ጠይም ናት ደግሞም ከቁመቷ አጠር ትላለች፣ ቢሆንም ግን ነብሱን ይማረውና ባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋዬ አያ ሙሌ “ለዓይን ባልሞላም ለነብስ እደርሳለሁ” እንደሚለው ለዓይን ባትሞላም ለነብስ ትደርሳለች ማን? እስከዳር።
መኖር እዳው ገብስ ነውና የፈተገ ሁሉ እንደፈለገ ከሰፌድ እየዘገነ አይቅመውም፤ እስከዳርም መኖርን በገደምዳሜው ኑራዋለች ሲከፋትም ሲደላትም። ነብሱን ይማረውና ባለቅኔው ጸጋዬ ገብረመድኅን:-
“እኔስ ኑሬዋለሁ ሲከፋኝ ሲደላኝ፣
ከእንግዲህ ተዎልዶ ሰው ለሚሆን ይብላኝ፤”
እንዳለው ዓይነት መሆኑ ነው።
እስከዳር በስራዋ የህግ ጠበቃ ናት። ደግሞም ቀደም ባለው ጊዜ ጥቁር ጋዎን ደርባ፣ መዶሻ ጨብጣ ከጠረጴዛ ጋር ስታዋድድ ቆይታለች። ህግ እንዲከበር ፈቃዷ ብዙ ቢሆንም ይሄ ሃሳቧ አንዴ ሲሳካላት ሌላ ጊዜ ደግሞ ጉም ሆኖ እንደ ደመና ሲበተንባት ኖሯል። በሩቅ የሚያውቋት “እስከዳር” ይሏታል የቅርቦቿ ደግሞ “እስኩ” ይሏታል ወዳጆቿስ ደግሞ የተባለ እንደሆን “እስኩቲ” ይሏታል። እሷ እንደሆነ ለሁሉም “ለበይክ” ከማለት እና እንጀራ በስሱ ቆርሶ ከመብላት በቀር የምታውቀው ነገር የላትም። ወይ ጉድ አማርኛ ሲተባ ቋንቋ ሲተረማመስ እና እንደ አሸን ሲፈላ መገረም ነው! ስንት ቀለም የዘለቃትን ልጅ የምታውቀው የላትም ማለት ምን ማለት ነው? ተረጋጉ ወገኖቼ ለአገላለጽ ያመች ዘንድ ነው እንጂ ማንስ ቢሆን ማን ሰው ሆኖ እስከተፈጠረ ድረስ ብዙውን የውቃል፤ ጥቂቱን ይረዳል በጣም ጥቂቱን ደግሞ በተግባር ተርጉሞ ይኖረዋል።
እስከዳር ያደገችው ላለመሸነፍ ስትጥር ስትፍጨረጨር ነው። የሰው እድገቱ ልዩ ልዩ ነው። በአካል፣ በአእምሮ እና በመንፈስ ያድጋል። የታደሉት ሶስቱን አዋህደው ያስኬዱታል። ይሄን አስመልክቶ እስከዳር አንድ የምትለው አባባል አላት “ ህይዎት ቅጥልጥል ናት፤ አንዱ ባንዱ ይደገፋል” ትላለች። ጋንን ያህል ትልቅ ነገር በጠጠር ሲደገፍ ስላየች።
መከታተል፣ መቀጣጠል እና መነጣጠል የህይዎት ቋሚ ህጎች የሆኑ ይመስል መከሰታቸው ይደጋገማልሳ? ደግሞስ አንዱ አንዱን ሲጠራ በሌላ አገላለጽ ለማለት ያህል ሲያስከትል መኖሩ እጅግም ያስገርማል። ትዳር መመስረት ከዛም ልጆች መውለድ ይከተላል፣ ልጆችን ማሳደግ ይቀጥላል ከዛም ማለቂያ የለውም፤ ኑረት ከትውልድ ጅረት ጋር እየተናነቀ ቁልቁል ይፈተለካል። አንዱን ሲይዙ ደግሞ አንዱን ሲለቁ፤ ማጣት እና ማግኜትን በተራ ሲያስተናግዱ መኖር ነው።
