ለጠቅላላ ምርጫው ስኬት ከማን ምን ይጠበቃል?

0
104

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እንደሚደነግገው በሃገራችን በየአምስት ዓመቱ ሃገራዊ ምርጫ ይካሄዳል፤ ዘንድሮ ታዲያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ በሰፊው ዝግጅት ላይ ትገኛለች።

ምርጫ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የሕዝብ ድምፅ የሚከበርበት፣ ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ የሚሸጋገርበት እና የሀገር የወደፊት አቅጣጫ የሚወሰንበት ታላቅ የፖለቲካ ሂደት ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ብዝኃነት መገለጫቸው ለሆኑ ሃገራት ምርጫ የፖለቲካ ፉክክር ብቻ ሳይሆን የሰላም፣ የአንድነት እና የልማት መሠረት ተደርጎ ይታያል።

 

በዓለም ሀገራት የተገኙ ልምዶችም ይህንን ያረጋግጣሉ። ለአብነት ደግሞ ደቡብ አፍሪካ ከዘር መድልዎ ሥርዓት ወጥታ የሁሉንም ዜጋ እኩል ድምፅ በምርጫ ማረጋገጥ ችላለች። ደቡብ ኮሪያ ደግሞ የዴሞክራሲ እና የምጣኔ ሀብት ዕድገት ግንባታዋን በምርጫ አጠናክራለች። ኢትዮጵያም በተመሳሳይ ምርጫን ለሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር፣ ለሕዝብ ተሳትፎ ማጠናከሪያ እና ለሀገራዊ መረጋጋት መሣሪያ አድርጋ እየተጠቀመችበት ትገኛለች።

 

ከቀናት በኋላ ጠቅላላ ምርጫን የምታካሂደው ሃገራችን ታዲያ ለብዙ ወራት የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ስታከናውን ቆይታለች።

 

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው በተዋረድ የምርጫ ማስፈፀሚያ ጽ/ቤቶችን ከማቋቋም እና አስፈፃሚዎችን በመምረጥ ተገቢውን ስልጠና በመስጠት እንዲሰማሩ ማድረግን ጨምሮ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

 

በመረጃው እንደተመላከተው ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮች ይበጀኛል የሚሉትን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ አውጥተዋል።

 

የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በአግባቡ ስለመከናወናቸው ነው የተገለጸው። በስኬት እንዲጠናቀቅ ደግሞ በምርጫው ወቅት እና በድህረ ምርጫ ከማን ምን ይጠበቃል? የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ ነው። ምርጫ የአንድ ተቋም ወይም የአንድ ፓርቲ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጎች፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግሥት አካላት፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የሚዲያ ተቋማት እና የጸጥታ አካላት የጋራ ኃላፊነት ነው።

 

ዜጎች በቅድሚያ የሚጠበቅባቸው የመራጭነት ካርድ በወቅቱ ማውጣትና በንቃት መሳተፍ ነው። የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዋ ቦሴ አህመድ፣ የኮምቦልቻ ከተማ በርበሬ ወንዝ ነዋሪዋ  ወይዘሮ መሰረት ሰይድ እና የደራ ወረዳ አርሶ አደር ይታይ በላይ ለበኩር እንደተናገሩት “’የመራጭነት ካርድ የሰላም መታወቂያ ነው”’ የሚለው አባባል  ትልቅ ትርጉም አለው” ብለዋል። ካርዱ የድምፅ መስጫ ፈቃድ ብቻ ሳይሆን የዜግነት ኃላፊነት መግለጫም መሆኑን ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ በምርጫው ወቅትም የሚወክላቸውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን ተማግረዋል።

የምርጫ ካርድ ሕዝቡ የሀገሩን ዕጣ ፈንታ በሰላማዊ መንገድ ለመወሰን ፍላጎቱን የሚያሳይበት መሣሪያ መሆኑን ነው የተናገሩት።

 

