የፈተና ቅድመ ዝግጅት ምን ይመስላል?

0
61

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒሥቴር ከሰሞኑ እንዳስታወቀው በተያዘው ዓመት ሁሉም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ተፈታኞች ፈተናውን የሚወስዱት በቴክኖሎጂ (Online System) መሆኑን አሳውቋል። ይህን መሠረት በማድረግም የሚመለከታቸው ሁሉ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው ፈተናዎች በበይነመረብ መሰጠታቸው የፈተና ስርቆትን፣ ማጭበርበርን እንዲሁም ስህተትን ለመቀነስ፣ ለደህንነት ጥበቃ እና የተሻለ ውጤትን ለማግኘት፣ ጊዜ እና ጉልበትን ለመቆጠብ እና ከዚህ ባለፈም የተሻለ የመረጃ ቋት እንዲኖር እና ፈጣን ግብረ መልስ ለመስጠት ያስችላል፡፡
እኛም ይህን መነሻ በማድረግ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ቅድመ ዝግጅት እንዴት እንደ ሆነ የሚመለከታቸውን አነጋግረናል:: ተማሪ ነሲቡ በላይነህ በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጣና ሐይቅ አጠ/2ኛ ደረጃ ት/ቤት የ12ተኛ ክፍል ተማሪ ነው:: ተማሪው ለበኩር እንደተናገረው ለብሔራዊ ፈተናው በቂ ዝግጅት አድርጓል። የተለያዩ የትምህርት ዓይነቶችን ይዘትም ሸፍኗል። የመደበኛውን ክፍለ ጊዜ ትምህርት በአግባቡ ከመከታተሉ እና ቤተ መጻሕፍት በአግባቡ ከመጠቀሙ በተጨማሪ ከጓደኞቹ ጋር ማጥናቱ ለውጤታማነቱ በእጅጉ እንደ ሚያግዘው ተስፋ ሰንቋል። ያልገባውን እንዲረዳም አስችሎታል።
ነሲቡ እና ጓደኞቹ በትምህርት ቤታቸው ቅዳሜ እና እሁድ የማጠናከሪያ ትምህርትም እየተሰጣቸው ነው። ባለፉት ጊዜያት ከዘጠነኛ ክፍል ጀምሮ ያሉ የፈተና ወርክ ሽቶችን በመሥራትም ለፈተናው ልምምድ እንደሚያደርጉ ነግሮናል::
ነሲቡ በሀገር አቀፍ ፈተና ውጤታማ ለመሆን የተለያዩ መንገዶችን ቢጠቀምም ፈተናው በበይነ መረብ የሚሰጥ መሆኑ ግን ስጋት ፈጥሮበታል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እስካሁን ምንም አይነት የኮምፒውተር ልምምድ አለማድረጉ መሆኑን ነው የገለፀው። ችግሩን በመረዳት በአስቸኳይ እንዲጀመርላቸውም ጠይቋል።
ሌላዋ ሐሳቧን ያጋራችን የጣና ሐይቅ አጠ/2ኛ ደረጃ ት/ቤት የ12ተኛ ክፍል ተማሪዋ ማህደር ታዘበው ናት:: ተማሪዋ እንዳለችው ከክረምት ጀምሮ ባለፉት ጊዜያት የተሰጡ ፈተናዎችን በመሥራት፣ ቅዳሜ እና እሁድ የተመረጡ የትምህርት ዓይነቶችን የማጠናከሪያ ትምህርት በመማር እና ከጓደኞቿ ጋር በማጥናት ለፈተና እየተዘጋጀች ትገኛለች።
ፈተናው በበየነ መረብ በመሆኑም ቀደም ባሉት ጊዜያት ከቤት ውስጥ ባለ ላፕቶፕ ልምምድ ታደርግ እንደነበር ነው ተማሪዋ የገለጸችው:: በቀጣይም ትምህርት ቤቱ የሚሰጠውን የቅድመ ፈተና የኮምፒውተር ልምምድ በማድረግ ፈተናውን ያለምንም መጨናነቅ ለመፈተን በሥነ ልቦና ጭምር መዘጋጀቷን ተናግራለች::
አሁን ላይ በኢንተርኔት መቋረጥ ምክንያት ትምህርት ቤት ላይ ልምምድ እያደረጉ ባለመሆኑ ትምህርት ቤቱ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን ችግሩ ተፈትቶ ልምምድ እንዲጀምሩ ነው የጠየቀችው:: “እኔ ዕደለኛ ሆኘ ከቤት ባለ ላፕቶፕ በቤተሰቦቸ እገዛ ልምምድ እያደረግሁ ነው፤ ሆኖም ኮምፒውተር እንኳን ነክቶ የማያውቅ ተማሪ አለ:: ትምህርት ቤቱ ይህንን ታሳቢ ማድረግ ይኖርበታል” በማለት ጠይቃለች።
የጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአይ ቲ መምህር አቶ ዓለምነው ምትኩ ተማሪዎች ያነሱትን ሐሳብ ተጋርተዋል፤ ትምህርት ቤቱ ችግሩን ለመፍታት ኢንተርኔት ባለባቸው አካባቢዎች ተማሪዎችን በመውሰድ ከአሁኑ ልምምድ እንዲያደርጉ ፕሮግራም እያወጣ እንደሚገኝም ነው የተናገሩ።
በት/ቤቱ ከአንድ ሺህ በላይ የ12ተኛ ክፍል ተፈታኞች አሉ:: የጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ደረጀ ከፋለ ተፈታኝ ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ቅዳሜ እና እሁድን በመጠቀም ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ የፈተና ወረቀቶችን በመሥራት የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን ጠቁመዋል:: በሥነ- ልቦና ባለሙያ የታገዘ የስነ – ልቦና ዝግጅት እንዲኖራቸው መደረጉንም ተናግረዋል::
ለልምምድ በቂ ኮምፒውተር ቢኖርም የኢንተርኔት መቋረጥ ግን አስቸጋሪ እንደሆነባቸው አቶ ደረጀ አክለዋል፤ ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት ተፈታኝ ተማሪዎችን ፕሮግራም በማውጣት ኢንተርኔት ባለባቸው አካባቢዎች በመውሰድ ልምምድ እንዲያደርጉ ይሠራል ነው ያሉት::
በምሥራቅ ጎጃም ዞን የደብረ ማርቆስ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ሜሮን ከበደ እንዳለችው ትምህርት ቤቱ ከሰኞ እስከ እሁድ የቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረጉ አመስግናለች፤ ለብሔራዊው ፈተናም እየተዘጋጀች ነው:: በበይነ መረብ ለመፈተንም ከአይ ቲ ክፍል ባለኮምፒውተር እየተለማመደች መሆኗን ነው የተናገረችው:: የቆዩ የፈተና ሽቶችን በመሥራት እንዲሁም የተለየዩ ጥያቄዎችን በማውጣት እንዲሠሩ መምህራን እንደሚያግዟቸውም አክላለች::
ሌላው የደብረማርቆስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ኪሩቤል ደመቀ በበኩሉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከመጀመሪያው ጀምሮ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግሯል:: በተለይ ደግሞ የበይነ መረብ ፈተናውን ለመውሰድ በአይ ቲ ክፍል የኮምፒውተር ልምምድ እያደረገ ነው:: በሁሉም ነገር የመምህራን እገዛ የተሻለ መሆኑንም ጠቁሟል::
የደብረ ማርቆስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተወካይ ርእሰ መምህር አቶ አድለው ዓለሙ በተያዘው ዓመት ሰባት መቶ አራት ተማሪዎችን ለ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለማስፈተን መዘጋጀታቸውን ነው የተናሩት:: ተማሪዎችን ዝግጁ ለማድረግም ከሕዳር ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ከመደበኛው ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ባለፉት ዓመታት ለፈተና የወጡ ጥያቄዎችን በመሥራት መምህራን እያገዟቸው መሆኑን ተናግረዋል:: ሁሉም ተፈታኝ ተማሪዎችም በበይነ መረብ ፈተናውን እንዲወስዱ እያዘጋጇቸው መሆኑንም አመላክተዋል::
የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ብርሐን አንተነህ በበኩላቸው በተያዘው የትምህርት ዘመን አንድ ሺህ 850 ተማሪዎችን የ12ተኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና በበይነ መረብ ለማስፈተን ዝግጅት እየተደረገ ነው:: በዚህም ተማሪዎች የሚፈተኑባቸው ኮምፒውተሮችን በማሟላት ኢንተርኔት እና መብራት በተቆራረጠባቸው አካባቢዎች የኤሌትሪክ ምሰሶዎችን እና ጀኔሬተሮችን በማቅረብ ዝግጁ እንዲሆኑ እየተሠራ ይገኛል::የኮምፒውተር ግብአት ባልተሟላባቸው አንዳንድ አካባቢዎችም ከኮሌጆች እና ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች ጋር እየተሠራ መሆኑንም ነው የተናገሩት::
