የኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ ተስፋ

0
161

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምሥራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) መድረክ አልፎ በአህጉራዊ የውድድር መድረኮች ላይ እያሳየ ያለው መነቃቃት የብዙ ስፖርት አፍቃሪያንን ቀልብ መሳብ ችሏል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በታዳጊዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ከጀመረ ወዲህ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ የተሻለ መረጋጋት ማሳየት ጀምሯል፡፡ ይህ አዲስ ትውልድ በሜዳ ላይ ባለው ከፍተኛ ፍጥነት፣ በኳስ ቁጥጥር ፍላጎቱ እና የኋላ ክፍሉ መናበቡ በኢትዮጵያ አዲስ የእግር ኳስ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑን ያሳያል፡፡ በአሜሪካዊ ዋና አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚሰለጥነው ይህ ቡድን በሀገሪቱ የስፖርት ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ሊከፍት እንደሚችል በስፋት እየተነገረ ይገኛል፡፡

 

ይህ የታዳጊዎች ስብስብ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ተቃራኒ ቡድንን የማስደንገጥ ብቃታቸው እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ በተለያዩ ጨዋታዎች አስመስክረዋል፡፡ ይህ ስልታዊ ተለዋዋጭነት አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር ቡድኑ በተለያዩ አስቸጋሪ የአየር ንብረቶች እና የሜዳ ሁኔታዎች ውስጥም ቢሆን የራሱን የጨዋታ የበላይነት ይዞ ለመውጣት እንዲችል ትልቅ እገዛ አድርጎለታል፡፡ ሜዳ ላይ የሚያሳዩት የታክቲክ ዲሲፕሊን የታዳጊዎቹን ብስለት ያሳያል፡፡ ቡድኑን ከቀጣናው አልፎ በአህጉራችን ክስተት እንደሚሆን ከወዲሁ ፍንጭ ሰጥቷል፡፡

 

ብሄራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎች እና በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ያስመዘገባቸው ደማቅ ስኬቶች የኢትዮጵያን እግር ኳስ ትንሳኤ አመላካች ናቸው፡፡ በሴካፋ ውድድር ላይ ተቀናቃኞቹን ድል በማድረግ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያለፈበት መንገድ በብዙዎች አድናቆት ተችሮታል፡፡ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ቆይታውም  ከግብፅ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይቷል፡፡ በሞሮኮ ደግሞ ሁለት ለአንድ ተሸንፏል፡፡ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያም ሌላኛዋን ሰሜን አፍሪካዊት ሀገር ቱኒዚያን አንድ ለባዶ ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ታዳጊዎቹ የአካል ብቃት የበላይነትን ተቋቁመው ቴክኒካዊ እግር ኳስ መጫወት እንደሚችሉ እና በእግር ኳስ ካደረጉት የሰሜን አፍሪካ ሀገራት ጋር መፎካከር እንደሚችሉ አሳይተዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ታችኛው መዋቅር ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ከጀመረ ወዲህ የተገኘ ፍሬ ነው፡፡

 

በጨዋታዎች ላይ ቀድሞ ግብ ቢቆጠርባቸው እንኳ ተስፋ ሳይቆርጡ ወደ ጨዋታው የመመለስ አስደናቂ የስነ ልቦና ጥንካሬ በተለይ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ በተደጋጋሚ ተመልክተናል፡፡ ይሁን እንጂ ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ይበልጥ ብቁ ለመሆን አሁንም የሚታዩ አንዳንድ ክፍተቶችን መሙላት ይኖርባቸዋል። ታዳጊዎቹ በእግር ኳስ ካደጉ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር የሚኖራቸው ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታዎች  ልምድ ማነስ ይታይባቸዋል፡፡ በአየር ላይ በሚጣሉ ኳሶች፣ በማዕዘን ምቶች ላይ የሚታየው የአቀማመጥ ስህተት እንደ ክፍተት ይነሳባቸዋል፡፡ የፊት መስመሩም በተቃራኒ የግብ ክልል ሲድረስ  የመረጋጋት ችግር ይስተዋልበታል። እነዚህ  ክፍተቶች ከተሞሉ ቀይ ቀበሮዎቹ  ወደ ማይበገሩ ታላላቅ ብሄራዊ ቡድኖች ተርታ የሚሰለፉበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡

 

