጥቃት ለመከላከል በበቀል እና ቁርሾ እንድንነሳ ሊያደርገን ይችላል። ስሜቱ በውስጥ ራሳችንን ጎድቶ ሲያበቃ ሰዎችን ወደ መጉዳት ያድጋል። ለዚህ ነው የተጎዱ ሰዎች በብዛት የመጉዳት ዕድላቸው ከፍ የሚለው።
አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ። በህይወታችሁ ውስጥ ነገሮች ባልተጠበቀ ሁኔታ ሲበላሹ፣ ሲከሽፉ ወይም ግባችሁ ሳይመታ ሲቀር ጣታችሁ ወዲያውኑ ወደ ማን ይሄዳል? ወደ አለቃችሁ? ወደ መንግሥት? ወደ ኢኮኖሚው? ወይስ ወደ ወላጆቻችሁ?
“እኔን ሰው ይበድለኛል፣ ዓለም በሙሉ ፊቷን አዙራብኛለች፣ ዕድሌ የተረገመ ነው” ብላችሁ በምሬት የምታምኑ ከሆነ ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ። ራሳችሁ ውስጥ እስር ቤት ሰርታችሁ ራሳችሁን ቆልፋችኋል። ከውስጣችሁ የሚጨስ የተሸናፊነት እሳት አለ።
ዛሬ ስለ አንድ አደገኛ የአስተሳሰብ ቫይረስ እናነሳለን። ይህ ቫይረስ ህልሞችን የሚበላ፣ እድገትን የሚያቀጭጭ እና ሰውን የራሱ ህይወት ታዛቢ ብቻ የሚያደርግ የተጎጅነት እሳቤ ይባላል።
የስነ-ልቦና ባለሙያዎች ይህንን ክስተት “የተማረ አቅመ-ቢስነት” (Learned Helplessness) ከሚባል ስርአት ጋር ያያይዙታል። አንድ ሰው ለራሱ ችግሮች፣ ውድቀቶች፣ እና የህይወት መሰናክሎች ሁሉ ተጠያቂው ውጫዊ አካል (ሰዎች፣ ዕድል፣ አካባቢ፣ መንግሥት፣ቤተሰብ፣ የትዳር አጋር) ነው ብሎ የሚያምንበት የአስተሳሰብ ዘይቤ ነው።
ይህ እሳቤ ሲያይል ግለሰቡ “የእኔ ህይወት በእጄ አይደለም፤ እኔ የህይወት አውሎ ነፋስ እንደሚያዝዘው ቅጠል ነው” ብሎ በጽኑ ያምናል። ይህ አስተሳሰብ ለግለሰቡ ምቹ ይመስላል። ምክንያቱም ለውድቀቱ ተጠያቂው እሱ ስላልሆነ የጥፋተኝነት ስሜት አይሰማውም፤ ለድህነቱ፣ ለውድቀቱ፣ ለችግሩ ሁሉ ኀላፊነት የሚወስዱት ውጫዊ አካላት ናቸው። ነገር ግን ዋጋው እጅግ ውድ ነው። የሚገርመው እነዚህ ሰዎች ትንሽ ስኬት መሳይ ውጤት ሲያገኙ ዋንጫውን ለመጨበጥ የሚሽቀዳደሙ ናቸው። ችግሩ ሲሰናከሉ ነው። ያን ጊዜ ሌሎችን ይረግማሉ። ይህ አስተሳሰብ የሰው ልጅን የማሰብ፣ የመፍጠር እና የመለወጥ አቅም የሚገድብ የብረት ሰንሰለት ነው።
አንድ ሰው የዚህ ችግር ተጠቂ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች አሉ። የመጀመሪያው ሃላፊነትን መሸሽ ነው። ለተፈጠረ ችግር መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ይህ የሆነው እኮ በአንተ/በእነሱ ምክንያት ነው የሚል ሰበብ መደርደር ይቀናቸዋል።
ሁለተኛው የማያቋርጥ ማማረር ነው። ችግር ሲያጋጥም መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ችግሩን ለሌሎች በመንገር የሰውን ርህራሄ መፈለግ የእነዚህ ሰዎች መገለጫ ነው። ተበዳይ ሆነው በሄዱበት ሁሉ ታሪካቸውን ያወራሉ። ራሳቸውን ከጥፋት ነጻ አድርገው ያቀርባሉ።
ሦስተኛው ምልክት ከመጠን ያለፈ ምቀኝነት አለባቸው። ሌሎች ሲሳካላቸው “እነሱ እኮ እድለኛ ናቸው” ወይም “ያገኙት ዘርፈው ነው ወይም ሀብታም ቤተሰብ ስላላቸው ነው” በማለት ስኬታቸውን ማሳነስ ይወዳሉ።
አራተኛው መገለጫ እነዚህ ሰዎች በቁጣ የተሞሉ ናቸው። ዓለም ለእኔ ክፉ ናት የሚል ስሜት ስላቸው ለትንሽ ነገር መቆጣት እና መበሳጨትን ይመርጣሉ።
አምስተኛው “ለምን እኔ ብቻ?” የሚል ጥያቄ ውስጣቸው አለባቸው። ሁልጊዜ ችግሮች በእነሱ ላይ ብቻ እንደሚደርሱ ነው የሚያስቡት። ጦርነቱ በእነሱ ላይ ብቻ፣ ኢኮኖሚው እነሱን ለማጥቃት፣ የትምህርት ስርዓቱ የእነሱን ልጆች ለማሰናከል የተነሳ ይመስላቸዋል።
