የተለያዩ መስፈርቶችን መሠረት አድርጎ የዓለም ሀገራትን ወታደራዊ አቅም በየዓመቱ ይፋ ያደርጋል – ግሎባል ፋየር ፓወር (www.globalfirepower.com) የተባለው ዓለም አቀፍ ተቋም። ማወዳደሪያ መስፈርቶቹን መሠረት በማድረግም አሜሪካን የዓለማችን ልዕለ ኃያል፣ ቻይናን ደግሞ ሁለተኛዋ ልዕለ ኃያል ሲል ነው ያስቀመጣቸው።
የመረጃ ምንጩ እንዳስነበበው ሁለቱ የዓለማችን ልዕለ ኃያል ሃገራት የዓለማችንን ፖለቲካ ዘዋሪ ናቸው። በመሆኑም የሃገራቱ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ የዓለም ሕዝብ ሁሉ የትኩረት ማዕከል ነው።
በተመሳሳይ የዓለም ገንዘብ ድርጅት (IMF) መረጃ እንደሚያመላክተው ሁለቱ ኃያላን የምድራችንን 43 በመቶ ጥቅል ሀብት (GDP) ድርሻ ሲኖራቸው አሜሪካ በቀዳሚነት ትመራለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት አሁን አሁን ገጽታውን በየቀኑ መቀያየር መገለጫው እስኪመስል ድረስ አጀንዳ ሆኗል። ኃያልነታቸውን ለማጠናከር ወይም ለማስቀጠል በተለይ በአፍሪካ አህጉር የሚያደርጉት እሽቅድምድም፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ፣ የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት እና መሰል ዓለም አቀፍ ርእሰ ጉዳዮች ሃገራቱ ጸብ አጫሪ ቃላትን እንዲሰነዛዘሩ ምክንያቶች ናቸው።
ይሁን እንጁ ላይ ላዩን ለሚያየው ግንኙነታቸው ባላንጣነት ያየለበት ቢመስልም እውነታው ግን አንዱ በሌላኛው ላይ ጥገኛ፣ የንግድ ትስስራቸውም በትሪሊዮን ዶላሮች የተገመደ መሆኑን የአልጀዚራ መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ ያስነበበው መረጃ ይጠቁማል።
የኃያልነት እሽቅድምድም
ሁለቱ ሃገራት በተለይ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የቃላት ጦርነታቸው ከፍ ብሎ ሰነባብቷል። ለዚህ መነሻ ደግሞ አሜሪካ በቻይና ምርቶች ላይ የጣለችው ከፍተኛ የቀረጥ ጭማሪ ነው። በአጸፋውም ቻይናም በአሜሪካ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ያለችውን ጭማሪ አድርጋለች።
የኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ እንደሚያመላክተው ሃገራቱ አንዱ በአንዱ ላይ ያደረጉት የቀረጥ ጭማሪ ከምጣኔ ሃብታዊ አንድምታ የተሻገረ ነው። ልዕለ ኃያልነታቸውን ለማጠናከር ሲሉ በምርቶች ላይ ከፍተኛ ቀረጥን በመጫን ምጣኔ ሃብታዊ ክስረትን ለማምጣት ነው።
ይህ የሁለቱ ኃላን መካረረ ከፍ ያለው ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ከመጡ ማግስት ነው፤ ችግሩ የምጣኔ ሃብት ጦርነት ቢመስልም የከፋ ውጤት እንዳላስከተለ ፋይናንሻል ታይምስ አስነብቧል። እንደ መረጃው ከሆነ ከአንድ መቶ ሺህ በላይ አሜሪካዊያን በቻይና ከትመዋል። ከአሜሪካ ውጪ ይህን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ያለው አሜሪካዊም ከቻይና ውጪ በሌላ በየትኛውም የዓለም ክፍል አይገኝም። ይህ ታዲያ በሁለቱ ሃገራት መካከል ጠንካራ ምጣኔ ሃብታዊ መጋመድን አመላካች ነው። በተመሳሳይ ከአሜሪካ ጋር የንግድ መስመራቸውን ያጠናከሩ እና አለፍ ሲልም መኖሪያቸውን ያደረጉ ቻይናውያን ቁጥርም ከፍተኛ ነው፤ ይህ ሁሉ ተደማምሮ ታዲያ የሁለቱ ኃያላን ፍጥጫ ከቃላት ጦርነት እንደማያልፍ ነው ዘገባው የጠቆመው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ “ለኃያልነት እሽቅድምድማቸው ሁለቱ ኃያላን አንድም ቀን ተኝተው አያውቁም” ሲል ያስነበበው ደግሞ ዘ ሚድል ኢስት ሞኒተር ነው። ለዚህም ማሳያዎችን ያነሳል። አሜሪካ በሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በኩል የምታደርገው የኃይል የበላይነት ሩጫ እና ቻይና ደግሞ ሮድ ኤንድ ቤልት (አንድ መቀነት) በሚል የትስስር መስመሯ የምታደርገው እንቅስቃሴ ይጠቀሳሉ።
ሰሞነኛው ሙቀት
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሙኑ መዳረሻቸውን ቻይና ላይ አድርገው ነበር፤ የዓለም ትኩረት ሁሉ የነበረውም ይህ ታሪካዊ ጉብኝት ነው፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በቻይናዋ መዲና ቤጂንግ ከተማ ሲደርሱበቀይ ምንጣፍ ባሸበረቀ እና የሀገሪቱን ክብር በሚመጥን ወታደራዊ ትርዒት ነበር አቀባበል የጠበቃቸው፡፡
ለፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ልዑካቸው ደማቁን አቀባበል ያደረጉላቸው የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በንግግራቸው “ቻይና እና አሜሪካ በትብብር ሲሠሩ ለዓለም መረጋጋትና ልማት አስፈላጊ ናቸው” ብለዋል። ለማንኛውም ነገር ውይይትና መተማመን የተሻለው መንገድ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው ነው ያነሱት።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ሁለቱ ኃያላን ሃገራት በምጣኔ ሀብት፣ በደኅንነት፣ በቴክኖሎጂ እና በአየር ንብረት ጉዳዮች ላይ በጋራ መሥራት አለባቸው” ሲሉ ነው የተደመጡት። ከዚህ በተጨማሪም የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ወደ ግጭት እንዳያመራ በጥንቃቄ መተዳደር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ኃያላኑ ስለ ምን መከሩ?
