በዓለም አቀፍ ደረጃ የስም አወጣጥ ባህሎች እና ልማዶች ከሀገር ሀገር፣ ከባህል ባህል እንዲሁም ከሀይማኖት ሀይማኖት በእጅጉ ይለያያሉ። ስም የአንድን ሰው ማንነት፣ የትውልድ ሐረግ፣ ታሪክ እና ማህበራዊ ትስስር የሚገልጽ ትልቅ ትርጉም ያለው መለያ ነው።
ስም “ሰመየ” ስም አወጣ፣ ጠራ፣ ለየ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ነው። ትርጓሜውም መጠሪያ፣ መለያ ማለት ነው፡፡ በዚህም ስም ማለት መጠሪያ፣ መለያ፣ አንድን አካል ከሌላው አካል የምንለይበት ሆኖ ያገለግላል።
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ስሞች በሁኔታ እና ምክንያት ይወጣሉ። ቴሶል ዓለም አቀፍ ማህበር ገጽ (TESOL International Association) ይህን ጉዳይ በስፋት ተመልክቶታል።
* የቤተሰብ ስም (Surname) ቅድሚያ የሚሰጥባቸው ባህሎች
በቻይና፣ ኮሪያ፣ ጃፓን እና ሌሎች የምስራቅ እስያ ሀገራት ሲጻፍም ሆነ ሲጠራ የቤተሰብ ስም ከግለሰቡ ስም ይቀድማል። በእነዚህ ባህሎች ከግለሰባዊነት ይልቅ ለቤተሰብ፣ ለትውልድ እና ለማህበረሰብ ትስስር ከፍተኛ ክብር ይሰጣል። ስለዚህም ግለሰቡ ከየትኛው ቤተሰብ እንደመጣ ለማሳየት የቤተሰብ ስም ቅድሚያ ይወስዳል።
* በአባት እና በእናት ስም ላይ የተመሰረቱ ስሞች በሩሲያ የስም አሰጣጥ ስርዓት እያንዳንዱ ሰው የግል ስም በአባቱ ስም ላይ የተመሰረተ መካከለኛ ስም እና የቤተሰብ ስም ይኖረዋል። መካከለኛው ስም ለወንድ “ኦቪች” ለሴት “ኦቭና” የሚል ቅጥያ ይኖረዋል (ለምሳሌ ኢቫኖቪች ማለት የኢቫን ልጅ ማለት ነው)። በሌላ በኩል በአይስላንድ ሀገር የቤተሰብ ስም የሚባል ነገር የለም፤ ከዛ ይልቅ የልጁ/ልጅቷ የመጨረሻ ስም የአባታቸው (አልፎ አልፎ የእናታቸው) የመጀመሪያ ስም ላይ ለወንድ “ሰን” ለሴት “ዶቲር” የሚል ቅጥያ በማድረግ ይወጣል። ይህም የትውልድ ሐረግን በትክክል ለማስቀመጥ እና አባትየውን/እናትየዋን ለማክበር ነው።
* ድርብ የቤተሰብ ስሞች
በስፔን እና በላቲን አሜሪካ ሀገራት አንድ ልጅ የግል ስሙን ይይዝና በመቀጠል ሁለት የመጨረሻ ስሞች ይሰጡታል፤ የመጀመሪያው የአባቱ የቤተሰብ ስም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የእናቱ የቤተሰብ ስም ነው። ይህም የሚሆነው ልጁ/ልጅቷ የሁለቱም ቤተሰቦች (የአባትም የእናትም) የዘር ግንድ ውጤት መሆኑን/መሆኗን እኩል እውቅና ለመስጠት እና የቤተሰብን ታሪክ ላለማጥፋት ነው።
* በኮከብ ቆጠራ፣ በእምነት እና በተወለዱበት ቀን ላይ የተመሰረቱ ስሞች
በህንድ የሂንዱ እምነት ተከታዮች የልጁን ስም የሚያወጡት በልደት ቀኑ እና ሰዓቱ ላይ ባለው የፕላኔቶች እና የከዋክብት አቀማመጥ (ራሺስ) ላይ ተመሥርተው ነው። በምዕራብ አፍሪካ፣ በተለይም በጋና ልጆች በተወለዱበት የሳምንቱ ቀን መሠረት ስም ይሰጣቸዋል። ለምሳሌ አርብ ለተወለደ ወንድ ‘ኮፊ’፣ ቅዳሜ ለተወለደ ‘ክዋሜ’ የሚል ስም ይሰጠዋል። ምክንያቱ እጣ ፈንታ፣ መንፈሳዊ ትስስር እና ሃይማኖታዊ እምነቶች በልጁ የወደፊት ህይወት ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ ያመጣሉ ተብሎ ስለሚታመን ነው።
- የትውልድ ሰንሰለትን የጠበቀ የስም አሰጣጥ