ስቴቨን ኮቪ የስኬታማ ሰዎች ሰባቱ ልማዶች በሚለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት የተጎጅነት እሳቤ የሰውን የኃላፊነት ተጽእኖ ያጠባል፡፡ የማደግ ዕድልን ይዘጋል። እኔ ተጎጂ ነኝ ካልን ለመሻሻል አንሞክርም። ስህተት የሌለበት ሰው ከስህተቱ መማር አይችልምና። ማህበራዊ መገለልም ይፈጥራል። ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ ሊያዝኑልን ይችላሉ፤ ነገር ግን ዘወትር አማራሪ እና ተጎጂ መስሎ የሚታይን ሰው ማንም አብሮት መሆን አይፈልግም። እነዚህ ሰዎች ስሜታዊ መታወክ ይገጥማቸዋል። የማያቋርጥ የጭንቀት፣ የቁጣ እና የብቸኝነት ስሜት ያሳድዳቸዋል። ማሰብ ለሚከብዳቸው የራሳቸውን ህይወት ኀላፊነት ለሌላ ሰው አሳልፈው ይሰጣሉ።
ምርምሮች እንደሚያሳዩት አንዳንዶች ይህንን አስተሳሰብ እንደ መከላከያ ጋሻ (Defense Mechanism) ይጠቀሙበታል። ከባድ የስነ-ልቦና ቀውስ የደረሰባቸው ሰዎች እንደገና እንዳይጎዱ በመስጋት “እኔ ምንም ማድረግ አልችልም፤ ሁሉ ነገር በሰው እጅ ነው” ብለው ራሳቸውን ያሳምኑታል። ሌላው ምክንያት ደግሞ ከህፃንነት ጀምሮ በቤተሰብ ዘንድ የሚሰጠው “ሁሉ ነገር ይደረግልህ” የሚል ልማድ ትልቅ ሰው ሲሆኑም ማህበረሰቡ እንዲንከባከባቸው እንዲጠብቁ ያደርጋቸዋል።
ከዚህ የተሸናፊነት እና ተሳዳጅነት እሳቤ መውጣት ይቻላል።
ቀዳሚው ዘዴ ቋንቋዎን መቀየር ነው። ከ “ለምን እኔ?” ወደ “አሁን ምን ማድረግ እችላለሁ?” አስተሳሰብ መለወጥ ያሻል።
የቁጥጥር ቦታን መቀየር ቀጥሎ የሚመጣው መላ ነው። ነገሮች በእርስዎ እጅ እንደሆኑ ማመን ይጀምሩ። “ይህ ችግር ተፈጠረ፣ ታዲያ እኔ ምን ላድርግ?” ብለው ራስዎን ይጠይቁ። ለራስዎ ሕይወት ኀላፊነትን ይውሰዱ።
አነስተኛ ድሎችን ማስመዝገብ ለትልቁ ጉዳይ ያዘጋጀናል። ትናንሽ ሃላፊነቶችን መውሰድ ይጀምሩ። ሃላፊነት ሲወስዱ የመቆጣጠር ስሜትዎ ይመለሳል። ቢያደርጉልኝ ከሚል እኔ ማድረግ እችላለሁ ወደ ሚል እሳቤ ያድጋሉ።
ህይወት ስፍር የለውም። የትኛው ትንሽ እና የትኛው ብዙ እና በቂ እንደሆነ አልሰፈርነውም። አንጻራዊ ነው። ስለዚህ አሁን በእጃችን በያዝነው መደሰት እና ማመስገን ስንጀምር ውስጣችን ይጠግባል። ለያዝነው ነገር ዋጋ መስጠት እንጀምራለን። መስፈሪያ በሌለው እና በማይሞላ የሰው ልጅ ፍላጎት ዓለም ካጎደለን ይልቅ ያለን ነገር ይበልጣልና ማመስገን መዳኛው መንገድ ነው።
የስነ-ልቦና ባለሙያው ቪክቶር ፍራንክል በናዚ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ተጥለው ነበር። ቤተሰቦቻቸው ተገድለዋል፣ ተርበዋል፣ ተሰቃይተዋል። የሰው ልጅ ትርጉም ፍለጋ (Man’s Search for Meaning) በሚለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ አሉ።
“በሰው ልጅ ላይ ሊወሰዱ ከማይችሉት ነገሮች ሁሉ የመጨረሻዋ ነጻነት ናት። በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የራስን አመለካከት የመምረጥ ነጻነት” ሀሳባቸውን የመምረጥ ነጻነት አልተወሰደባቸውም።
ፍራንክል ተጎጂ እንደሆኑ ማሰብን ቢመርጡ ኖሮ በዛው ካምፕ ውስጥ በጭንቀት ይሞቱ ነበር። ነገር ግን፣ “ይህ መከራ ለአንድ ዓላማ ነው” ብለው በመወሰናቸው በህይወት ተርፈው ዓለምን ቀይረዋል። አሜሪካዊው ስኬታማ ነጋዴ ቶኒ ሮቢንስ እንደሚለው “ህይወት የሚሆነው በራሱ አይደለም፤ ህይወት የሚሆነው በእርስዎ አማካኝነት ነው።”
ሁሉም ሰው የህይወቱ ጸሐፊ እንጂ የሁኔታዎች ሰለባ አይደለም። ጣትን ከሰዎች ላይ አንስቶ ወደ ራስ ሲያመልከቱ የእውነተኛ ነጻነት በር ይከፈታል።
ዛሬውኑ ይወስኑ። ተጎጂ ሆነው መቅረት ይፈልጋሉ ወይስ የህይወትዎ ጌታ መሆን? መከራዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን እነዚያ መከራዎች እርስዎ ማን እንደሆኑ እንዲወስኑ መፍቀድ የለብዎትም። የእርስዎ ምርጫ የእርስዎ ህይወት ነው። ዛሬውኑ የኃላፊነት ካባዎን ይልበሱ!::
(አቢብ ዓለሜ)
በኲር የሚያዚያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


