በራስ መተማመኑ እንዴት ይጎልብት?

0
82

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት እና የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ “ትምህርት ዓለምን ለመቀየር የሚያስችል እጅግ ኃይለኛ መሣሪያ ነው” በሚል ለትምህርት ያላቸውን የገዘፈ ስሜት ገልጸውታል። በሌላ በኩል “ፍርሃት የወደፊት ሕይወትህን እንዲወስን አትፍቀድ” ሲሉም ነው የጭንቀትን (የፍርሃትን) አፍራሽ መዘዝ ያስገነዘቡት።

በተመሳሳይ ዳላይ ላማ የተባሉ የስነ ልቦና ምሁር “የተረጋጋ አእምሮ ውስጣዊ ጥንካሬንና ራስ መተማመንን ያመጣል” ይላሉ። አባባላቸው ደግሞ በተለይ ተማሪዎች በፈተና ወቅት ጠንካራ የስነነልቦና ዝግጅት እንዲኖራቸው ትኩረቱን ያደረገ ነው።

በሃገራችን ሰኔ ወር ትምህርት ቤቶች የዓመቱን ትምህርት የሚያጠቃልሉበት፣ የማጠቃለያ ፈተናም የሚሰጥበት፣ በተለይ ደግሞ ብሔራዊ ፈተና የሚሰጥበት መሆኑ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል።

የ2018 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰኔ ወር እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። ብሔራዊ ፈተና ደግሞ ለተማሪዎች የትምህርት ዕውቀታቸውን ብቻ ሳይሆን የስነ ልቦና ዝግጅታቸውንም የሚፈትን አስፈላጊ የሕይወት ደረጃ ነው። ብዙ ተፈታኞች በፍርሃት፣ በጭንቀት እና በራስ መተማመን እጥረት ምክንያት ያላቸውን ዕውቀት በአግባቡ ማሳየት ይቸገራሉ።

ስለዚህ ከትምህርት ዝግጅት ጋር ተያይዞ የአዕምሮ መረጋጋት፣ ጥሩ አመለካከት እና ራስን መቆጣጠር በፈተና ውጤት ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ጠንካራ የስነ ልቦና ዝግጅት ተፈታኞች በራስ መተማመን እንዲፈተኑ፣ ጭንቀትን እንዲቀንሱ እና የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ያግዛቸዋል።

እኛም የተማሪዎችን የስነ ልቦና ዝግጅት በተመለከተ የሚመለከታቸውን አነጋግረናል።

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ነሲቡ በላይነህ ለፈተና እንዴት መዘጋጀት እንዳለበት የስነ ልቦና ስልጠና አግኝቷል። “ከዚህ በፊት ለፈተና በብዙ መንገዶች ራሴን ለማዘጋጀት ጥረት አድርጌያለሁ። ካገኘሁት ስልጠናው በኋላ ደግሚ ትምህርትን ማንበብ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ተረድቻለሁ” ነው ያለን። ተማሪው እንደነገረን ስልጠናው በቀረው አጭር ጊዜ እንዴት በአግባቡ ማጥናት እንዳለበት እና በፈተና ጊዜም አረንዴት ተረጋግቶ መሥራት እንዳለበት ተሞክሮ ሰጥቶታል።

ሌላዋ ሐሳቧን ያካፈለችን በዚሁ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ ትዕግስት ዳኘው ናት፤ እርሷም እንደ ተማሪ ነሲቡ የስነ ልቦና ግንባታን በተመለከተ ስልጠና ወስዳለች፤ ስልጠናው በራስ መተማመኗን እንዳጠናከረውም ተናግራለች። “እስካሁን በበቂ አላነበብኩም፤ ከእንግዲህ በኋላ ባነብም አይሳካልኝም የሚል ስሜት መኖር እንደሌለበት ተረድቻለሁ፡፡ ቀሪውን ጊዜ በመጠቀም እንዴት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ተምሬበታለሁ” ብላለች።

በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የአዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ ሰላማዊት ሀብታሙም በስልክ ተሞክሮዋን አካፍላናለች፡፡ ተማሪዋ እንዳለችው ሀገር አቀፍ ፈተናን በተመለከተ ከማንበብ በተጨማሪ ምን አይነት ስነ ልቦናዊ ዝግጅት ሊኖር እንደሚገባ ስልጠና አግኝታለች፤ ይህ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ጥቅምን አስገኝቶላታል፡፡

ከስልጠናው በፊት የጊዜ አጠቃቀሟ የተዛባ እንደነበርና ይህም በራሷ ላይ ጭንቀት ፈጥሮባት ነበር። ከስልጠናው በኋላ ግን ጊዜዋን በአግባቡ መጠቀም እንደቻለች ነው የነገረችን፤ ለዚህ ማሳያ ደግሞ የሞዴል ፈተና ውጤቷ በእጅጉ መሻሻሉን ነው ያነሳችው።

“ያለኝ ጊዜ በቂ እንደሆነ ተረድቻለሁ፤ በራሴም ተማምኜ ለፈተናው መዘጋጀት ጀምሬያለሁ” ብላለች።

ሌላው የዚሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪ ጌራወርቅ አበበ በበኩሉ፤ ለፈተናው በቂ ዝግጅት ማድረጉን ነግሮናል፤ ይን እንጂ ስለ ብሔራዊ ፈተናው ሲያስብ እንደሚጨናነቅ አልሸሸገም።

ይህ በእንዲህ እንዳ ታዲያ በትምህርት ቤቱ የተሰጠው የስነ ልቦና ግንባታ ስልጠና በራስ መተማመኑን አዳብሮለታል፤ ይህም መነቃቃትን ፈጥሮለታል፡፡ ብሔራዊ ፈተናውንም ያለ ምንም ጭንቀት እንደሚፈተን ተናግሯል።

በጣና ሐይቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማር ማስተማር ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ደረጀ ከፋለ እንዳስታወቁት 946 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለሁለት ተከታታይ ቀናት የስነ ልቦና ስልጠና ወስደዋል። ይህም በተማሪዎች ላይ በግልጽ የሚታይ እና ውጤት ያስገኘ መነቃቃትን ፈጥሯል።

ምክትል ርዕሰ መምህሩ አክለውም ስልጠናው ተማሪዎች ለፈተና ዝግጁ እንዲሆኑ፣ ያለምንም ጭንቀት እንዲፈተኑ እንዲሁም የተሸለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳው ገልጸዋል።

በደብረ ማርቆስ አዲስ ዓለማየሁ ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ደረጀ ከፈለኝ በበኩላቸው፤ ተማሪዎችን በዕውቀት ብቻ ሳይሆን በስነ ልቦናም ማዘጋጀት ለተሻለ ውጤት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ለትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የስነ ልቦና ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል።

እንደ ርዕሰ መምህሩ ገለጻ፤ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ ትምህርት ቤቱ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከ500 በላይ ውጤት የሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ቁጥር እያደገ ነው። በቀጣይም የስነ ልቦና ስልጠናው ከመፈተኛ ጊዚያቸው ቀደም ብሎ በሁሉም የክልሉ ትምህርት ቤቶች ቢሰጥ ብዙ ውጤታማ ተማሪዎችን ማፍራት ይቻላል ነው ያል፡፡

እሱባለው ይርጋ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የስነ ልቦና አሰልጣኝ ናቸው፤ መምህሩ እንዳስገነዘቡት ተማሪዎች ውጤታማ እንዳይሆኑ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል በራስ አለመተማመን፣ ፈተናን አግዝፎ ማየት እና ራስን ዝቅ አድርጎ መገምገም ዋነኞቹ ናቸው።