በብዙ የዓረብ ሀገራት እና እንደ ሶማሊያ ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የልጁ ሙሉ ስም የሚገነባው የራሱ ስም ሲደመር የአባት ስም ሲደመር የአያት ስም ሲደመር የቅድመ አያት ስም ወ.ዘ.ተ በመቀጠል ነው። በዓረብኛ “ቢን” ለወንድ ልጅ እና “ቢንት” ለሴት ልጅ በማስገባት ሰንሰለቱ ይቀጥላል። ምክንያቱ የጎሳ ትስስርን ለማሳየት እና ማህበራዊ መዋቅሩን ጠብቆ ለማቆየት ነው። በአፍጋኒስታንም ቢሆን የመጨረሻ ስሞች ከጎሳ፣ ከትውልድ ቦታ እና ከሙያ ጋር ተያይዘው ይወጣሉ።
በኢትዮጵያ ያለው የስም አወጣጥ ባህል ልዩ፣ ጥልቅ ትርጉም ያለው እና ከሀገሪቱ የረጅም ዘመን ታሪክ፣ ሀይማኖት፣ እንዲሁም የቋንቋ እና የብሔር ብዝኀነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው።
ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ሰምና ወርቅ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ ስነ-ማህበረሰብ አጥኚዎች የኢትዮጵያውያን ስም የቤተሰብን እምነት፣ ማህበራዊ ሁኔታ እና ፍልስፍና እንዴት አምቆ እንደያዘ ጽፈዋል።
በኢትዮጵያ እንደ ምዕራባውያን አገራት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የቤተሰብ ስም የለም። አብዛኛው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የሚጠቀመው “የግል ስም ሲደመር የአባት ስም ሲደመር የአያት ስም” በሚል ቅደም ተከተል ነው። ለምሳሌ የአንድ ሰው ስም “ሸጋው ዘመን ታደሰ” ቢሆን፤ ሸጋው የልጅ ስም፣ ዘመን የአባቱ ስም፣ ታደሰ የአያቱ ስም ይሆናል።
በኢትዮጵያ ልጆች ስም ሲወጣላቸው በአብዛኛው ከሚከተሉት ሶስት ምክንያቶች በአንዱ ላይ የተመሰረተ ነው።
ሃይማኖታዊ እና መንፈሳዊ ምክንያቶች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እና ካቶሊክ እምነት ተከታዮች ብዙውን ጊዜ ስማቸውን ከእግዚአብሔር፣ ከድንግል ማርያም፣ ከመላእክት እና ከቅዱሳን ጋር በማስተሳሰር ያወጣሉ። ለምሳሌ፡ “ገብረ ሚካኤል” (የሚካኤል አገልጋይ)፣ “ኃይለ ማርያም” (የማርያም ኃይል)፣ “ሰይፈ ሚካኤል” እያሉ ስም ያወጣሉ።
በተጨማሪም ልጆች ክርስትና ሲነሱ መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ብቻ የሚውል የክርስትና ስም ይሰጣቸዋል፤ በዕለት ከዕለት ህይወታቸው ግን “የዓለማዊ ስም” በሚባለው (ወላጆች ባወጡላቸው ስም) ይጠራሉ።
የእስልምና እምነት ተከታዮች ከነቢዩ መሐመድ ታሪክ፣ ከቁርአን እና ከአረብኛ ቃላት ጋር የተያያዙ መንፈሳዊ ስሞችን ያወጣሉ። ለምሳሌ መሐመድ፣ አህመድ፣ አብዱላሂ፣ ፋጡማ፣ ኑር ወ.ዘ.ተ እያሉ ይሰይማሉ።
ምክንያቱ ልጆች በአላህ ጥበቃ ስር እንዲያድጉ እና የእምነቱ በረከት እንዲጠብቃቸው በማሰብ ነው።
የቤተሰብ ስሜት፣ ምኞት እና የህይወት ገጠመኝ
ወላጆች ልጁ በሚወለድበት ወቅት ያላቸውን የደስታ፣ የምስጋና፣ የተስፋ ወይም የኀዘን ስሜት በልጁ ስም ይገልጻሉ። ስም እንደ ታሪክ ማስታወሻ ሆኖ ያገለግላል። “እናትህ በጣም ታማብኝ ነበር። በኋላ ለአንተ አባት ስድራት ጤናዋ ተመለሰ። ወዲያውም አረገዘች። አንተን ስትወልድ ለፈጣሪ ምን ይከፈለዋል ብዬ ‘ምንውዬለት’ አልሁህ” ስትል አያቴ እንዴት ስም እንዳወጣችልኝ ነግራኛለች።
