ቀንዲሉ ዲፕሎማት

0
67

ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ካላቸው ታላላቅ ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው። መጋቢት 5 ቀን 1904 ዓ.ም በሸዋ ክፍለ ሀገር ቡልጋ ወረዳ የተወለዱት አክሊሉ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል። ከዚያም ወደ ውጭ ሀገር በማቅናት በግብፅ እና በፈረንሳይ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በተለይም በፈረንሳይ ፓሪስ ከሚገኘው ታዋቂው ሶርቦን ዩኒቨርሲቲ በሕግ እና በፖለቲካ ሳይንስ ዘርፍ መመረቃቸው ለወደፊት የዲፕሎማሲ ስኬታቸው ትልቅ መሠረት ጥሎላቸዋል።

ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ በተለያዩ ከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች አገልግለዋል። በተለይም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ያደረጉት ተጋድሎ የሚታወስ ነው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ ላይ ያቀረቡት ሕጋዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ክርክር እንዲሁም የኤርትራና የኢትዮጵያን ፌዴሬሽን ስምምነት በማሳካት ረገድ የነበራቸው ሚና ዘውዴ ረታ በጻፉት የኤርትራ ጉዳይ በተሰኘው መጽሐፍ ሰፍሯል። በተጨማሪም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት እና መቀመጫው አዲስ አበባ እንዲሆን በማድረግ ሂደት ውስጥ ካደረጓቸው አስተዋጽኦዎች ባሻገር የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ታማኝ አማካሪ በመሆን ለረጅም ዘመናት አገልግለዋል።

ተቋም ገንቢው አክሊሉ የኢትዮጵያን የፍትሕ ስርዓት በማዘመን የፍትሐብሔር ሕግ፣ የወንጀል ሕግ፣ የንግድ ሕግ፣ የባሕር ሕግ፣ ወዘተ እንዲረቀቁ እና በተሻሻለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ሕገ መንግሥት ቍጥር 34 እና 88 መሠረት የሕግ መወሰኛ እና የሕግ መምሪያ ምክር ቤቶች ከመከሩበት እና የሚሻሻለው ተካትቶ ካጸደቁት በኋላ ኢትዮጵያን የሕግ ሀገር በማድረግ ረገድ ቀዳሚውን ሚና ተጫውተዋል።

አክሊሉ ሀብተ ወልድ መጋቢት 20 ቀን 1953 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ተሾሙ። በዚህ የኃላፊነት ዘመናቸው የመንግሥትን መዋቅር ለማዘመን እና አስተዳደራዊ ለውጦችን ለማምጣት ጥረት አድርገዋል። ሆኖም የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮት እየተጋጋለ ሲመጣ እና ሕዝባዊ ተቃውሞው ሲበረታ ለሀገሪቱ ሰላም ሲሉ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣን ለመልቀቅ ወሰኑ። ይህ ውሳኔያቸው በወቅቱ በአፍሪካ የፖለቲካ ባሕል ውስጥ እምብዛም የማይታይ እና የሚደነቅ ተግባር ነበር።

ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ በክርክር ብቃታቸው እና በሀገራዊ ተሟጋችነታቸው የሚጠቀሱባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ:: አክሊሉ ሀብተ ወልድ በዓለም አቀፍ መድረክ ካደረጓቸው ታላላቅ የዲፕሎማሲ ተጋድሎዎች ቀዳሚው ኤርትራ ወደ እናት ሀገሯ እንድትመለስ ያደረጉት ጥረት ነው። በወቅቱ በነበሩት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስብሰባዎች ላይ ኤርትራ በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካ ራሷን ችላ መቆም እንደማትችል እና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ ቁርኝት የማይነጠል መሆኑን በሕግ እና በምክንያት በማስደገፍ ተከራክረዋል። በተለይም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የቀድሞ የጣሊያን ቅኝ ግዛቶች እጣ ፈንታ በሚወሰንበት ወቅት፣ የታላላቅ ሀገራትን ተጽዕኖ በመቋቋም በ1945 ዓ.ም የፌዴሬሽን ስምምነቱ እንዲሳካ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

