በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከ260 እስከ 340 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ከአስም በሽታ ጋር ይታገላሉ:: በቀጣይ ዓመታት ከከተሜነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ እና በአየር ብክለት የአስም ተጋላጭ ዜጎች ቁጥር 400 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል:: በየዓመቱ ከአስም ጋር በተያያዘ 450ሺህ ሰዎች ሕይዎታቸውን እንደሚያጡም መረጃው አመላክቷል::
በአብዛኛው በአስም በሽታ የሚከሰተውን ሞት ትክክለኛውን መድኃኒት በመጠቀም ማስቀረት እንደሚቻል ግሎባል ኢንሼቲቭ ፎር አስም (የአስም በሽታን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና ለማከም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርግ ድርጅት) መረጃ አስነብቧል:: መረጃው 90 በመቶ የሚሆነው በአስም ምክንያት የሚከሰተው ሞት በታዳጊ ሀገራት መሆኑንም ጠቁሟል::
አስም ምንድን ነው?
አስም በማንኛውም እድሜ ላይ የሚከሰት በሽታ ነው:: አስም የአየር (የመተንፈሻ) ቧንቧ ላይ ችግር የሚፈጥር በሽታ ነው:: አስም የሚከሰተው የመተንፈሻ ቱቦ ሲቆጣ፣ ሲያብጥ ወይም በተለያዩ ባእድ ነገሮች( ፈንገስ፣ ባክቴሪያ ወይም ቫይረስ) ሲዘጋ ነው:: በዚህ ጊዜ ቱቦው አየር በተገቢው መንገድ ማስተላለፍ ስለሚሳነው ግለሰቡ ለመተንፈስ ይቸገራል:: አስምን በሕክምና ፈጽሞ ማዳን እንደማይቻልም መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ይሁንና በአስም ምክንያት የሚከሰተውን የመተንፈሻ ቧንቧን መጥበብ እና መቆጣት በሕክምና ማከም እንደሚቻል የዓለም ጤና ድርጅት ላይ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል::
ለአስም አጋላጭ ምክንያቶች
አስም ተላላፊ በሽታ አይደለም:: ነግር ግን አስም በዘረመል ወይም በቤተሰብ ሊተላለፍ ይችላል:: ማለትም እናት ወይም አባት የአስም በሽታ ካለባቸው ልጅ የመያዝ አጋጣሚ ሊኖረው ይችላል:: እንደ ድመት ወይም ውሻ ያሉ የቤት እንስሳት የጸጉር ብናኞች እንዲሁም መጥፎ እና ጥሩ ሽታዎችም አስምን ሊያስነሱ ወይም ሊያባብሱ ይችላሉ:: ፋብሪካዎች የሚያመርቷቸው የተለያዩ ኬሚካሎች፣ የጥጥ ብናኞች… ለአስም በሽታ የማጋለጥ አጋጣሚያቸው የሰፋ ነው::
በተጨማሪም የአየር ብክለት (Airpolution)ለአስም በሽታ አንዱ አጋላጭ መንስኤ ነው:: ሲጋራ ማጨስ በአጫሹም ሆነ በአጫሹ ተጋላጪ በሆኑ ሰዎች ላይ አስምን ሊያሲዝ ወይም በፊት ያለባቸውን ሰዎች ሊያባብስባቸው ይችላል:: የመኪና ጭስ፣ ለምግብ ማብሰያ የሚውሉ ከሰል እና የማገዶ እንጨት ጭስ፣ የእጣን ጭስ፣ የአካባቢ ንጽሕና ጉድለት ያለበት አካባቢ ላይ የሚኖሩ ሰዎች በአስም የመያዝ አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው:: ሽቶ ወይም አቧራም አስምን ሊቀሰቅስ ይችላል:: ከልክ በላይ ጭንቀት፣ ኬሚካሎች በሚበዙበት ቦታ መሥራት፣ የአለርጂ ህመም…ለአስም አባባሽ ናቸው::
ምልክቶቹ
ምልክቶቹ ከቀላል እስከ ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ:: አብዛኛውን ጊዜ ረዥም ጊዜ የቆየ ሳል የያዛቸው ሰዎች የሳንባ ምች ነው ተብለው መድሃኒት ሊወስዱ ይችላል:: እንዲሁም የሳንባ ነቀርሳ ነው ተብለው እንዲሁ ታክመው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ለውጥ ከሌለው ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ሳል የአስም ምልክት መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ አመላክቷል::