ስሞች ብዙ ሀሳቦችን ይገልጻሉ። ተስፋ እና ደስታን ለመግለጽ ተስፋዬ፣ ደስታ፣ ፍሥሐ፣ ቢሆነኝ የሚሉ ስሞች ይወጣሉ። ምስጋናን ለመግለጽ ምስጋናው፣ ታደሰ፣ በረከት፣ ትሩፋት የሚሉ ስሞች ይሰጣሉ። ከችግር እና ትዕግስት በኋላ ለተወለደ ልጅ ካሳ፣ መከታ፣ ጽናት፣መታገስ የሚሉ ስሞች ይወጣሉ።
የእናቴ ስም አስረስ ነው። አያቴ ዘጠኝ ወንድ ወልዳለች። አዲት ሴት ስትወልድ በልጅነቷ ሞተች። አያቴ በዚያች ልጅ ክፋኛ ታዝን ነበር። ሴት ባለመውለዷ ውስጧ ይከፋል። የእኔ እናት ስትወለድ አያቴ ከደስታዋ ብዛት አስረስ አለቻት። ኀዘኔን አስረሳሽኝ ለማለት ነው።
የብሔር፣ የቋንቋ እና የባህል መገለጫ
ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች እና ቋንቋዎች ያሉባት ሀገር በመሆኗ ስሞች የዚያን ማህበረሰብ ቋንቋ፣ ጀግንነት፣ ወይም የተፈጥሮ ትስስር ይገልጻሉ።
በኦሮሞ ባህል የልጁን እድገት፣ ጥንካሬ ወይም የተወለደበትን ሁኔታ የሚገልጹ ስሞች በብዛት ይወጣሉ። ለምሳሌ ጫላ የበለጠ/ብልጫ ያለው፣ ጉዲና እድገት፣ ሌሊሳ የሚያብብ/የሚለመልም ማለት ነው። በትግራይ ሓዱሽ አዲስ፣ ጽጌ አበባ፣ ሓየሎም ሀይለኛ ማለት ነው።
በሌሎችም የደቡብ፣ የሶማሌ፣ የአፋር ወ.ዘ.ተ ማህበረሰቦች ውስጥ ከቋንቋቸው እና ከባህላቸው የመነጩ እጅግ ጥልቅ ትርጉም ያላቸው ስሞች ይሰጣሉ።
ስም አወጣጥ ሁልጊዜ የማህበረሰብን ባህል፣ ቋንቋ፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ዘመን ተከትሎ ይጓዛል። አሁን በከተሞች የሚወጡ ስሞች ከመጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱስ ቁርዓን የሚሰጡ ናቸው። ተሻገር ቀስቅሰው ጥጋቡ የሚል ስም በከተሞች መስማት አሁን ከባድ ነው። የኢብራይስጥ ስሞች በስፋት ለልጆች ይሰጣሉ። በእስልምናው እምነትም የቅዱስ ቁርዓን ስሞች ለልጆች ይሰጣሉ።
ስም ለባለቤቱ ሞራል በረከት እና መኩሪያ የመሆን ጥቅም አለው። በአንጻሩ ወላጆች የራሳቸውን ብሶት ወይም ከጎረቤት ጋር ያላቸውን ጠብ “አትርሳው” ብለው በልጃቸው ስም ሲገልጹት በልጆቹ ላይ የስነልቦና ጠባሳ ይፈጥራል። ለበቀል እና ተንኮል ዝግጁ ሆነው ቂም ቋጥረው ያድጋሉ።
ስም የሚለወጥ መለያ ነው። ስሞች በብዙ ምክንያቶች ይቀየራሉ። ሰዎች ሃይማኖት ሲለውጡ፣ ከገጠር ከተማ ሲመጡ፣ አካባቢ ሲለውጡ፣ አዲስ ማንነት ለመገንባት፣ ለመድረክ ስምነት፣ በፓለቲካ ርዕዮት ዓለም ለውጥ፣ በወንጀል እና ሌሎች ምክንያቶች ስማቸውን ይቀይራሉ።
የሰብእና ግንባታ እና የአስተሳሰብ ለውጥ አሰልጣኙ ዳዊት ግብረ እግዚአብሔር ስሙን ከአዲስ ራዕይ እና ሕልም ጋር ለማያያዝ ዳዊት ድሪምስ ብሎ የአባቱን ቀይሯል። ድምጻዊ ኤልያስ ተባባል ጎንደር ሲኖር ስሙ ልዋጥህ ነበር። አዲስ አበባ ሲገባ ግን በዙሪያው ያሉ ሰዎች ኤልያስ አሉት።
ስሞች ከዘመኑ መንፈስ ጋር ይጓዛሉ። ዘመኑ ራሱ ጥሩ ወይም መጥፎ ብሎ ይፈርጃቸዋል።
ማረፊያ
እኔ ምን አገባኝ የምትሉት ሀረግ
ይኸ ነው ሀገሬን ያረዳት እንደበግ
የሚል ግጥም ልፅፍ ብድግ አልኩኝና
ምን አገባኝ ብየ ቁጭ አልኩ እንደገና
ከ ኑረዲን ኢሳ
(አቢብ በዓለሜ)
በኲር የሚያዚያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


