ባንኮክ – የዓለም ቱሪዝም መዳረሻ

0
110

ባንኮክ የታይላንድ ዋና ከተማ ስትሆን በዓለም ላይ በጣም በብዙ ጎብኚዎች ከሚጎበኙ ጥቂት ከተሞች መካከል አንዷ ናት። የታሪክ ቅርሶች፣ ዘመናዊ ሕንፃዎች፣ የባህል ማዕከላት፣ የመዝናኛ ስፍራዎችና የተለያዩ የግብይት ማዕከላት በአንድ ላይ በመጣመራቸው ባንኮክ የዘመናዊነትና የባህላዊነት ውህድ ልዩ ከተማ ሆናለች። ይህች ከተማ የታይላንድ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ፣ ባህልና ቱሪዝም ዋና ማዕከል ስትሆን በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን ትቀበላለች።

ባንኮክ በፈጣን እድገቷ የምትታወቅ ቢሆንም ታሪኳንና ባህላዊ ማንነቷን አልተወችም። የቤተመቅደሶቿ ውበት፣ የወንዞቿ ድምቀት፣ የገበያዎቿ እንቅስቃሴና የሕዝቦቿ እንግዳ ተቀባይነት ለጎብኚዎች ልዩ ተሞክሮ ይፈጥራሉ።

የባንኮክ አመሰራረት

ባንኮክ በ1782 ዓ.ም. በንጉሥ ራማ ቀዳማዊ በይፋ የታይላንድ ዋና ከተማ ሆና ተመሠረተች። ከዚያ በፊት አካባቢው ትንሽ የንግድ መንደር ነበር። ከተማዋ በቻዎ ፍራያ ወንዝ አቅራቢያ መገኘቷ ለንግድና ለመጓጓዣ በጣም አመቺ አድርጓት ነበር። ወንዙ በዚያን ጊዜ የንግድ መንገድና የመጓጓዣ መስመር ስለነበር ባንኮክ በፍጥነት የኢኮኖሚ ማዕከል ሆና እንድታድግ አስችሏታል።

ንጉሥ ራማ ቀዳማዊ ዋና ከተማውን ወደዚህ ስፍራ ያዛወረው በፖለቲካና በወታደራዊ አቅም ሀገሪቱን ለማጠናከር ነበር። በዚህም መሠረት መንግሥታዊ ተቋማት፣ ቤተመንግሥቶች፣ ቤተመቅደሶችና የንግድ ማዕከላት ተገነቡ። በቀጣይም ባንኮክ የታይላንድ ዋና የንግድና የባህል ማዕከል ሆና ማደግ ጀመረች።

ባንኮክ “ክሩንግ ቴፕ” ተብላም ትጠራለች። ይህም “የመላእክት ከተማ” ማለት ነው። የከተማዋ ሙሉ ስም በዓለም ላይ ከረጅሞቹ የከተማ ስሞች አንዱ መሆኑም ባንኮክን ለየት ያደርጋታል።

የባንኮክ እድገት

ባንኮክ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ በፍጥነት ያደገች ከተማ ናት። በ19ኛውና 20ኛው ክፍለ ዘመን ከውጭ ሀገራት ጋር የንግድ ግንኙነቷ እየሰፋ በመሄዱ ከተማዋ በኢኮኖሚ በጣም ጠነከረች። የመንገድ፣ የባቡርና የአየር መጓጓዣ መሠረተ ልማቶች በመስፋፋታቸው ባንኮክ የደቡብ ምስራቅ እስያ ዋና የንግድ መዳረሻ ሆነች።

ዛሬ ባንኮክ በረጃጅም ሕንፃዎች፣ በዘመናዊ የገበያ ማዕከላት፣ በታላላቅ ሆቴሎችና በቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች የተሞላች ከተማ ሆናለች። በተመሳሳይ ጊዜ ግን ባህላዊ ማንነቷን አልተወችም። ቤተመቅደሶቿ፣ ባህላዊ ገበያዎቿና የታይ ሕይወት ባህል እስካሁን ድረስ በግልጽ ሁኔታ ይታያሉ።

ባንኮክ የታይላንድ ኢኮኖሚ ልብ ስትሆን በቱሪዝም፣ በንግድ፣ በቴክኖሎጂና በፋይናንስ ዘርፍ ትልቅ ሚና ትጫወታለች። በየዓመቱ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች ወደ ባንኮክ ይመጣሉ። ይህም ከተማዋን በዓለም ከቱሪዝም ማዕከላት አንዷ አድርጓታል።

ሆኖም ፈጣን እድገቷ አንዳንድ ችግሮችንም አስከትሏል። የትራፊክ መጨናነቅ፣ የአየር ብክለትና የሕዝብ ብዛት በከተማዋ የሚታዩ ችግሮች ናቸው። ቢሆንም መንግሥቱ በዘመናዊ መጓጓዣና በከተማ ልማት ላይ በማተኮር እነዚህን ችግሮች ለመቀነስ እየሠራ ይገኛል።