“ከባዱ ነገር አይቀልም ነገር ግን ተሸካሚው ይጠነክራል” ትላለች እስከ-ዳር። “መወለድ ለመኖር ነው ካልሆነም ለመሞት ነው” ስትልም ታክላለች። የት እንዳነበበችው አታስታውሰውም ነገር ግን በየነገራቶቿ መሃል ላይ ቀላቅላ ትጠቀምባቸዋለች ያው ነገርን ለማሳመር ያህል። አንዳንድ ነገሮች አይከብዱም ነገር ግን የሰው አረዳድ ያከብዳቸዋል። ለምን ቢሉ ሰው ያልበላውን ማከክ ስለሚወድ ነው የሚል ይሆናል መልሱ። ታዲያ ሰውን በጅምላ መፈረጅ ነውር ከመሆኑም በላይ እንደ እስከዳር አይነት በስነ-ስርዓት የተማረ ጠበቃ ካገኘዎትም ዘብጥያ ሊወርዱ ይችላሉ። መገን! የየሰው ሁሉ ሃብቱ ልዩ ልዩ ነው አሉ! መቼስ ለመገረም ሩቅ መጓዝ አያስፈልግም ደግሞም ለመደሰትም ዓይንን ጨፍኖ ትንሽ አሰብ ማድረግ በቂ ነው።
እስከዳር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለስራ ተመድባ ከጎንደር ከተማ በቅርብ ርቀት ወደ ምትገኝ አንዲት የወረዳ ከተማ መጥታለች። ከተማውን ለመልመድ በምትፍጨረጨርበት ወቅት አንድ የህግ ኬዝ ያጋጥማታል። ጉዳዩ እንዲህ ነው አንዲት የአስራምስት ዓመት መናገር የማትችል ታዳጊ ተደፍራ ፍትሕ ለማግኜት ወደ ፍርድ ቤት ትመጣለች። ጉዳዩን ለመከታተል ደግሞ እስከዳር ቅድሚያ ፍላጎት በማሳየቷ እና ደግሞም በስራዋ የተመሰከረላት በመሆኗ ጉዳዩን መከታተል ትጀምራለች። ጉዳዩን ተከታትላ የህግ ውሳኔ ብታሰጥበትም ነገር ግን በታዳጊዋ ላይ የደረሰው ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ለማከም ልጂቱን መንከባከብ ትጀምራለች። እስከዳር ከህግ ባለሙያነቷ ባንዴ ወደ ህክምና እና ስነ-ልቦና ባለሙያነት ለመሸጋገር ግብግብ ጀመረች።
ታዳጊዋን አዲስ ስም አወጣችላት። ወትሮ በዘፍጥረት እንደተገለጸው ስም የማውጣት ስራ የአዳም ነበረ ዘንድሮ እስከዳር የተጋራችው ይመስለኛል። ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ ጉደኛዋ እስከዳር ስሟን ማን ብላት ይሆን? ለመጠየቅ የደፈረ ካለ ይጠይቅ! ለማንኛውም ሃገር ብታጣ ብታጣ አንድ ልባም አታጣምና እኔ ደፍሬ ጠየኩ እንዲህ መለሰችልኝ፦ “ስሟን መልዓክ ሹክ ብሎኝ እኔ ነኝ ያወጣሁላት፤ ‘እስከ-ዳር’ ብያታለሁ።” አለችኝ ያው በሌላ አገላለጽ ስሟን አጋራቻት ማለት ነው። “ምንም ነገር ዳር አለው” አለች እስከዳር።
ደግሞ ቀጥላ እንዲህ ታብራራለች “አንዳንዴ ከአንድ ተራራ ቁመን የምናየው የአድማስ ጥግ ተጠግተን ደግሞ ስናዬው ሌላ የአድማስ ጥግ አለው ስለዚህ የህይዎትንም ጥጓን ማግኘት ይከብዳል። ለበጎ ያሉት ከሞት አፋፍ ይጥላል፤ ክፉ ነው ያሉት አጋጣሚ ደግሞ ህያው ያደርጋል። ምንም ነገር ጨርሶ ሊታዎቅ አይችልም ነገሩ ለመታዎቅ ከባድ ላይሆን ይችላል ነገር ግን የሰው ልጅ የማዎቅ እና የመረዳት ውስንነት ነው ገደቡ።
