አርበኝነት

0
95

አርበኝነት ማለት በቀላል አገላለጽ ሀገርን መውደድ እና ለሀገር ደህንነት እና ክብር መጨነቅ ነው። በድሮ ዘመን አባቶቻችን እና እናቶቻችን አርበኛ የሚባሉት የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር እና ነፃነቷን ለመጠበቅ በዱር በገደሉ ተዋድቀው ድል ሲቀዳጁ ነበር። የእነሱ ጀግንነት ዛሬ እኛ በነፃነት እንድንኖር አስችሎናል። ዛሬ ግን የአርበኝነት ትርጉሙ ከጦር ሜዳ አልፎ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ የምናሳየው መልካም ተግባር ሆኗል።

አንድ ልጅ አርበኛ ሊሆን የሚችለው በትምህርቱ ጎበዝ ሆኖ ለሀገሩ የሚጠቅም እውቀት ሲቀስም ነው። በትምህርት ቤት የሀገርን መዝሙር በአክብሮት መዘመር፣ ሰንደቅ ዓላማን መውደድ እና የሀገርን ታሪክ በሚገባ ማወቅ ትልቅ የአርበኝነት ተግባር ነው። ከዚህ በተጨማሪም ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት መስጠት፣ ዛፎችን መትከል እና ቆሻሻን በተገቢው ቦታ መጣል ሀገራችን ውብ እና ለኑሮ ምቹ እንድትሆን ስለሚረዳ ይህ ራሱ አርበኝነት ነው።

እውነተኛ አርበኛ ለሰዎች ደግነትን የሚያሳይ፣ ሽማግሌዎችን የሚረዳ እና ሕግን የሚያከብር ዜጋ ነው። እናንተም በቤታችሁ ወላጆቻችሁን በመታዘዝ፣ በትምህርት ቤታችሁ ጓደኞቻችሁን በመርዳት እና በጨዋታችሁ ታማኝ በመሆን የዘመኑ አርበኞች መሆን ትችላላችሁ። ሀገር የምትገነባው በታላላቅ ጀግኖች ብቻ ሳይሆን እንደ እናንተ ባሉ ትንንሽ ልጆች መልካም ተግባር እና ፍቅር ጭምር መሆኑን አትርሱ።

ምንጭ፡- የጀግኖች ታሪክ ለህፃናት

ተረት

ቁራ እና ቀበሮ

አንድ ቀን አንዲት ቁራ አንድ ትልቅ ቁራጭ አይብ አግኝታ ዛፍ ላይ አረፈች። አይቡን ለመብላት ስትዘጋጅ በረሃብ ተመትቶ የነበረ አንድ ቀበሮ በዛፉ ስር መጣ።

ቀበሮው አይቡን ሲያይ በጣም አማረው እና ቁራዋን አታልሎ ለመውሰድ አሰበ። ቀና ብሎ እያያት እንዲህ አላት፦ “ወይ ጉድ! አንቺ ቁራ እንዴት እንዲህ ታምሪያለሽ? ላባሽ እንዴት ያብረቀርቃል! አይንሽንማ ተይው። እርግጠኛ ነኝ ድምፅሽም እንደ ውበትሽ ያማረ መሆን አለበት። እስኪ አንድ ጊዜ ዘፍነሽ አሰሚኝ?”

ቁራዋ በቀበሮው ውዳሴ ተታለለች። ድምፅዋ ምን ያህል መልካም እንደሆነ ለማሳየት ፈልጋ አፏን ከፍታ “ቃ! ቃ!” ስትል፣ በአፍዋ የያዘችው አይብ መሬት ላይ ወደቀ።

ቀበሮውም የፈለገው ይሄው ስለነበር፣ አይቡን ወዲያው ለቅሞ ዋጠው እና እየሳቀ እንዲህ አላት፦ “አይ አንቺ ቁራ! ውበትስ አለሽ፣ ግን ትንሽ ብልሃት ይጎድልሻል።”

ይህ ተረት የሚያስተምረን “በሽንገላ እና በከንቱ ውዳሴ መታለል እንደሌለብን” ነው።

ሞክሩ

ረጅሙ የአንገት ባለቤት እንስሳ ማን ይባላል?

ፀሐይ በየት በኩል ትወጣለች?

በአንድ አመት ውስጥ ስንት ወራት አሉ?

መልስ

ቀጭኔ

በምስራቅ

12 (ወይም በኢትዮጵያ 13) ወራት

ነገር በምሳሌ

  • ሀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ነው፣ ለሀምሳ ሰው ግን ጌጡ ነው።

ለአንድ ሰው የሚከብድ ስራ በጋራ ከተሰራ ቀላል ይሆናል።

 

  • ከነገሩ ጦሙን እደሩ።

ከማያውቁት ነገር ውስጥ ገብቶ ከመቸገር መራቅ ይሻላል።

 

  • ለሀገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ።

ለነገሮች አዲስ መሆንን ይገልጻል፡፡።

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here