እያንዳንዱ ልጅ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ አብሮት የሚመጣ የራሱ የሆነ ልዩ ተሰጥኦ እና ዝንባሌ አለው። ይህ ተሰጥኦ ገና በለጋ ዕድሜ የሚታይ ፍንጭ ሲሆን በትክክል ከተያዘ እና ድጋፍ ከተደረገለት ለልጁ የወደፊት ስኬት ወሳኝ መሠረት ይሆናል። ተሰጥኦን ለይቶ ማወቅ እና ማሳደግ ደግሞ ከማንም በላይ የወላጆች ቀዳሚ ኃላፊነት ነው።
ልጆች ተሰጥኦአቸውን ሁልጊዜ በግልጽ ላያሳዩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በሚያሳዩት የማወቅ ጉጉት፣ በሚመርጧቸው ጨዋታዎች እና ለተወሰኑ ነገሮች በሚሰጡት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥኦአቸውን መረዳት ይቻላል። አንዳንዶች በስዕል፣ ሌሎች በንግግር፣ አንዳንዶች ደግሞ ነገሮችን በመገጣጠም እና በመፍታት ረገድ ልዩ ችሎታ ሊኖራቸው ይችላል። ወላጆች ልጆቻቸው ነፃ ሆነው የተለያዩ ነገሮችን እንዲሞክሩ ዕድል መስጠት እና ምርጫቸውን በትዕግሥት መታዘብ ይኖርባቸዋል።
የወላጆች እገዛ ሲባል ቁሳቁስ ማሟላት ብቻ አይደለም። ከሁሉ አስቀድሞ የልጁን ፍላጎት ማክበር እና የሥነ-ልቦና ድጋፍ መስጠት ዋናው ተግባር ነው። ብዙ ጊዜ ወላጆች የራሳቸውን ያልተሳካ ምኞት በልጆቻቸው ላይ ለመጫን ሲሞክሩ ይታያሉ። ነገር ግን እውነተኛ እገዛ ማለት ልጁ በደመ ነፍስ የሚሳብበትን ዘርፍ አውቆ ያንን እንዲያለማ ማበረታታት ነው።
ልጁ በጀመረው የፈጠራ ሥራ ወይም ሙከራ ላይ ስህተት ቢሠራ እንኳ ተስፋ እንዳይቆርጥ ማገዝ እና ጥረቱን ማድነቅ ለተሰጥኦው እድገት ትልቅ ጉልበት ይሆነዋል። በተጨማሪም ለተሰጥኦው እድገት የሚረዱ መጻሕፍትን፣ መሣሪያዎችን ወይም አጫጭር ሥልጠናዎችን ማመቻቸት የልጁን አድማስ ያሰፋለታል።
ተሰጥኦ እንደ ተክል ነው። ተክሉ እንዲያድግ ውኃ እና እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ሁሉ የልጆች ተሰጥኦም እንዲያብብ የወላጆች ያልተቆጠበ ድጋፍ እና ፍቅር ያስፈልገዋል። ወላጆች የልጆቻቸውን ልዩ ችሎታ አውቀው ካገዙ ልጁ ለራሱ የሚኖረው ግምት ከፍ ይላል፤ ለሀገር እና ለዓለም የሚተርፍ ትልቅ ሰው የመሆን ዕድሉም ሰፊ ይሆናል ይላል አሜሪካን ሳይኮሎጂካል አሶሴሽን ላይ ያገኘነው መረጃ።
ተረት
ቀበሮ እና የወይን ዘለላ
ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት የተራበች ቀበሮ ምግብ ፍለጋ ስትዘዋወር በአንድ አጥር ላይ ተንጠልጥለው የሚታዩ በጣም የሚያምሩ እና የበሰሉ የወይን ዘለላዎችን አየች። ወይኖቹ በጣም ያጓጓሉ፤ ቀበሮዋም “እነዚህንማ በልቼ ረሃቤን መቁረጥ አለብኝ” ብላ አሰበች።
ቀበሮዋ ወይኑን ለመቅጠፍ ወደ ላይ ዘለለች፤ ነገር ግን ወይኑ የተንጠለጠለበት ቦታ በጣም ረጅም ስለነበር ልትደርስበት አልቻለችም። ደጋግማ ሞከረች፤ በኃይል ዘለለች፤ ወደ ኋላ ራቅ ብላ እየሮጠች መጥታ ብትዘልም ፈጽሞ ልትነካው አልቻለችም።
በመጨረሻም ቀበሮዋ በጣም ደከማት እና ተስፋ ቆረጠች። አፍንጫዋን ወደ ላይ ሰቅላ ወደ ሌላ ቦታ እየሄደች “ይህ ወይን እኮ ገና አልበሰለም፤ እንዲያውም በጣም ኮምጣጣ ነው፤ ባልበላው ይሻለኛል” አለች ይባላል። ብዙ ሰዎች አንድን ነገር ለማግኘት ጥረው ሳይሳካላቸው ሲቀር ያንን ነገር እንደማይረባ እና እንደማይጠቅም አድርገው ያጣጥሉታል።
ሞክሩ
- አንድ አባት ለሁለት ልጆቹ 10 ብር ሰጠ። አንደኛው ልጅ ከሌላኛው በ2 ብር ይበልጣል፤ ታዲያ ለእያንዳንዱ ስንት ስንት ሰጣቸው?
- በሩጫ ውድድር ላይ ሁለተኛ የነበረውን ሰው ቀደምከው፤ አሁን ስንተኛ ሆንክ?
- ስትወስድለት የሚተልቅ፣ ስትጨምርለት የሚያንስ ምንድን ነው?
መልስ
- 6 ብር እና 4 ብር
- ሁለተኛ
- ጉድጓድ
ነገር በምሳሌ
-ሰባት ጊዜ ውደቅ፤ ስምንት ጊዜ ተነሳ፡-ውድቀት መጨረሻ አይደለም፤ ዋናው ቁምነገር ተስፋ ሳይቆርጡ እንደገና መሞከር ነው።
-አንድን ሰው ዓሣ ከሰጠኸው ለአንድ ቀን ይመገባል፤ ዓሣ ማጥመድ ካስተማርከው ግን ለሕይወት ዘመኑ ይመገባል፦ ዕውቀት መስጠት ከጊዜያዊ እርዳታ ይበልጣል ማለት ነው።
-“አንድን ልጅ ለማሳደግ መንደር ሙሉ ያስፈልጋል፦ የአንድ ልጅ ስኬት እና መልካም ስነ-ምግባር የቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡም የጋራ ኃላፊነት ነው።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