የቻይናው ዜና ማሰራጫ ሲ ጂ ቲ ኤን እንደዘገበው የመሪዎቹ ውይይቱ በንግድ ግንኙነት፣ በታይዋን ጉዳይ፣ በቴክኖሎጂ ውድድር እና በዓለም የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነበር። ዘገባው አክሎም ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለቀናት ቤጂንግ የከተሙት ከ10 በላይ ኩባንያዎችን ሥራ አስፈጻሚዎች አስከትለከው መሆኑን አስታውሷል፡፡
በሌላ በኩል እ.አ.አ በ2025 ይፋ የተደረገው የዓለም ባንክ ምጣኔ ሀብታዊ መረጃ (World Bank Economic Data) ቻይና ለአሜሪካ ገበያ የምታቀርበው ምርት 440 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። አሜሪካ ወደ ቻይና የምትልከው ምርት ደግሞ 145 ቢሊዮን ዶላር ነው። ይህ ሰፊ የንግድ ጉድለት ታዲያ በፕሬዚዳንት ትራምፕ ከባድ ቂም እንዲቀቋጥሩ አድርጓቸዋል፡፡ በመሆኑም በቻይና ምርቶች ላይ የ145 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ እንዲጥሉ ምክንያት ሆኗቸዋል። ቻይናም በአሜሪካ ምርቶች ላይ የ125 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ ማድረጓ አይዘነጋም፡፡
የሰሞኑ ጉብኝት ታዲያ ይህንኑ ቅራኔ ለማርገብ መልካም አጋጣሚ ከመሆኑም ባለፈ የመሪዎቹ ዋና የውይይት አጀንዳ ሆኗል፤ ለዚህ ደግሞ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደ ቻይና አስከትለዋቸው የሄዱት እና አንድ ትሪሊዮን ዶላር ያህል ሀብት ያላቸው 12 የኩባንያ ሥራ አስፈጻሚዎች ማሳያ ናቸው።
በውይይቱ በዋናነት የንግድ ግጭቶች እና ምጣኔ ሀብታዊ ውድድሮችን የተመለከቱ ሐሳቦች ከፍ ብለው ተነስተውበታል፤ የዓለም ምጣኔ ሀብት መረጋጋት ከትብብር ጋር እንደሚያያዝ ያነሱት መሪዎቹ ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓት ለማስፈን እንደሚሠሩም አስታውቀዋል።
የታይዋን ጉዳይ ደግሞ ሌላው የመሪዎቹ የውይይት ማዕከል ነበር፤ ሀገራቱን የቃላት ጦርነት እንዲወራወሩ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች መካከል የታይዋን ጉዳይ ይጠቀሳል፡፡ ቻይና ታይዋንን የራሷ የግዛት አካል አድርጋ ነው የምትመለከታት፤ አሜሪካ በበኩሏ በክልሉ የሚፈጠር ግጭት እንዳይባባስ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጠይቃለች። ይህ ጉዳይ በሁለቱ ሃገራት መካከል ከፍተኛ ውጥረትን ፈጥሮ ቆይቷል። መራቹ ይህን ጉዳይ መነሻ እንደተናሩት ማንኛውንም ችግር ለመፍታት ውይይት ቁልፉ መፍትሔ ነው፡፡
በሌላ በኩል መሪዎቹ በወታደራዊ ግንኙነት ላይም ገንቢ ውይይት ማድረጋቸውን ነው ያስታወቁት፤ ዝርዝር ነጥቦች ባይጠቀሱም ስምምነት ማድረጋቸውም ነው የተነገረው።
ሁለቱ ሃገራት በዓለም ከፍተኛውን የካርቦን ልቀት በማምረት ለዓየር ንብረት መዛባት ተጠያቂ ናቸው፤ በሰሞኑ ውይይት ታዲያ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። ትብብሩም በዓለም አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ጥረቶች ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ዕምነት ተጥሎበታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ሃገራቸው ከተመለሱ ማግስት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቱን ወደ ቻይና ማቅናታቸው ግርምትን ፈጥሯል፤
ትራምፕን አስተናግዳ የሸኘችው ቻይና፣ ወዲያውኑ ከሞስኮ ጋር በመቀናጀት በዋሽንግተን ላይ ያነጣጠረ ጠንካራ የጋራ መግለጫ አውጥታለች። የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቤጂንግ ካደረጉት ውይይት በኋላ ባወጡት በዚህ የጋራ መግለጫ፤ አሜሪካ በመላው ዓለም የምታካሂዳቸውን ወታደራዊ ዘመቻዎች እና በሌሎች ሃገራት ላይ የምትፈጽማቸውን ድንገተኛ ወታደራዊ ጥቃቶች አውግዘዋል።
አሜሪካ የምትወስዳቸው እነዚህ እርምጃዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስምምነቶችንና ዓለም አቀፍ ሕግጋትን የሚጥሱ መሆናቸውን ቤጂንግ እና ሞስኮ በጋራ ባወጡት መግለጫ ማሳወቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
(ጌትሽ ኃይሌ)
በኲር የግንቦት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


