ብዙዎቹ በእግር ኳስ ቆርቧል ይሉታል፤ እግር ኳስን እንደነብሱ ይወዳል፤ በእግር ኳስ ምክንያት የ30 ዓመት ትዳሩ ተናግቷል፤ ስለ ስፖርት ስነ ልቦና እና ፍልስፍና ያለእረፍት ያነባል፤ ይመራመራል፡፡ ለመማር ዝግጁ ነው፤ የማይነጥፍ የፈጠራ እና የታክቲክ እውቀት አለው፤ የካታሎናውያን ኩራት ነው፤ የእግር ኳስ አርቲስትም ነው፡፡ የቅርጫት ኳስ እና የጎልፍ ስፖርት አፍቃሪ፤ የእግር ኳስ ደግሞ ሊቅ ነው። በአሰልጣኝነት ህይወቱ በክለቦች ተሰናብቶ አያውቅም፡፡ በሊግ ውድድር ከሁለተኛ ደረጃ በታች ይዞ አጠናቆም አያውቅም፡፡ የዓለም እግር ኳስ ማርሽ ቀያሪው አሰልጣኝ- ጆሴፕ ፔፕ ጓርዲዮላ፡፡
ስፔናዊው ታክቲሺያን የ21ኛው ክፍለ ዘመን አቢዮተኛ አሰልጣኝ ነው፡፡ በሚከተለው ኳስን ተቆጣጥሮ የመጫወት (ፖዚሽናል ፕሌይ) ስልት በባርሴሎና፣ ባየርሙኒክ እና ማንቸስተር ሲቲ አስደናቂ ስኬትን አስመዝግቧል፡፡ ጓርዲዮላ የ21ኛው ክፍለ ዘመን እግር ኳስን መቀየሩን ብዙዎች ይመሰክሩለታል። በእግር ኳስ ስፖርት የመነኮሰው ጓርዲዮላ ሁሌም ሀሳቡ እግር ኳስ እና እግር ኳስ ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ 30 ዓመታትን ከደፈነው ትዳሩ ጋር አለያይቶታል፡፡
ጓርዲዮላ ከአርጀንቲናዊው አሰልጣኝ ማርሴሎ ቤልሳ በተጫማሪ የአንጋፋው የቅርጫት ኳስ አሰልጣኝ ጆን ውድ ተጽእኖ እንዳለበት የጎል ዶት ኮም መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህ ደግሞ በጨዋታ አቀራረብ እና ፈጠራ እንዲካን አግዞታል ይላል መረጃው፡፡ ጓርዲዮላ ብዙ ጊዜውን ከጨዋታ በኋላ የእግር ኳስ ትንተና ሲሠራ እና ሲያነብ እንደሚያሳልፍ መረጃው አመልክቷል፡፡ በጓርዲዮላ መነጽር የትኛውም ጥቃቅን የእግር ኳስ ክስተት እና ሀሳብ ዋጋ አልባ አይደለም፡፡
ነገሮቹን በጥልቀት መመርመሩ አሁን ለደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ አግዞታል፡፡
ጓርዲዮላ በተጫዋችነት ዘመኑ ድንቅ የመሀል ሜዳ ኦርኬስትረኛ እንደነበር የእርሱ ትውልድ የቀድሞ ተጫዋቾች ይናገራሉ፡፡ ይህ ብቻ ግን ድንቅ አሰልጣኝ አላደረገውም፡፡
እ.አ.አ በ2006 በተጫዋችነት የእድሜ ማምሻው ወደ ሜክሲኮ በመብረር በዶራዶስ ዶ ሲናሎአን መጫወቱን የግል የታሪክ ማህደሩ ያስነብባል፡፡ ታዲያ በዚህ ክለብ ያሳለፈው ጊዜ አጭር ቢሆንም በእግር ኳስ ህይወቱ ማርሽ ቀያሪ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በሜክሲኮ ቆይታው የታክቲክ እውቀቱን በማጎልበት ልዩ የስልጠና ዘይቤ እንዲከተል እና የተለያዩ የእግር ኳስ አስተሳሰቦችን እንዲገነዘብ አስችሎታል፡፡ በተጨማሪም ወደ አርጀንቲና ተጉዞ ከአሰልጣኝ ማርሴሎ ቤልሳ እግር ስር በመማር አዲስ የስልጠና አስተሳሰብ ፈጥሯል፡፡ በተለይ ጓርዲዮላ በካታሎኑ ክለብ ቤት በነበረበት ወቅት ይታወቅበት የነበረውን የቲኪ-ታካ የእግር ኳስ ፍልስፍና የወለደው ከአሰልጣኝ ማርሴሎ ቤልሳ ጋር ከተገናኘ በኋላ ነው፡፡ የፔፕ ጓርዲዮላ አስተሳሰብ በታላቁ አሰልጣኝ ሆላንዳዊ ዮሃን ክራይፍ መቀረጹንም መረጃው አልሸሸገም፡፡
ጓርዲዮላ የታክቲካል አባዜ የተጠናወተው አሰልጣኝ ነው ማለት ይቻላል። የጨዋታ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን(ቪዲዮችን) መመልከት፣ መተንተን እና አዳዲስ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የጨዋታ ዘይቤ እና ስልቶችን በመንደፍ ይታወቃል፡፡ በዚህም የእግር ኳሱ ፈላስፋ የሚል ስያሜን አግኝቷል፡፡ በ17 ዓመታት የአሰልጣኝነት ህይወቱም ዋንጫ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን የዓለምን እግር ኳስ የቀየረ አዲስ አስተሳሰብ እና ጽንሰ ሀሳብ ፈጥሯል፡፡