ይች ሞክሼዬ እስከዳር ብዬ የሰየምኳት ታዳጊም ነገ ከነገ ወዲያ እያንዳንዱን የአድማስ ጥግ እስከ-ዳር እንድታካልል እፈልጋለሁ። ፍላጎት ብቻም ሳይሆን ክንውኑን ለማዬት ነው የምለፋው። የምደክመው ለሷ ብቻ አይደለም ለኔም ነው። እድሜዬ ይገፋል ምናልባት የተመኘሁትን ሃብት፣ ዝና እና ሌሎችንም ነገሮች አገኝ ይሆናል ነገር ግን ከዚህ ከተማ ስዎጣ ብቸኛው ትውስታዬ የሁለት እስከዳሮች የህይዎት ውጣውረድ ጣጣ ይሆናል።” አለች እስከዳር። ጥሩ ታብራራለች ነገር ግን ትፈጥናለች።
እስከዳር ጸጉሯን ባጭሩ መቆረጥ እና ፍሪዝ ማድረግ ይመቻታል። ምናልባት ሃይል እንደ ሶምሶን በጸጉሯ ተሰጥቷታል ብሎ ሰው እንዳያማት እና እንደ ደሊላ ያለች አንዲት መሰሪ እንዳታቃጥርባት ፈርታም ይሆናል። በርግጥ እሷ ፍርሃት አያውቀኝም ትላለች። ነገር ግን በጥልቅ ሲመረመር አለመፍራት በራሱ ትንሽ ፍርሐት አለበት። ለምን ቢሉ መልሱ ግልጽ ነው ሰው አለመፍራትን የሚመርጠው መፍራትን ስለሚፈራ ነዋ! ነገር ግን ወዳጆቼ ፈጣሪን መፍራት ጥበብ እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ያትታል።
እስከዳር መፍጨርጨር ትወዳለች በትርፍ ጊዜዋ ዳንቴል ትሰራለች። በርግጥ ዳንቴሎቹ ለራሷ ስካርፍ እና ኮፍያ ከመስራት ባይዘልም ነገር ግን በደምብ ትሰራለች። ይሄን ሙያዋን ለሞክሼዋ እስከዳር ለማስለመድ ብዙ ጥራለች ነገር ግን “ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ” እንዲሉ ታዳጊዋ እስከዳር በአሁኑ ወቅት አስተማሪዋን በልጣታለች። እስከዳር በርግጥም የታዳጊዋን እስከዳርን ስነ-ልቦና ለማከም የቻለች ትመስላለች። ነገር ግን በየቤቱ ያሉ የታናሿ እስከዳር አይነት ታሪክ ተጋሪዎች ብዙ ናቸው። እነሱን መታደግ እና መንከባከብ ከዚህም ሲያልፍ ስምን ጭምር ሳይሰስቱ ማጋራት ከታላቁ እስክንድር ሳይሆን ከልባሟ እስከዳር የምንማረው ተግባር ነው። እኔ በበኩሌ የቤት ስራዬን ወስጃለሁ። እናመሰግናለን እስከ-ዳር።
መረፊያ
እማማ
የማንነቴ መለኪያ ኩራቴ መመኪያዬ ክብሬ፣
የሦስት ሺህ ዓመት እመቤት አንድ ናት ኢትዮጵያ ሀገሬ!
እቴ አንቺ የኔ ሙሽራ ሀገሬ እስኪ ልጠይቅሽ፣
ያገቡሻል ይፈቱሻል ያጩሻል አሁንም ድንግል ነሽ!
ከክብርሽ በታች ወደቁ ነገስታት በፍቅርሽ ተነድፈው፣
ደናግላን መነኑልሽ ዓለምን ደስታቸውን ጥለው!
እማማ እናት ኢትዮጵያ፣
እማማ አንቺ እናት አለም!
ዘመን አመጣሽ የዘር በሽታ፣
መድኃኒት አለው የማታ ማታ፣
ሀገር በወገን እንዴት ይረታ፣
ፍቅር በነገር እንዴት ይፈታ!
ዘር ሳይለያየን ወይ ሐይማኖት፣
ከጥንት በፍቅር የኖርንባት!
እናት ኢትዮጵያ ውዲት ውዲቷ፣
በጎጆ አያልቅም ሙሽርነቷ!
እማማ!
(ድምጻዊት እጅጋየሁ ሺባባው)
(ደረጀ ደርበው)
በኲር የግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


