ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት

0
130

የአቮካዶ ምርት ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ እና የጤና በረከት ካላቸው የፍራፍሬ ዓይነቶች አንዱ ነው። በአሁኑ ወቅት መንግሥት እና የተለያዩ የግብርና ፕሮጀክቶች አርሶ አደሮች የተሻሻሉ ዝርያዎችን በስፋት እንዲያመርቱ እያበረታቷቸው ነው፡፡

የአቮካዶ ልማትን በማዘመን የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በትኩረት እየሠራ ይገኛል። ሀገር አቀፍ የአቮካዶ ልማት ኢኒሼቲቭ ከሚተገበርባቸው ክልሎች መካከል አንዱ በሆነው በአማራ ክልል የአቮካዶ ልማትን ማስፋፋት ይቻል ዘንድ ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ተቀርጾ በይፉ ተጀምሯል። የክልሉ ግብርና ቢሮ የብሔራዊ አቮካዶ ልማት ፕሮግራም በተመለከተ ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የትዉዉቅ እና የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ  እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ በአማራ ክልል በ11 ዞኖች ውስጥ ባሉ 39 ወረዳዎች ለ15 ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ነው። ይህ የአቮካዶ ልማት ኢኒሼቲቭ ዋና ዓላማ ምርቱን በቴክኖሎጂ በማዘመን አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች ግብዓትነት፣ ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ማሳደግ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው። ሌላው የአቮካዶ ምርትን የገበያ ተወዳዳሪነትን መሰረት አድርጎ በስፋት፣ በጥራት እና በዓይነት በማምረት ለተጠቃሚው ተደራሽ ለማድረግ ነው።

ቢሮ ኃላፊው እንደገለጹት የአቮካዶ ልማት ለአርሶ አደሩ ዘላቂ የገቢ ምንጭ ከመሆን ባለፈ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን ለማፋጠን  ሚናው የጎላ ነው። በክልሉ በሚቀጥሉት ዓመታት በትኩረት ከሚከናወኑ የግብርና ሥራዎች የአቮካዶ ልማት አንዱ መሆኑንም አስረድተዋል። አቮካዶ በወቅቱ ተሰብስቦ ለገበያ ካልቀረበ በቀላሉ በመበላሸት ለከፍተኛ ኪሳራ ስለሚዳርግ   ከምርት እስከ ግብይት ያለውን ሥራ በደንብ ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በአማራ ክልል  ከሚመረተው አቮካዶ 50 በመቶው ለውጭ ገበያ (ለኤክስፖርት)፣ 40 በመቶው ለምግብ እና ሥርዓተ ምግብን ለማረጋገጥ እንዲሁም 10 በመቶው ደግሞ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንደሚውልም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ የፕሮጀክቱን ዓላማ  ከግብ ለማድረስ እና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የዓብይ (እስትሪንግ) ኮሚቴው እና ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ አመራር እና ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አቶ ደረጀ ተናግረዋል። በየደረጃው ያሉ የግብርና መዋቅር፣ ባለድርሻ አካላት እና አርሶ አደሮችም በተመሳሳይ በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የብሔራዊ አቮካዶ ልማት ፕሮግራም አሥተባባሪ አቶ ይበልጣል ወንድምነው በበኩላቸው እንደ ሀገር የአቮካዶ ምርትን በመጠን እና በጥራት ለማምረት እና ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል ልምድ አናሳ እንደ ነበር አንስተዋል። ይሁን እንጅ አሁን ላይ የብሔራዊ አቮካዶ ልማት ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱን ነው የገለጹት። ይህም የአቮካዶ ምርት በጥራት እና በብዛት ለማምረት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ክልሉ ዘግይቶ ወደ ልማቱ ቢገባም የሌሎች አካባቢዎችን ተሞክሮ በመውሰድ እና ዘመናዊ አሠራሮችን በመተግበር የሀገሪቱን ትልቁን ድርሻ ለመውሰድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስተባባሪው ጠቁመዋል። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ በክልሉ 50 ሺህ ሄክታር መሬት በአቮካዶ በመሸፈን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በትኩረት ለመሥራትም ታቅዷል። በምርታማነታቸው፣ በሽታን በመቋቋም እንዲሁም በገበያ ተፈላጊ የሆኑ የአቮካዶ ዝርያዎችን በማቅረብ በኩልም በትኩረት እንደ ሚሠራ ጠቁመዋል።

ክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን እና የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከጀመራቸው አዳዲስ የልማት መስኮች አንዱ “ሀስ”  የተሰኘው  የአቮካዶ ዝርያ ልማት ነው። ክልሉ ይህንን ከፍተኛ የገበያ ተፈላጊነት ያለውን ዝርያ በማልማት ወደ ውጭ ገበያ መላክ ጀምሯል።