የዚህ ቡድን ዋነኛ መለያ ባህሪ ዘመናዊ እና ማራኪ የእግር ኳስ ፍልስፍናን እንደሚከተል በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው የተስፋ ኮከብ ብረሃን የእግር ኳስ ፕሮጀክት አሰልጣኝ የሆኑት አዲሱ ምሬ ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ የስፖርት ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡ “ፕሮጀክት ከታች ነው መሰራት ያለበት የሚለውን ነገር ሁሌም እናነሳ ነበር” የሚሉት አሰልጣኙ  ልጆቹ በታዳጊነት ዕድሜያቸው ተገቢውን ሥልጠና እና እንክብካቤ አግኝተው ማደጋቸው አሁን ለታየው ውጤት ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

 

የዚህ የ17 ዓመት በታች ቡድን ምርጥ አቋም በራሱ ለሌሎች ፕሮጀክቶች ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሯል፡፡ አሰልጣኙ እንደሚሉት አሁን ሜዳ ላይ የምናያቸው ታዳጊዎች ለሌሎች ሕፃናት  አርአያ ሆነዋል፡፡ በአካባቢ ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች እነዚህን ልጆች በማየት “ነገ እኛም እንደነሱ መሆን እንችላለን” የሚል ተስፋ እንዲያሳድሩ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በታችኛው እርከን ለሚሰሩ አሰልጣኞች ተተኪ ስፖርተኞችን ለማውጣት ያላቸውን ወኔ አሳድጎላቸዋል፡፡

 

ይሁን እንጂ አሰልጣኝ አዲሱ ከ17 ዓመት በታች ብቻ ሳይሆን ከ13 ዓመት በታችም ካልተሰራ አሁን የተገኘው ስኬት ብልጭ ብሎ የሚጠፋ ሊሆን ይችላልም ብለዋል፡፡ እነዚህ ታዳጊዎች ለፍተው እና ብዙ መዋዕለ ንዋይ ፈሶባቸው እዚህ ደረጃ ከደረሱ በኋላ እንዳይበተኑ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ እናም አሁን ያለውን አቅም ለማስቀጠል የባለሙያ፣ የቴክኒክ እና የሞራል ድጋፍ ለቡድኑ ወሳኝ እንደሆነ አሰልጣኝ አዲሱ አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

 

ቀይ ቀበሮዎቹ  ውጤት ከማምጣታቸው ባሻገር ለብዙ ዓመታት ጠፍቶ የነበረውን የኢትዮጵያን እግር ኳስ ማንነት እና ማራኪ የአጨዋወት ስልት ድጋሚ አሳይተዋል፡፡ ይህንን አዲስ ትውልድ ጠብቆ ማቆየት ከተቻለ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ወደ ቀደመ ክብሩ መመለስ ብቻ ሳይሆን በአህጉራችን ትልቅ ስም ያለው ጠንካራ ስብስብ መገንባት ይቻላል- የአሰልጣኝ አዲሱ አስተያየት ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ ፌዴሬሽኑ፣ ክለቦች እና የስፖርት አፍቃሪው በጋራ በመሆን ለታዳጊዎቹ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አሰልጣኝ አዲሱ ምሬ ያምናሉ፡፡ እግር ኳስ በአንዴ ውጤት የሚመጣበት ሳይሆን በሂደት የሚገነባ መሆኑን ተረድቶ የፌዴሬሽኑ አመራሮች፣ የቴክኒክ መሪዎች እና አሰልጣኞች የየራሳቸውን ድርሻ በአግባቡ ከተወጡ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ግብዓት የሚሆኑ ተጫዋቾችን በዘላቂነት ማግኘት ይቻላል፡፡

 

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የሀገሪቱን እግር ኳስ የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስኑ ደማቅ ከዋክብት መሆናቸውን ከወዲሁ እያሳዩ ነው፡፡ ይህንንም በአፍሪካ ዋንጫ እና በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አስመስክረዋል። የዋናውን ብሔራዊ ቡድን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ዘመናዊ የእግር ኳስ ስልጠናዎችን ማመቻቸት፣ ሳይንሳዊ የአመጋገብ እና የአካል ብቃት ክትትል ማድረግ፣ ተጫዋቾቹ ወደ ትልልቅ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ክለቦች ተሻግረው የጨዋታ እድል እንዲያገኙ ማገዝ የሁሉም ድርሻ ሊሆን ይገባል፡፡

 

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here