ይሁን እንጂ የምርጫ ካርድ መያዝ ብቻ በቂ አይደለም። መራጮች የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፖሊሲ፣ እቅድ እና አቋም በጥንቃቄ መከታተል ይጠበቅባቸዋል። በስሜት፣ በሀሰተኛ ወሬ ወይም በጥላቻ ሳይሆን በሀገራዊ ጥቅምና በእውነተኛ መረጃ መሠረት ውሳኔ መስጠት ይኖርባቸዋል። “መሪን በንቃት መምረጥ ሥልጡንነት ነው” የሚለውም መልዕክት ይህንን እውነታ ያጠናክራል።

 

መብታቸውን ለመጠቀም ታዲያ የምርጫ ካርድ በወቅቱ እንዳወጡ ነው የተናገሩት። በምርጫው ዕለት ደግሞ ለቀጣይ ዓመታት  ይመራኛል የሚሉትን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

 

አቶ ኑሩ አሕመድ በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ናቸው። ምርጫ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ይላሉ። መንግሥት ደግሞ በሕዝቡ ዘንድ ቅቡልነት እንዲኖረው ፍትሐዊ እና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

መምህሩ እንዳብራሩት የተሳካ ምርጫ ማለት ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ግልጽ እና ሰላማዊ የሆነ ምርጫ ሲካሄድ እና መራጩ ሕዝብም ውጤቱን በይሁንታ ሲቀበለው ነው። እንዲህ አይነት ምርጫ የሚያካሂዱ ሀገራትም ጠንካራ ዴሞክራሲም ይገነባሉ። ለአብነትም ኖርዌይ፣ ካናዳ፣ ህንድ፣ ጋና፣ ቦትስዋና እና ደቡብ አፍሪካ ይጠቀሳሉ።

 

በእነዚህ ሀገራት የተካሄዱ ምርጫዎች ፍጹም በሚባል ደረጃ ዲሚክራሲያዊ ናቸው ባይባልም እንኳን በብዙኃን ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ እና የተሻሉ የምርጫ ተሞክሪዎች ስለመሆናቸው አንስተዋል፡፡

መምህሩ አክለውም በቅድመ ምርጫም ሆነ ከምርጫ በኋላ አንዳንድ ሀገራት ውጤቱን ባለመቀበል ብዙ የሰው ህይወት እየጠፋ እና ንብረቶች እየወደሙ ጦርነት እና ግጭት ውስጥ እንደሚገቡ ጠቅሰዋል።

በእኛ ሀገርም ይህ እንዳይከሰት በቅድመ ምርጫም ሆነ ከምርጫ በኋላ ውጤቱን ከመቀበል አንጻር በገለልተኛ ወገን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡

ንቃተ ህሊናው የዳበረ፣ ፖለቲካውን የተረዳ እና ምህዳሩን ከግምት ውስጥ አስገብቶ የሚንቀሳቀስ ዜጋን መፍጠር ምርጫን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለማስኬድ ዋና መፍትሄ ስለመሆኑም  አክለዋል፡፡

 

ለዚህ ደግሞ በተለይ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው። በድሩ ወንድሙ የአማራ ክልል ወጣቶች ማኅበር ፕሬዚዳንት ነው። ፕሬዚዳንቱ ለበኩር እንደተናገረው ወጣቶች በመራጭነትም ሆነ በተወዳዳሪነት በንቃት መሳተፍ አለባቸው። ከዚህ በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማጣራት እውነተኛ መረጃን መጠቀም ይጠበቅባቸዋል። የዛሬው ምርጫ በቴክኖሎጂ እና በሚዲያ ዘመን የሚካሄድ በመሆኑ የሀሰት ወሬ እና የጥላቻ ቅስቀሳ የምርጫ ሂደቱን ሊያውኩ ይችላሉ። ስለዚህ ወጣቶች የሰላም እና የእውነት አምባሳደሮች ሊሆኑ ይገባል።