ሀስ አቮካዶ ለምግብነት፣ ለግብርና ኢንዱስትሪ ግብዓትነት እንዲሁም ለመዋቢያ ምርቶች (Cosmetics) ዝግጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተፈላጊነት አለው። አቮካዶን በክላስተር፣ በጓሮ እና በተፋሰስ ልማቶች በማካተት ሰፊ የኢኮኖሚ ንቅናቄ ለመፍጠር እየተሠራ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በአማራ ክልል በዓመት እስከ 900 ሺህ ኩንታል አቮካዶ ይመረታል፡፡ ነገር ግን ወደ ውጭ የሚላከው ከ10 ሺህ ኩንታል የዘለለ አይደለም። ለዚህም ዋነኛ ማነቆዎች የመሰረተ ልማት አለመስፋፋት፣ የዝርያ ምርምር ውስንነት፣ ተባይ፣ በሽታ፣  የገበያ ትስስርና መሰል ችግሮች ናቸው። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በቅንጅት መሥራት ይጠይቃል ብለዋል።

በአማራ ክልል እየተመረተ ያለው  አቮካዶ ከፍተኛ የዘይት ይዘት (Oil content) ያለው በመሆኑ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ተመራጭ ያደርገዋል። ስለሆነም በብዛት እና በጥራት ማምረት ይጠበቃል ነው ያሉት።

ምርቱ ከተሰበሰበ በኋላ የሚበላሽበት አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ ቀደም ሲል በሞጆ፣ በቢኮሎ ዓባይ፣ በቆቦ ጊራና እና ሌሎች አካባቢዎች የተገነቡት የድህረ-ምርት ማዘጋጃ ማዕከላት ዳግም ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ  እየተሠራ ነው።

በተጨማሪም የዝርያ አቅርቦትን ለመፍታት ከክልሉ ግብርና ምርምር ተቋማት እና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት የቲሹ ካልቸር (Tissue culture) ሥራዎች ተጀምረዋል። የመጓጓዣ ችግርን ለመቅረፍም በፌዴራል መንግሥት የ500 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከደብረ ኤልያስ እስከ ጎንደር እንዲሁም ከሸዋሮቢት እስከ ቆቦ ባሉ ወረዳዎች ልማቱ በስፋት እየተካሄደ ነው። የመሰረተ ልማት እና የቴክኖሎጂ አቅርቦቶች ከተሟሉ የአማራ ክልል የሀስ አቮካዶ ዝርያ  ልማት ለክልሉ አርሶ አደሮች የሀብት ማመንጫ፣ ለሀገር ደግሞ የውጭ ምንዛሬ ምሰሶ መሆኑ እንደ ማይቀር ጠቁመዋል፡፡

በውይይቱ ከተሳተፉት መካከል በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ቡድን መሪ አቶ  አዲሱ ዓለሙ ለበኵር እንደተናገሩት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የፍራፍሬ ልማትን በማዘመን ከፍተኛ ምርት ለማግኘት እና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ቡድን መሪው  እንዳስታወቁት በአሁኑ ወቅት በዞኑ 487 ሄክታር መሬት በአቮካዶ የለማ ሲሆን ከዚህም  በዓመት እስከ 21 ሺህ ኩንታል ምርት ይገኛል። በተለይም በጓንጓ እና ባንጃ አካባቢዎች ከዚህ ቀደም የነበረውን የገበያ ትስስር እና የምርት ጥራት ችግር ለመፍታት የተሻሉ ዝርያዎችን በክትባት (ግራፍቲንግ) የማባዛት እና አርሶ አደሩን በማገዝ የተሻለ ምርት የማግኘት ሥራ በስፋት እየተሠራ ነው።

አሁን ላይ የተጀመረውን ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ተከትሎ በዞኑ 100 ሄክታር የክላስተር ማሳ ተለይቶ ወደ ሥራ ተገብቷል። ለዚህም 27 ሺህ 800 የተከተቡ ችግኞች የሚያስፈልጉ ሲሆን አርሶ አደሮችን በማህበር በማደራጀት በሳይንሳዊ መንገድ የጉድጓድ ቁፋሮ፣ የኮምፖስት ዝግጅት እና የውኃ ቦይ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በሰሜን ጎጃም ዞን ከሜጫ ወረዳ ጋር በመተባበር ምርትን ወደ ውጭ ለመላክ ተሞክሮ እስከ አራት ጊዜ የተሳካ ሥራ ተከናውኗል፡፡ ነገር ግን  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት ተስተጓጉሎ ቆይቷል። ይሁን እንጂ አሁን እየተተገበረ ባለው ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም የተሻሻሉ እና ጥራታቸውን የጠበቁ የአቮካዶ ምርቶችን በስፋት በማምረት ዳግም ለውጭ (ለኤክስፖርት) እና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ጠንካራ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የቡድን መሪው አረጋግጠዋል።

በአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የወራሚት የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርምር ዘርፍ ዳይሬክተር እና ተመራማሪ  አቶ ምንውየለት ጀምበሬ እንደገለጹት ማዕከሉ የፍራፍሬ ልማትን ለማሻሻል ሰፊ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በተለይም ሀስ የተሰኘው የአቮካዶ ዝርያ ከ15 ዓመታት በፊት ወደ ክልሉ ቢገባም በኤክስቴንሽን ሥራ ማነስ ምክንያት በተፈለገው ልክ ሳይስፋፋ ቆይቷል። አሁን ላይ ግን “ሀስን” እና ሌሎችን  ጨምሮ ስድስት የአቮካዶ ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል። በተጨማሪም በአቮካዶ ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመቋቋም ከእስራኤል አዳዲስ ዝርያዎችን እና የበሽታ መቋቋም አቅም ያላቸውን የመሰረተ-ግንድ (Rootstock) በማስገባት እንዲሁም በቲሹ ካልቸር ቴክኖሎጂ ከበሽታ የፀዱ የቡና እና የአቮካዶ ችግኞችን በማባዛት ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

የክልሉ መንግሥት አሁን ላይ በዘርፉ የጀመረው አዲስ የልማት ንቅናቄ እና የሰጠው ትኩረት ለምርምር ሥራቸው ትልቅ መነቃቃት መፍጠሩን ተመራማሪው አክለዋል። ከዚህ ቀደም የግብርናው ትኩረት በሰብል ልማት ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረ ሲሆን አሁን ግን የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማትም የትኩረት አቅጣጫ ሆኗል።

የልማት ንቅናቄ የምርምር ማዕከሉ ያገኛቸውን የተሻሻሉ ዝርያዎች እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች በቀላሉ ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርሱ ትልቅ ድልድይ ሆኗል። በዚህም ተመራማሪዎች የተገኘውን ምቹ ሁኔታ እና የበጀት ድጋፍ በመጠቀም የተሻሻሉ አዳዲስ ዝርያዎችን በፍጥነት በማስፋፋት የክልሉን የፍራፍሬ ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረግ ይገኛል ነው ያሉት።

በአማራ ክልል የአቮካዶ ምርትን ከውጭ ገበያ ጋር ለማስተሳሰር ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ የተናገሩት ደግም የክልሉ የሕብረት ሥራ ኮሚሽን የግብዓት እና ግብይት ዳይሬክተር አቶ ዓለምዘውዱ ስሜነህ ናቸው።

በክልሉ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለውን የሀስ (Hass) አቮካዶ ዝርያ  ምርት ከገበያ ጋር ለማስተሳሰር ሰፊ የማሻሻያ እና የማደራጀት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ነው የገለጹት። አርሶ አደሮች በማህበር ተደራጅተው ለውጭ ገበያ (ኤክስፖርት) የሚመጥን ምርት እንዲያመርቱ ከተደረገ በኋላ ምርቱን በቀጥታ መሸጥ እንዲችሉ ከ12 በላይ ባለሙያዎችን (ኤክስፖርተሮችን) ከአዲስ አበባ በመጋበዝ ከምርት አቅራቢዎች ጋር ቀጥተኛ የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራ ተሠርቷል። ምንም እንኳን የምርቱ የገበያ ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም የገበያ ትስስሩን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የመሰረተ ልማት እጥረት በተለይም የምርት ማቀዝቀዣ እና ማከማቻ (Cold room) ችግር ማነቆ መሆኑን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።  በቀጣይ የምርት መጠኑን በስፋት በማሳደግ በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደሚታየው አይነት የአቮካዶ ዘይት የሚያመርቱ የአግሮ-ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎችን ወደ ክልሉ በመሳብ ምርቱን እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል።

መረጃ

የብሔራዊ አቮካዶ ልማት ፕሮጀክት ዋና ዋና ዓላማዎች፦

የተሻሻሉ ዝርያዎችን ማቅረብ፦ ለዓለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊ የሆኑ አቮካዶ ምርጥ ዝርያዎችን ማባዛት  ለአርሶ አደሩ ማድረስ።

የክላስተር ልማትን ማስፋፋት፦ አምራች አርሶ አደሮችን በኩታ ገጠም በማደራጀት የምርት መጠንን እና ጥራትን ማሳደግ።

የቴክኖሎጂ እና አቅም ግንባታ፦ ለአርሶ አደሮች እና ለባለሙያዎች ዘመናዊ የአመራረት፣ የኤክስፖርት ጥራት አጠባበቅ እና የድህረ-ምርት አያያዝ ስልጠናዎችን እና ድጋፎችን መስጠት።

 

(መልካሙ ከፋለ)

በኲር የግንቦት 17   ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here