የባንኮክ የቱሪዝም መስህቦች

ባንኮክ በታሪካዊ ስፍራዎች፣ በባህላዊ ቤተመቅደሶች፣ በዘመናዊ የገበያ ማዕከላትና በውብ የመዝናኛ ስፍራዎች የታወቀች ናት።

ታላቁ ቤተመንግሥት

በባንኮክ ውስጥ በጣም የሚታወቅ ታሪካዊ ስፍራ ነው። ለብዙ ዓመታት የታይላንድ ነገሥታት መኖሪያ ነበር። የወርቅ ጌጦቹ፣ የባህላዊ ሕንፃ አወቃቀሩና የጥበብ ሥራዎቹ ቱሪስቶችን በጣም ይማርካሉ።

የእምራልድ ቡዳ ቤተመቅደስ

ዋት ፍራ ካዎ በታይላንድ እጅግ የተከበረ የሃይማኖት ስፍራ ነው። በውስጡ የሚገኘው የእምራልድ ቡዳ ሐውልት በሀገሪቱ ሃይማኖታዊ ታሪክ ታላቅ ቦታ አለው።

የተኛው ቡድሃ ቤተመቅደስ

ዋት ፎ በትልቁ የተኛ የቡድሃ ሐውልት የሚታወቅ ቤተመቅደስ ነው። በተጨማሪም የባህላዊ የታይ ማሳጅ ትምህርት ማዕከል በመሆኑ ብዙ ጎብኚዎች ይጎበኙታል።

የቻኦ ፕራያ ወንዝ

የቻኦ ፕራያ ወንዝ የባንኮክ ሕይወት መሠረት ተብሎ ይጠራል። በወንዙ ላይ በጀልባ መጓዝ የከተማዋን ውበት በቅርብ ለማየት ያስችላል። በሌሊት ጊዜ የከተማዋ ብርሃን በወንዙ ላይ ሲንፀባረቅ እጅግ ውብ እይታ ይፈጥራል።

የተንሳፋፊ ገበያዎች

ዳምኖክ ሳዱዋክ  ገበያዎች እና ሌሎች የተንሳፋፊ ገበያዎች የባንኮክ ባህላዊ የንግድ ሕይወትን ያሳያሉ። ነጋዴዎች ከጀልባ ላይ ፍራፍሬ፣ ምግብና የእጅ ስራዎችን ሲሸጡ ማየት ለጎብኚዎች ልዩ ተሞክሮ ይሰጣል።

ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት

አይኮኒስያም እና ኤምቢኬ ማእከል እንደሚባሉ የገበያ ማዕከላት ለግብይትና ለመዝናኛ በጣም ተወዳጅ ናቸው። እዚህ የዘመናዊ የፋሽን ልብሶች፣ ኤሌክትሮኒክስና ባህላዊ ዕቃዎች በስፋት ይገኛሉ።

የባንኮክ ባህልና ምግብ

ባንኮክ በልዩ የምግብ ባህሏ በዓለም ታዋቂ ናት። በተለይ የመንገድ ምግቦቿ ብዙ ቱሪስቶችን ይማርካሉ። ፓድ ታ፣ ቶም ዩም እና የተለያዩ የባህር ምግቦች በጣም ተወዳጅ ናቸው።

ከምግብ በተጨማሪ የታይ ባህላዊ ዳንስ፣ ሙዚቃና የጥበብ ሥራዎች የከተማዋን ውበት ያጎላሉ። በየሌሊቱ የሚካሄዱ የመዝናኛ ዝግጅቶችም ባንኮክን የማትተኛ ከተማ አድርጓታል።

ባንኮክ የታሪክ፣ የባህልና የዘመናዊ ልማት ተዋህዶ የተገነባች ታላቅ ከተማ ናት። ከታሪካዊ ቤተመንግሥቶች እስከ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት፣ ከባህላዊ ገበያዎች እስከ ውብ ወንዞች ድረስ ለጎብኚዎች የማይረሳ ተሞክሮ ትሰጣለች። በዚህ ምክንያት ባንኮክ በዓለም የቱሪዝም ካርታ ላይ የተለየ ቦታ ይዛ ቀጥላ ትገኛለች።

አጫጭር እውነታዎች

  • ዋና ከተማዋ ባንኮክ ናት።
  • የሀገሪቱ ሕዝብ ከ70 ሚሊዮን በላይ ነው።
  • ዋና ቋንቋዋ ታይ ቋንቋ ነው።
  • የሀገሪቱ ገንዘብ “ባህት” (Baht) ተብሎ ይጠራል።
  • ታይላንድ በአስደናቂ የባህር ዳርቻዎች፣ ደሴቶች እና ቱሪዝም በጣም ታዋቂ ናት።
  • Phuket እና Pattaya በቱሪስቶች በጣም የሚጎበኙ ቦታዎች ናቸው።
  • የሀገሪቱ ዋና ሃይማኖት ቡድሂዝም ነው።
  • ታይላንድ “የነፃነት ሀገር” ተብላ ትታወቃለች፤ ምክንያቱም በቅኝ ግዛት ያልወደቀች ከጥቂት የእስያ ሀገራት አንዷ ናት።
  • የታይ ምግቦች በቅመም እና በልዩ ጣዕማቸው ይታወቃሉ፤ Pad Thai በዓለም የታወቀ ምግብ ነው።
  • በሀገሪቱ ብዙ የዝሆን ጥበቃ ማዕከላት አሉ፤ ዝሆንም የታይላንድ ባህላዊ ምልክት ነው።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር የግንቦት 3 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here