በተመሳሳይ ከፖለቲካ ፓርቲዎችም ብዙ ነገር ይጠበቃል። ፓርቲዎች ፉክክራቸውን በሃሳብና በፖሊሲ መሠረት ማካሄድ አለባቸው። ጥላቻን፣ ግጭትን እና አመጽን ከመቀስቀስ በመቆጠብ ሕዝብን በአማራጭ ሀሳብ ማሳመን ይኖርባቸዋል። የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተስፋሁን ዓለምነህ እንደተናገሩት “ሥልጣን ከካርድ እንጂ ከጠመንጃ አይገኝም” የሚለው መልዕክት የሁሉም ፓርቲዎች መርህ ሊሆን ይገባል። የዴሞክራሲ ዋና መሠረት የሕዝብ ድምፅ መከበር ነው፤ ይህም የሚረጋገጠው በሰላማዊ ምርጫ ብቻ ነው።

በሰላም እና በምርጫ  ጉዳይ የጋራ ምክር ቤቱ ወጥ አቋም ወስዶ እየሠራ ስለመሆኑም አንስተዋል።

አቶ ተስፋሁን አክለውም “ምርጫ ካለ አሸናፊ እና ተሸናፊ የፖለቲካ ፓርቲ ይኖራል፤ ነገር ግን አሸናፊ ሀገር እና አሸናፊ ዴሞክራሲ መኖር አለበት፤ ለዚህ ደግሞ በጋራ መሥራት አለብን” ብለዋል።

 

ሌላው ትልቁ ድርሻ መንግሥትና የምርጫ ቦርድ ናቸው። የምርጫ ሂደቱ ነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ተአማኒ እና ግልጽ እንዲሆን ማረጋገጥ አለባቸው። የመራጮች ምዝገባ፣ የድምፅ አሰጣጥ፣ የውጤት ቆጠራ እና የውጤት ግልጽነት በጥንቃቄ መከናወን ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውን ማስታወቁ የሕዝቡን የፖለቲካ ተሳትፎ ያሳያል። ይህ ቁጥር በሀገሪቱ ውስጥ የዴሞክራሲ ፍላጎት እያደገ መሆኑን የሚጠቁም ነው።

 

በተመሳሳይ የጸጥታ አካላትም በምርጫው ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና አላቸው። የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት ምርጫው በሰላም እንዲካሄድ በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

ዶክተር እሸቱ እንዳሉት በጸጥታ ችግር ምክንያት የሚስተጓጎል የምርጫ ክልልም ሆነ ጣቢያ የለም፤ ለዚህም አስተማማኝ ዝግጅት ተደርጓል። የጸጥታ ኃይሎች ዋና ተግባር ሕግን  ማስከበር እና የሕዝብን ደኅንነት ማረጋገጥ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ሴቶች እና ማኅበረሰብ አቀፍ ተቋማትም በምርጫው ውስጥ የሚጫወቱት ሚና ትልቅ ነው። የሴቶች የምርጫ ተሳትፎ ከፍ ማለት የዴሞክራሲ ስፋትን ያሳያል። ሴቶች በመራጭነት፣ በተወዳዳሪነት እና በምርጫ ክትትል ላይ በንቃት መሳተፍ አለባቸው። የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት እና የሚዲያ ተቋማትም ሕዝቡን በማስተማር፣ ሰላምን በማጠናከር እና ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባቸዋል።

በጠቅላላው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ ነው። ይህ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ እና ተአማኒ ሆኖ ከተጠናቀቀ ለሀገሪቱ ፖለቲካዊ መረጋጋት፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ለሕዝብ አንድነት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም አካላት ከራሳቸው የሚጠበቀውን ኃላፊነት በብቃት መወጣት አለባቸው። ምርጫ የካርድ እንጂ የጠመንጃ ጉዳይ አለመሆኑን ሁሉም በመረዳት ድምፃቸውን ለሰላም፣ ለአንድነት እና ለሀገር ግንባታ መጠቀም ይገባል።

(ሰናይት በየነ)

በኲር የግንቦት 17   ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here