“ብዙ ተማሪዎች ጠንክረው ቢያነቡም ለራሳቸው ያላቸው አመለካከት ዝቅ ካለ የሚፈልጉትን ውጤት ማምጣት አይችሉም” ያሉት ባለሙያው፤ የስነ ልቦና ዝግጅት ለተማሪዎች ስኬት ትልቅ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ስልጠናው በአራት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈለ ነው፤ የመጀመሪያው ተማሪዎች ስለራሳቸው ያላቸውን አመለካከት ማስተካከልና የተደበቀ አቅማቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ውጤታማ የአጠናን ስልቶችን ማስተዋወቅ ሲሆን፣ ሦስተኛው ስልክና ማሕበራዊ ሚዲያን ለትምህርት ዓላማ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳይ ነው።

አራተኛው ክፍል ደግሞ የጭንቀት ቁጥጥርና የጊዜ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል። ተማሪዎች በፈተና ዕለት እንኳን ምን ማድረግ እንዳለባቸውና ከምን መቆጠብ እንዳለባቸው በስልጠናው ውስጥ መካተቱንም ጠቁመዋል።

ባለሙያው አክለውም፤ ጠንካራ ትውልድ ለመፍጠር በተማሪዎች ላይ መሥራት የሁሉም ማሕበረሰብ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸው፣ የስነ ልቦና ስልጠናዎች በክልል ደረጃ በስፋት ተደራሽ ቢሆኑ በተማሪዎች ውጤታማነት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚመጣ ተናግረዋል።

 

መረጃ

ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የአዕምሮ እና የስነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ ትልቅ ሚና አለው፡፡ ተማሪዎች ውጤታማ ለመሆን የሚከተሉትን ዋና ዋና የስነ ልቦና ዝግጅቶች ማድረግ እንዳለባቸው የዘርፉ ምሁራን ይመክራሉ፡-

  1. ግብን መወሰን

ተማሪዎች “ምን ለመሆን እፈልጋለሁ? “ለምን እማራለሁ?” የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ ይገባቸዋል፡፡ ግብ ያለው ተማሪ በቀላሉ አይደክምም፤ ችግርንም ይቋቋማል፡፡

  1. በራስ መተማመን

“እችላለሁ” የሚል አስተሳሰብ ለተማሪዎች ትልቅ ኃይል ነው፡፡  ስህተት ሲፈጠር “በቀጣይ የተሻለ እሠራለሁ” ብለው መነሳሳት ያስፈልጋል፡፡

  1. ውጥረትን መቆጣጠር ጭንቀትን ለመቀነስ፦

በጊዜ ማጥናት፣ እረፍት መውሰድ፣ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ከቤተሰብ እና ከጓደኞች ጋር መወያየት እንዲሁም ጥሩ እንቅልፍ መተኛት አስፈላጊ ናቸው፡፡

  1. ትኩረት ማዳበር

የጥናት ሰዓት ሲሆን ስልክ፣ ማሕበራዊ ሚዲያ እና ሌሎች አላስፈላጊ ነገሮችን ማራቅ አለባቸው፡፡ የተወሰነ የጥናት ቦታና ጊዜ መኖሩም ትኩረትን ያጠናክራል፡፡

  1. ጊዜን በአግባቡ መጠቀም

የጊዜ አስተዳደር የስኬት ቁልፍ ነው፡፡ ተማሪዎች የቀን እቅድ በማዘጋጀት ምን መቼ እንደሚያጠኑ መወሰን አለባቸው፡፡

  1. ከውድቀት መማር

ውድቀትን እንደ መጨረሻ ሳይሆን እንደ ትምህርት መመልከት ያስፈልጋል፡፡ የተሳሳቱበትን በመገምገም  የተሻለ ዝግጅት ማድረግ ይችላሉ፡፡

ምንጭ፡- ዩኒሴፍ።

 

(ሰናይት በየነ)

በኲር የግንቦት 10  ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here