በቻይና ደቡብ ምእራብ በዊክሲ ግዛት 137 የቲያንፒንግ ማህበረሰብ አባላትን ከቀሪው ዓለም ጋር ለማገናኘት ከተገነባው ሦስት ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትር ከሚረዝመው 453 ሜትር የተላካው ጠመዝማዛ መንገድ አስቸጋሪ እና አስፈሪነቱን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
የሊንግፓይሹ የጠጠር መንገድ 18 ስለታም ጠባብ መታጠፊያዎች ወይም ማዞሪያዎች አሉት መታጠፊያዎቹ ልምድ ያላቸው አሽከርካሪዎችን ሳይቀር በእጅጉ ፈታኝ መሆናቸውም ነው የተገለፀው፡፡
አስቸጋሪውን የአውራ ጐዳና መንገድ ለመስራት በአደገኛ እና አድካሚ ሁኔታ አቀበት ቁልቁለቱን ሲወጡ እና ሲወርዱ ላሳለፉት የ “ሚንዙ” መንደር የማህበረሰብ አባላት መሰረተ ልማት መገንባት ግድ ማለቱን ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡በገደል እና ገደል ወይም በሁለት ግራ እና ቀኝ በቆሙ አቀበቶች መካከል የሚተጣጠፈው የጠጠር መንገድ ተሽከርካሪዎች በዝግታ እንዲጓዙ የአሽከርካሪዎችን ጥንቃቄ የሚሻ እና ብቃታቸውንም ፈታኝ መሆኑ ነው የተጠቀሰው፡፡
የተገነባው የጠጠር መንገድ በጣም ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ ተሽከርካሪዎችን ጐን ለጐን ማስተላለፍ አይችልም፤ ረዣዥም ወይም ተሳቢ ያላቸውም ለመጓጓዝ ይቸገራሉ፤ አይፈቀድላቸውምም፡፡ ከሁሉም በላይ 453 ሜትሩ በጠመዝማዛነቱ የተለየው፣ አነስተኛ ተሽከርካሪዎችን ብቻ ነው የሚያስተናግደው፡፡
የአውራ ጐዳናው ወይም በጠጠር የተሰራውን የተሽከርካሪ መንገድ ለመውጣት አቀበትነቱ፣ ቁልቁል ለመውረድ ተዳፋታማነቱ የሰላ በመሆኑ አነስተኛ ተሽከርካሪዎችንም በአንደኛ ማርሽ መጓዝ ግድ እንደሚላቸው ነው ድረ ገጹ ያስነበበው፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።