አክሊሉ በዓለም ሀገራት ሸንጎ መድረክ ላይ ካደረጓቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ ንግግሮች መካከል የሚከተለው በተንቀሳቃሽ ምስል እና ድምጽ ተቀርጾ ይገኛል፡-«…ሀገሬ ኢትዮጵያ በዓለም ሸንጎ ላይ ፍርድ ተነፍጓት ስታዝን የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ኢትዮጵያ ያለፉት ታሪኮቿ በትክክል እንዳስረዱት ለነፃነቷ እና ለመብቷ በኮሎኒያሊስቶች ጣሊያን ጋር በየጊዜዉ ስተዋጋ ያሸነፈችዉ ብቻዋን ነው። የተጠቃቺውም ብቻዋን ስለሆነ ሀገሬ መቸውንም ለሚደርስባት አደጋ ከማንም እርዳታ አገኛለሁ ብላ አትጠብቅም። ዛሬም ሆነ ነፃነቷን ለመጠበቅ ታሪኳን ለማስከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ያለባት እሷ ራሷ ብቻ ነች»

አክሊሉ በ1937 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምሥረታ ወቅት ኢትዮጵያን በመወከል የድርጅቱን ቻርተር የፈረሙት እርሳቸው ነበሩ። በዚህ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ወቅት የደረሰባትን በደል እና የዓለም መንግሥታት ማኅበር የፈጸመውን ክህደት በማስታወስ አዲሱ ድርጅት ለዓለም ሰላም እና ለደካማ ሀገራት መብት መከበር ዋስትና እንዲሆን በጽናት ተሟግተዋል። ይህም ኢትዮጵያ የድርጅቱ መስራች እና ተሰሚነት ያላት ሀገር እንድትሆን አስችሏል።

ከሶማሊያ ጋር በነበረው የድንበር ውዝግብ እና በኦጋዴን ጉዳይ ላይ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ያሳዩት የዲፕሎማሲ ጥንካሬ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያ አንድም ኢንች መሬት አሳልፋ እንደማትሰጥ እና የሌሎች ሀገራትን የውስጥ ጉዳይ እንደማትከታተል በግልጽ በመግለጽ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በዲፕሎማሲያዊ መድረኮች አስከብረዋል። በተጨማሪም ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በነበሩ ድርድሮች የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስጠበቅ እና የውጭ ኃይሎች በሀገሪቱ ላይ የነበራቸውን ተጽዕኖ ለመቀነስ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል።

ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ ከታዋቂ ዲፕሎማትነታቸው ባሻገር በግል ሕይወታቸው እና ለሀገሪቱ ዘመናዊነት ባበረከቱት አስተዋጽኦ የሚጠቀሱ በርካታ ታሪኮች አሏቸው። የተወለዱት  ከገጠር ቤተሰብ ሲሆን አባታቸው በቡልጋ ወረዳ የቤተ ክርስቲያን ካህን ነበሩ። ከእሳቸው በተጨማሪ ወንድሞቻቸው መኮንን እና አካለወርቅ ሀብተ ወልድ በንጉሡ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ ደርሰው አገልግለዋል። ይህ የሀብተ ወልድ ቤተሰብ በወቅቱ በነበሩት ባላባቶች እና መኳንንት ዘንድ እንደ ተቀናቃኝ የሚታዩ እና በንጉሡ ዘንድ ደግሞ በዕውቀታቸው የሚታመኑ “ቴክኖክራቶች” ተደርገው ይቆጠሩ ነበር።

የትዳር ሕይወታቸውም በወቅቱ የነበረውን ማኅበራዊ ተጽዕኖ የተሻገረ ነበር። በፓሪስ ቆይታቸው ኮሌት ቫላድ የተባለች ፈረንሳዊት አግብተዋል።  ይህ ጋብቻ በኢትዮጵያ መኳንንት ዘንድ ከፍተኛ ትችት አስነስቶባቸው ነበር። ሆኖም አክሊሉ ለትዳራቸው እና ለፍቅራቸው ሲሉ የነበረውን ፖለቲካዊ ተጽዕኖ በጽናት ተቋቁመዋል። በስደት ዘመንም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት በፈረንሳይ ሆነው “Nouvelles d’Ethiopie” የተሰኘ ጋዜጣ በማዘጋጀት የኢትዮጵያን በደል ለዓለም በማሳወቅ እና የነፃነት ትግሉን በዲፕሎማሲው መስክ በመርዳት ትልቅ አሻራ አሳርፈዋል።

አክሊሉ ሀብተ ወልድ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ መዋቅር መዘርጋትም ግንባር ቀደም ነበሩ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲመሠረት በነበረው ድርድር እና ስምምነት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን በ1948 ዓ.ም የተሻሻለውን ሕገ መንግሥት በማርቀቅ ረገድም ከፍተኛ ባለሙያ ነበሩ። ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ጎን ለጎን የያዙት “ጸሐፌ ትዕዛዝ” ወይም “ሚኒስትር ደ ፕላን” የተሰኘው ሹመትም የንጉሡን ትዕዛዞች የመመዝገብ እና የመንግሥትን ማኅተም የመጠበቅ ትልቅ ኃላፊነት የነበረው በመሆኑ በዘመኑ በነበረው የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ቁልፍ ሰው ነበሩ።

ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ በደርግ እስር ቤት በነበሩበት ወቅት የጻፉት የመጨረሻ የምስክርነት ቃል ወይም “የታሪክ ማስታወሻ” በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰነድ ነው። ይህ ጽሑፍ በዋናነት ለደርግ መርማሪ ኮሚሽን የቀረበ ቢሆንም እርሳቸው እና መንግሥታቸው የፈጸሟቸውን ተግባራት እንዲሁም የሀገሪቱን የመጨረሻ ቀናት ውጥረት በዝርዝር የሚያስረዳ ነው።

በዚህ ቃላቸው ውስጥ አክሊሉ ሀብተ ወልድ በተለይ አጽንኦት የሰጡት በ1966 ዓ.ም በገዛ ፈቃዳቸው ከሥልጣን ለመልቀቅ የወሰኑት  ለሀገሪቱ ሰላምና ደኅንነት ሲሉ እንደነበር ነው። በወቅቱ የነበረው የሰራዊት እና የሕዝብ ቁጣ ደም መፋሰስ እንዳያስከትል በመስጋት ንጉሡን የሥልጣን መልቀቂያቸውን እንዲቀበሏቸው በጽናት እንደጠየቁ ገልጸዋል። ይህ ተግባራቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ሥልጣን ለመልቀቅ የተደረገ የመጀመሪያው ትልቅ ሙከራ ተደርጎ ይወሰዳል።

በተጨማሪም በምስክርነታቸው ላይ ስለ ኤርትራ ጉዳይ፣ ስለ ድንበር ውዝግቦች እና ስለ ሀገሪቱ ኢኮኖሚ የነበራቸውን ሚና አንጸባርቀዋል። በተለይም በኤርትራ ጉዳይ ላይ ያደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ ከሀገር ፍቅር የመነጨ እንደነበር እና ምንም ዓይነት ክህደት እንዳልፈጸሙ በዝርዝር አስረድተዋል። ይሁን እንጂ ደርግ ይህንን ቃላቸውን እና የቀረበውን ማስረጃ ከግምት ውስጥ ሳያስገባ ኅዳር 14 ቀን 1967 ዓ.ም ከሌሎች 60 ባለሥልጣናት ጋር በግፍ እንዲገደሉ አድርጓል።

ይህ የምስክርነት ቃል ከሞታቸው በኋላ “የታሪክ ማስታወሻ” በሚል ርዕስ በመጽሐፍ መልክ  ታትሟል፤ ስለ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ውድቀት እና ስለ አክሊሉ ሀብተ ወልድ እውነተኛ ማንነት በሚገባ ይገልጻል::

ሳምንቱ በታሪክ

የድል ሃውልት

ባለ አምስት ራስ የነፃነት ሐውልት በመባል የሚታወቀው እና በአዲስ አበባ አራት ኪሎ የሚገኘው የድል ሐውልት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለነፃነቱ ያደረገውን ተጋድሎ የሚዘክር ታሪካዊ መታሰቢያ ነው። ሐውልቱ የተመረቀው ሚያዝያ 27 ቀን 1936 ዓ.ም ነው፤ ይህም ፋሺስት ጣሊያን ተሸንፎ ሀገሪቱ ነፃነቷን ያበሰረችበትን  ሦስተኛ ዓመት መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ ነው። ሐውልቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያላቸውን በርካታ ምስሎችን እና ምልክቶችን በውስጡ የያዘ ነው።

በሐውልቱ አናት ላይ የሚገኘው የአንበሳ ምስል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ጽናትን ይወክላል።  በዙሪያው ያሉ መስተዋቶች እና ቅርጾች ደግሞ አምስቱን ዓመታት የቆየውን መሪር የትግል ዘመን ያሳያሉ። በሐውልቱ ግርጌ ላይ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ወደ ሀገር መመለስ እና የአርበኞችን የጀግንነት ታሪክ የሚተርኩ ምስሎች እንዲሁም ታሪካዊ ጽሑፎች ተቀርጸውበታል። ይህ ስፍራ በየዓመቱ ሚያዝያ 27 ቀን የድል በዓል በሚከበርበት ወቅት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የአርበኞች ማኅበር አባላት የአበባ ጉንጉን የሚያስቀምጡበት ብሔራዊ መካነ መታሰቢያ ነው።

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የሚያዝያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here