የኖራ መፍጫ ፋብሪካዎች ሊተከሉ  ነው

0
56

የዓለም እርሻ ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው በዓለም አቀፍ ደረጃ አራት ቢሊዮን ሄክታር ያህል መሬት በአሲዳማ አፈር የተጎዳ ነው፤ ይህም ከ30 እስከ 40 በመቶ ያህሉን ለእርሻ ሥራ ሊውል የሚችለውን መሬት ድርሻ ይይዛል፡፡በሀገራችንም ችግሩ እየተባባሰ መሄዱን የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል። ችግሩ የተስፋፋባቸው ከፍተኛ አምራች በሆኑ አካባቢዎች መሆኑ ደግሞ ችግሩን አሳሳቢ አድርጎታል።

የአፈር አሲዳማነት በምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፤ እያስከተለም ይገኛል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ታዲያ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት መንግሥት ለችግሩ መፍትሔ የሚሆኑ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል። ሆኖም ካለው የችግሩ ስፋት እና አሳሳቢነት አኳያ ፈጣን እርምጃ እና የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል።

በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ አውዘት ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ጣፈጠ በሪሁን ለበኩር በስልክ እንደተናገሩት  ማሳቸውን በማለስለስ እና   የተለያዩ ግብዓቶችን በመጠቀም ለረጅም ዓመታት ውጤታማ አምራች ሆነዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማሳቸው በአፈር አሲዳማነት በመጠቃቱ ምርት መቀነሱን ነው የተናገሩት፡፡ ችግሩን ለመፍታት ታዲያ በባለሙያ ምክረ ሀሳብ የማሳቸውን የአፈር ናሙና አስመርምረዋል፤ በአሲዳማነት የተጠቃውን መሬታቸውን በማከም ከበፊቱ የተሻለ ምርት ማምረታቸውን እና በመጣው ለውጥም መደሰታቸውን ገልጸውልናል፡፡

ሌላው በስልክ ያነጋገርናቸው አርሶ አደር የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ባንጃ ወረዳ   አርሶ አደር ደሳለው በላቸው በመሬታቸው የአፈር አሲዳማነት በመከሰቱ ምርታቸው በጣም ቀንሶ እንደነበር አስታውሰዋል። በባለሙያ ከመሬታቸው የአፈር ናሙና ተወስዶ ካስመረመሩ በኋላ የአፈር አሲዳማነት በመገኘቱ በኖራ ማከም እንደጀመሩም ነግረውናል። ይህም ውጤት እንዳስገኘላቸው ነው የገለጹት፡፡

አርሶ አደሩ እንዳሉት የአፈር አሲዳማነት ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር፤ በኖራ ከታከመ በኋላ ግን ምርታማነቱ ተሻሽሏል። በኖራ የታከመው መሬት ለሁለት ዓመት እና ከዚያ በላይ ምርት እንደሚሰጥ ተሞክሯቸውን አካፍለውናል።    ለዚህ ዓመትም መሬታቸውን ለማከም ኖራ ለመግዛት መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት። አሲዳማውን አፈር በኖራ ለማከም ደግሞ የባለ ሙያ ምክረ ሀሳብ በመቀበል በአግባቡ እና በጥንቃቄ እንደሚቀላቅሉ አክለዋል።

አርሶ አደሩ እንደነገሩን በአሲዳማነት የተጠቃ መሬት ምርት ካለመስጠትም ባሻገር ለከብት ግጦሽ የሚሆን ሳር እንኳን አያበቅልም። በመሆኑም አርሶ አደሮች በአሲዳማነት የሚጠረጠር መሬታቸውን የአፈር ናሙና በማስወሰድ የአፈሩ ጤንነት እንዲታይ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የሚመለከተው አካል ደግሞ በቂ ኖራ ለአርሶ አደሩ ማቅረብ ይገባዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን  ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ መልካም አያሌው ለበኩር በስልክ እንደተናገሩት በዞኑ ካሉት 13 ወረዳዎች ውስጥ  ከእብናት ወረዳ በስተቀር በሁሉም ወረዳዎች   መጠኑ ቢለያይም የአፈር አሲዳማነት ችግር ተከስቷል። ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ነው። በአሁኑ ወቅትም የአፈር ናሙና እየተወሰደ የመለየት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

ቡድን መሪው እንዳሉት ከ641 ሺህ 040 ሄክታር የእርሻ መሬት ውስጥ 197 ሺህ 342 ሄክታር መሬት የሚሆነው በአሲዳማ አፈር መጠቃቱን የአፈር ናሙና ተወስዶ ተረጋግጧል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ናሙና ተወስዶ በአሲዳማ አፈር የተጠቃ መሆኑ የተረጋገጠ 13 ሺህ 507 ነጥብ ዘጠኝ ሄክታር ያልታከመ መሬት መኖሩን ነው የተናገሩት። ለዚህ ደግሞ ከ270 ሽህ ኩንታል በላይ ኖራ ያስፈልጋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም 188ሺህ የአፈር ናሙና ይመረመራል ተብሎ በዕቅድ ተይዞ እስካሁን ከ90 ሺህ በላይ የአፈር ናሙና ተሰብስቧል።

በያዝነው ዓመት አንድ ሺህ 500 ኩንታል ኖራ ብቻ ለአንድ ወረዳ መቅረቡን የተናገሩት አቶ መልካም የሚመለከተው አካል በቂ የሆነ የኖራ አቅርቦት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ  ኃላፊ ወ/ሮ ቤዛዊት ጌታሁን ለበኩር በስልክ እንደተናሩት በብሔረሰብ አስተዳደሩ ከጃዊ ወረዳ በስተቀር በሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች መጠኑ ቢለያይም የአፈር አሲዳማነት ችግር ተከስቷል። ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም የአፈር ናሙና እየተወሰደ የመለየት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