በተመሳሳይ በደሴ እና ደብረ ብርሐን ከተማ አስተዳደሮች የተፈታኝ ተማሪዎችን ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ጠይቀናቸው ነበር:: አቶ ፍቅር አበበ የደሴ ከተማ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ናቸው:: የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ፈተና የቅድመ ዝግጅት ሥራ በሁለት መንገድ እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል:: ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ ቀዳሚው ሲሆን ለበይነ መረብ ፈተናው ምቹ ሁኔታን መፍጠር ደግሞ ሌላው ትኩረት የተደረገበት ሥራ እንደሆነ ነው የተናገሩት::
በደሴ ከተማ በአጠቃላይ ከአራት ሺህ በላይ የ12ተኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች እንዳሉ የተናገሩት ኃላፊው፤ መምሪያው የ12ተኛ ክፍል የዲጅታል ፈተና ሲያስፈትን ለሦስተኛ ጊዜ ነው፤ ለዚህ ዓመት ተፈታኞችም ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል::
የደብረ ብርሐን ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መቅደስ ብዙነህ በከተማ አስተዳደሩ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን የሚያስፈትኑ 10 ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን ተናግረዋል:: ትምህርት ቤቶቹም ተፈታኝ ተማሪዎችን ብቁ ለማድረግ ያለፈውን ዓመት ውጤት ከወላጆች ጋር በመገምገም የተሻለ ውጤት ያመጡትን በማበረታታት እና ዕውቅና በመስጠት፣ ሞዴል ፈተናዎችን በመስጠት፣ የማጠናከሪያ ትምህርት ቅዳሜና እሁድ በማስተማር እና በመከለስ ብቁ ለማድረግ ሲሠሩ መቆየታቸውን ነው የተናገሩት::
ኃላፊዋ አክለውም ባለፈው ዓመት የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ ማስፈተናቸውን አስታውሰዋል:: በዚህ ዓመትም ለሁለተኛ ጊዜ ለማስፈተን የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል::
በከተማ አስተዳደሩ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ተማሪዎች የሚፈተኑ ሲሆን ከዩንቨርሲቲዎች እና ከኮሌጆች ጋር በትብብር እንደሚሠሩ ነው ያብራሩት። የተማሪዎችን በራስ መተማመን ለማጎልበትም ከሥነ ልቦና ባለሙያ ጋር በመሆን የምክር አገልግሎት እንደተሰጣቸው አብራርተዋል:: ወላጆችም ልጆቻቸውን ለፈተና ዝግጁ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል::

ግእዝ በአማርኛ

አብ    —   አባት

እም    —   እናት

ወላዲ  —  ወላጅ አባት

ወላዲት — ወላጅ እናት

ንኡስ   — ትንሽ ልጅ

ንእስት — ትንሽ ሴት ልጅ

ደቂቅ  — ልጆች/አሽከሮች/

ደቃውቅ  — ጥቃቅን ልጆች

ሕጻን    — ትንሽ ልጅ

ሕጻናት — ትንንሽ ልጆች

(ሰናይት በየነ)

በኲር የሚያዝያ 26 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here