በጉንፋን ምክንያት የሚባባስ ሳል ይኖራል::የአስም ሳል አክታ ሊኖረውም ላይኖረውም የሚችል ሲሆን ብዙ ጊዜ ግን ደረቅ ሳል ነው:: ሳሉ አክታ ካለው አብሮ የሳንባ ምች የመኖሩ አጋጣሚ ሰፊ ነው:: ትንፋሽ ማጠር ሌላው የአስም ምልክት ነው:: በትንፋሽ ማጠር ምክንያትም እንቅልፋ ማጣት ይኖራል::
ቀላል የሆኑ ሥራዎችን በሚያከናውኑበት ጊዜ ሳይቀር አየር ሊያጥረዎት ይችላል:: ከባድ አስም ከሆነ ደግሞ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ትንፋሽ ሊያጥር ይችላል:: ትኩሳት ተጨማሪ የሳንባ ኢንፌክሽን እንዳለ ሊያመላክት ይችላል::
ሌላው የአስም በሽታ ምልክት የደረት መያዝ ወይም ሲተነፍሱ የመውጋት ስሜት ነው:: ሲተነፍሱ ሲር ሲር የሚል ድምጽ ይኖረዋል:: ከኦክስጅን ማነስ ጋር ተያይዞ የሰውነት ድካም ሊኖር እንደሚችልም መረጃው አመላክቷል::
ሕክምናዎቹ እና መከላከያዎቹ
ምልክቶቹ የታዩበት አንድ ሰው ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ የሳንባን የጤና ሁኔታ ለማወቅ የሚረዱ የተለያዩ የደም እና የራጅ ምርመራ ሊያደርግ ይችላል:: ይህም ምርመራ በአስም ምክንያት ነው? ወይስ በሌላ ምክንያት የመጣ ነው? የሚለውን ለማወቅ ያስችላል::
መረጃው እንደጠቆመው አስም ሙሉ በሙሉ ሊድን አይችልም፤ ሆኖም ግን የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል መቆጣጠር ይቻላል:: ይህ ሲባል አለርጂዎችን ከሚያባብሱ ነገሮች ማለትም ከጭስ፣ ከአቧራ፣ የራስን እና የአካባቢ ንጽሕናን በመጠበቅ፣ ከድመት እና ከውሻ ራስን በማራቅ፣ጉንፋን ከያዘው ሰው ጋር ባለመሆን፣ ከፋብሪካዎች ከሚወጡ ኬሚካሎች እና ጭሶች መጠበቅ እና የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር ተገቢ ነው:: ምክንያቱም ከመጠን በላይ ክብደት ያላቸው ሰዎች የአየር ቧንቧ ጥበት ስለሚያጋጥማቸው ለአስም የመጋለጥ አጋጣሚ ሊኖራቸው ይችላል:: የፍራሽ እና አንሶላ ንጽሕናን መጠበቅ፣ ከሽቶ ፣ ከቀለም መራቅ እና የአካል እንቅስቃሴ ማዘውተርም ይመከራል::
የአስም መድኃኒቶችን በሐኪም ትዛዝ በአግባቡ መውሰድ ይመከራል:: አስም ላለባቸው ሰዎች የማይሰጡ መድኃኒቶች ስላሉ ለማንኛውም የጤና እክል ለማዳን የሚሰጥ መድኃኒትን ከባለሙያ ጋር ተመካክሮ መውሰድ ተገቢ ነው:: “የታዘዘልኝ መድኃኒት ከአስሜ ጋር ይሄዳል ወይ? አስሜን አያባብሰውም ወይ?“ የሚሉትን ጥያቄዎች ሐኪም ጠይቆ መውሰድ ይመከራል::
የተዘረዘሩት የአስም በሽታ ምልክቶች ሲያጋጥሙ እና ሐኪም ያዘዘውን መድኃኒት ወስዳችሁ ካልተሻላችሁ እንዲሁም ጥፍር እና ከንፈራችሁ ከጠቆረ፣ ያልተለመደ ድካም እና ራስ ማዞር የሚሰማችሁ ከሆነ ቶሎ ወደ ሕክምና ተቋማት መሄድ ይኖርባችኋል::
መረጃ
የአሜሪካ የሳንባ አሶሴሽን እንደገለጸው የደረቁ ፍራፍሬዎች፣ ወይን፣ በፋብሪካ ተዘጋጅተው የሚሸጡ ጭማቂዎች እና የተቀናበሩ ምግቦች የአየር ቧንቧ መተላለፊያን ስርዓት ሊያውኩ ይችላሉ::
እንደ አፕል፣ ብሩቱካን፣ ካሮት ቆስጣ አንቲኦክሲዳንት (ቫይታሚን ሲ እና ቤታካሮቲን) ስለያዙ የአየር መተላለፊያ መቆጣትን ይከላከላሉ:: በመሆኑም አስም ያለበት ሰው አዘውትሮ ቢመገባቸው ይመከራል:: በተጨማሪም በኦሜጋ ሦስት እና በማግኒዥየም የበለጸጉ ምግቦችንም ቢመገቡ ጥሩ ነው::
የአሜሪካ የአስም እና አለርጂ ፋውንዴሽን ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ለአንዳንድ ሰዎች የወተት ምርቶች(ወተት ፣አይብ እና ቅቤ) የአየር ቧንቧ መታፈንን ሊያመጡ ይችላሉ:: በዘይት የተጠበሱ እና ማጣፈጫ የተደረገባቸው ምግቦች፣ አልኮል፣ የቀዘቀዙ ማንኛውም መጠጦች አስምን ሊቀሰቅሱ ስለሚችሉ ባይመገቧቸው ይመረጣል::
(ሳባ ሙሉጌታ)
በኲር የሚያዚያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


