በካርድዎ ለሀገር የሚበጀውን ይምረጡ!

0
9

ምርጫ ለሀገር ሰላም፣ ዕድገት እና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡ በመሆኑም ሀገራት  በየራሳቸው ሕገ-መንግሥት የምርጫ ሕግጋትን መሰረት በማድረግ የሚያከናውኑት፣ ዜጎች  በነፃነት እና በፈቃደኝነት መሪዎቻቸውን የሚመርጡበት፣  ሥልጣን ለሚሰጣቸው አካላት ይሁንታቸውን የሚገልጹበት፣   በድምጽ አሰጣጥ በቀጥታ የሚሳተፉበት  ዲሞክራሲያዊ ሂደት ነው።

ምርጫ ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ያላቸውን የመወሰን መብት በተግባር የሚተረጉሙበት መንገድም ነው። ምርጫ የዜጎችን ባለቤትነት ከማረጋገጡም ባሻገር   በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ያስችላል፣ ሰላማዊ ውድድርን ያበረታታል፣ በሐሳብ እና በፖሊሲ የበላይነት የመፎካከር ባህልንም ያዳብራል።

ምርጫ ዜጎች    መሪዎቻቸውን በቀጥታ በካርድ ለመምረጥ የሚደረግ ሕጋዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሂደት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሕዝብን ፍላጎት ለማሳካት፣ መንግሥትን ሕጋዊ ለማድረግ እና የዲሚክራሲ ሥርዓትን ለማጠናከር ያስችላል፡፡

ኢትዮጵያም በተያዘው ዓመት ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ ይዛለች፤ ለዚህ ደግሞ መራጮች የመራጭነት ካርድ ማውጣትን ጨምሮ በርካታ የቅድመ ምርጫ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የምርጫ ካርድ መያዝ ብቻ በቂ ባለመሆኑ  መራጮች የሚበጃቸውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ስለፓርዎች  በቂ መረጃ  እና ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

መራጮች የሚመርጧቸውን ዕጩዎች ማንነት እና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸውን ፕሮግራሞች በሚገባ ለይተው ማወቅና መመርመር  ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች እየቀረቡ የፖሊሲ አማራጮቻቸውን  እና ሐሳቦቻቸውን በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡ መራጮችም የፓርቲዎችን ፕሮግራም   በመከታተል መመርመር  እና ማጤን ይገባል። የትኛው ይሆነኛል?  ብሎ ራስን መጠየቅ እና መረዳትንም ይጠይቃልና መራጮች ካርድ ከማውጣት ባሻገር ለሚመርጡት ፓርቲ እና ተወካይ ልዩ ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል።

መራጮች በቀጣይ ተወካዮቻቸውን ለመምረጥ ያስችላቸው ዘንድ በመገናኛ ብዙኃን (በሚዲያ) እየቀረቡ ያሉትን ፓርቲዎች እና የእጩዎቻቸውን የመወዳደሪያ ሐሳብ ጠቃሚነት እና አስፈላጊነት እንዲሁም ተዓማኒነትን ግምት ውስጥ በማስገባት የፓርቲዎችን እና የእጩዎችን  ሐሳብ መረዳት፣ ማወዳደር እና መለየት ችላ የሚሉት ተግባር ሊሆን አይገባም።

በመሆኑም በመጪው ለሚከናወነው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሻለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ ከማውጣት በተጨማሪ የእጩ ተወዳደሪዎችን እና የፓርቲዎችን መወዳደሪያ የክርክር ሐሳብ መከታተል፣ ፖሊሲያቸውን እና ሐሳባቸውን መለየት ቁልፍ ተግባራት መሆናቸውን መረዳት ከመራጮች የሚጠበቅ ዓብይ ተግባር ነው።

በአማራ ክልል ለምርጫው ሰላማዊነት አስፈላጊው ሥራ መከናወኑ እና  የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቂ ዝግጅት ስለመደረጉም የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አሳውቋል። በጸጥታ ችግር ምክንያት የሚስተጓጎል የምርጫ ክልልም ሆነ ጣቢያ እንደማይኖር እና ይልቁንም አስተማማኝ ዝግጅት ስለመከናወኑ ቢሮው አረጋግጧል።

በመሆኑም በክልሉ በምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ምርጫውም በሰላማዊ ሂደት እና በስኬት እንዲጠናቀቅ እና የታቀደው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲከናወን ይቻል ዘንድ ማኅበረሰቡ ያሥተዳድረኛል የሚለውን መሪ በምርጫ  በመለየት ይመርጥ ዘንድ የምርጫ ሂደቱን ደኅንነት በመጠበቅ  ኃላፊነቱን  እና የዜግነት ግዴታውን መወጣት ይጠበቅበታል!።

በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here