ኃላፊዋ እንዳሉት ከ17 ሺህ 800 ሄክታር መሬት ላይ የአፈር ናሙና ተወስዶ 10 ሺህ 500 የሚሆነው ወደ አፈር ቤተ ሙከራ ተልኮ አብዛኛው የመሬት ክፍል በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ መሆኑ ተረጋግጧል። ችግሩን ለመከላከል እና ጉዳቱን ለመቀነስ ሰፊ ሥራን እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።

ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የኖራ እጥረት አጋጥሞ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊዋ በዚህ ዓመት በወቅቱ እና  በታሰበው ልክ እንዲቀርብ “በትኩረት እየተሠራ ነው” ብለዋል። ኖራን በእርሻ ወቅት የዝናብ እና የእርጥበት መጠኑ ሳይበዛ በተገቢው መንገድ መጥኖ መጨመር እንደሚገባም መክረዋል። ለዚህ ደግሞ የባለሙያን ምክረ ሀሳብ በመቀበል ኖራን ከአፈር ጋር ማቀላቀል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ችግሩን ለመከላከል ታዲያ የተፈጥሮ ማዳበሪያን (ኮምፖስትን) መጠቀም፣ በኖራ ማከም፣ የአፈር አሲዳማነትን ሊቋቋሙ የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን መጠቀም እና ሌሎች የአፈሩን ጤንነት ሊመልሱ የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።

በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ዳይሬክተር እና  የአፈር ለምነት ተመራማሪ ተስፋዬ ፈይሳ (ዶ/ር) “የአፈር አሲዳማነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሦስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዜጎችን የምግብ ዋስትና አደጋ ላይ የጣለ፣ በዓለም ኢኮኖሚ ላይም እስከ 40 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ እያስከተለ የሚገኝ ዝምተኛ ጠላት ነው” ብለዋል።

ዶክተር ተስፋዬ እንዳስገነዘቡት በኢትዮጵያ 44 በመቶ እና በአማራ ክልል ደግሞ (ከ12 ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት መሆኑን ልብ ይሏል) 36 ነጥብ ስድስት በመቶ መሬት በአሲዳማነት የተጠቃ ነው። በአሁኑ ወቅት ችግሩ እየተባባሰ በመምጣቱም አርሶ አደሮችን ከአስፈላጊ ምርቶች እያራቀ ይገኛል።

የአፈር አሲዳማነት እንዲከሰት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት መካከል ከፍተኛ የዝናብ ሥርጭት መኖር አንዱ ነው፤ ይህ ሲሆን ደግሞ በአፈር ውስጥ የሚገኙ እንደ ማግኒዚየም፣ ካልሺየም፣ ሶዲየም እና ፖታሺየም የመሳሰሉ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች በጎርፍ ስለሚታጠቡ ችግሩ ይፈጠራል፤ ከዚህ በተጨማሪም በተደጋጋሚ ወይም ለረዥም ዓመታት መሬቱን ማረስ፣ በተደጋጋሚ የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የባለ ሙያ ምክረ ሀሳብ ሳይቀበሉ ከመጠን በላይ መጠቀም፣ የአፈር እና የውኃ ጥበቃ ሥራ በተገቢው አለመሠራቱ፣ የሰብል ተረፈ ምርትን ከማሳ ሙሉ በሙሉ ማንሳት እና የመሬት ጥበቃ ሥራ አለመሠራት አፈር በአሲድ እንዲጠቃ ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው።

ተፅዕኖውን ለመቀልበስ ደግሞ ኖራን መጠቀም፣ ከልክ ያለፈ ግጦሽን ማስቀረት፣  ኖራን ከሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ማዳበሪያዎች ጋር አቀናጅቶ መጠቀም እንደሚገባ ዶክተር ተስፋዬ ፈይሳ ጠቁመዋል።

አሲዳማነትን መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎችን ስለመጠቀምም በተጨማሪ መፍትሔነት አንስተዋል። ለአብነትም ከብራዚል የመጣው እና ምንም ኖራ ሳይጨመርበት በሄክታር እስከ 40 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችለው “ሰከላ” የተባለው የስንዴ ዝርያ ውጤታማነቱ መረጋገጡንም ጠቀሙዋል።

በአሲዳማነት የተጠቃውን መሬት ለማከም ስድስት ከፍተኛ አቅም ያላቸው የኖራ መፍጫ ፋብሪካዎችን ለመትከል በግዥ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ዶክተር ተስፋዬ ፈይሳ አስታውቀዋል።

ኖራን ካለበት ቦታ መፍጨት የሚያስችሉ ተንቀሳቃሽ ማሽኖችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

አርሶ አደሮች ኖራ ሲበትኑ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን የጤና ስጋት ለመቀነስም የኖራ እንክብል መሥሪያ ማሽኖች እና በትራክተር የሚጎተቱ መበተኛ መሣሪያዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት ታሳቢ መደረጉን ገልጸዋል።

የምርምር እና የቴክኖሎጂ ሥራዎች ተቀናጅተው ከተሠሩ ክልሉ ራሱን ከመመገብ ባለፈ ለሀገር እና ለምሥራቅ አፍሪካ የሚተርፍ ምርት ማምረት የሚያስችል አቅም እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here