ቡና አዘውትሮ መጠጣት የአንጀት እና አንጐል ግንኙነትን በማሻሻል፣ የመንፈስ ጭንቀትን በመቀነስ የማገናዘብ እና የማስታወስ ዓቅምን ማሳደግ የሚያስችል የጤና ጥቅሞች ያሉት መሆኑን ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን ለንባብ አብቅቶታል፡፡
በአየርላንድ የኮርክ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ተመራማሪዎች ቡና ከሆድ – አንጐል ዘንግ (ገት- ብሬይን – አክሲስ) እንዴት እንደሚገናኝ በጥልቀት ፈትሸዋል፡፡ በምርምራቸውም ረቂቅ ተህዋስያኑ ጭንቀትን በመሰሉ ስሜቶች ላይ ተፅእኖ እንደሚያሳርፉ ደርሰውበታል፡፡
ተመራማሪዎቹ የተጠቀሰው ድምዳሜ ላይ ለመድረስ በ31 ቋሚ ቡና ጠጪዎች እና 31 ቡና የማይጠጡ ተሳታፊዎች መካከል የስነልቦና፣ የምግብ አቀባበል እና የቡና አወሳሰዳቸውን ተከታትለዋል፡፡ ተመራማሪዎቹ ከናሙና ጥናት ተሣታፊዎቹ በአንጀት ባክቴሪያ እና ስሜታዊ ለውጦችን ለመገንዘብ የሰገራ እና የሽንት ናሙናዎችንም በግብአትነት ተጠቅመዋል፡፡
ምርምሩ ከሦስት እስከ አምስት ኩባያ ቡና የሚጠጡትን የማያካትት ሲሆን ይህ መጠን በአውሮፓ የምግብ ደህንነት ባለስልጣን ደህንነቱ የተጠበቀ መካከለኛ መጠን ተደርጐ እንደሚወሰድም ነው የተገለፀው፡፡
በማጠቃለያነት በዩኒቨርስቲው የጥናት ምርምሩን የመሩት ኘሮፌሰር ጆን ክራያን “ካፊን” ያለውም ሆነ “ ካፊን” የሌለው ቡናን መጠጣት ጭንቀትን ከመቀነስ እና ንቁነትን ከመጨመር ባሻገር ለትክክለኛ የምግብ መፈጨት አብርክቶው የላቀ መሆኑን በመግለጽ ነው ያደማደሙት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።