የ55 ዓመቱ ስፔናዊ የልህቀት እና የፈጠራ ምልክትም ነው፡፡ የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ በላሊጋ፣ በቡንደስ ሊጋ እና በፕሪሚየር ሊግ የተለያዩ ዋንጫዎችን በማሳካት ውጤታማ አሰልጣኝ ነው፡፡ ይህ የክፍለ ዘመኑ ታላቅ አሰልጣኝ በሦስቱ ታላላቅ ሊጎች የገነባቸው ቡድኖች ለፍጹምነት የተቃረቡ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ጆሴፕ ፔፕ ጓርዲዮላ በፈጠራ የተካነ፣ ታታሪ፣ የላቀ የታክቲክ ግንዛቤ ያለው እና ድንቅ ጨዋታን የማንበብ ክህሎት ያለው የዘመናችን ታላቅ አሰልጣኝ ነው፡፡
በባርሴሎና እና በማንቸስተር ሲቲ ቤት የሦስትዮሽ ዋንጫ በማንሳት የመጀመሪያው አሰልጣኝ ነው፡፡ የአውሮፓ ክለቦች የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ከሦስት የተለያዩ ክለቦች ጋር በማሳካት የመጀመሪያው አሰልጣኝ ነው፡፡ በላሊጋ፣ በቡንደስ ሊጋ እና በፕሪሚየር ሊጉ በተከታታይ የሊግ ዋንጫዎችን በማሳካትም ባለክብረወሰን ነው፡፡
ፔፕ ጋርዲዮላ በስፔን፣ በጀርመን እና በእንግሊዝ ከ40 በላይ ዋና ዋና ዋንጫዎችን እና 12 የሊግ ዋንጫዎችን አሸንፏል፡፡
ማንቸስተር ሲቲ በተከታታይ አራት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን በማሸነፍ ብቸኛው የፕሪሚየርሊጉ ክለብ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ማንቸስተር ሲቲ በአሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ እየተመራ በእ.አ.አ 2017/18 100 ነጥቦችን የሰበሰበ የመጀመሪያው እና ብቸኛው የፕሪሚየር ሊጉ ክለብ መሆን ችሏል፡፡
በላሊጋ 16 ተከታታይ ድሎችን፣ በቡንደስሊጋ 19 ድሎችን እና በፕሪሚየር ሊጉ 18 ድሎችን በተከታታይ በማስመዝገብ አዲስ ክብረወሰን ይዟል፡፡ በ160 የአውሮፓ ሻምዮንስ ሊግ ጨዋታዎች 100 ድሎችን ያስመዘገበ ፈጣኑ አሰልጣኝ ነው፡፡ በባርሴሎና፣ ባየርን ሙኒክ እና በማንቸስተር ሲቲ ከ40 በላይ ዋና ዋና ዋንጫዎችን ሰብስቧል፡፡
ጓርዲዮላ በ2017/18 እ.አ.አ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በአንድ የውድድር ዘመን ብዙ ግቦችን በማስቆጠር (106) አዲስ ክብረወሰን ማስመዝገቡን የጎል ዶት ኮም መረጃ ያስነብባል፡፡ በሙያ ዘመኑ ከ500 በላይ ጨዋታዎችን ያከናወነው ስፔናዊው ታክቲሽያን ከ70 በመቶ በላይ ጨዋታዎችን አሽንፏል፡፡ ይህም በዘመናዊ እግር ኳስ ከፍተኛው እንደሆነ መረጃው ያመለክታል፡፡
ብዙዎቹ በዚህ አስደናቂ የእግር ኳስ ህይወቱ እና ክህሎቱ ፍቅር ወድቀው የፍልስፍናው እና የአስተሳሰቡ ምርኮኛ ሆነዋል፡፡ የእርሱ የእግር ኳስ ጥልቅ ስሜት የተጋባባቸው እና የተጠናወታቸው የእግር ኳስ ሊሂቃን አሁን በአውሮፓ ምድር አንቱ ተብለዋል፡፡ ገሚሶች የእርሱ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን እውቀቱን የተቋደሱ ናቸው፡፡ ገሚሶች ደግሞ በተጫዋችነት ዘመናቸው ወደ አሰልጣኝነት ህይወት የሚያመራቸውን እውቀት ከታላቁ አሰልጣኝ የሸመቱ ናቸው፡፡
ለአብነት ዣቪ ሄርናንዴዝ፣ የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትዱ እና የአያክስ አምስተርዳም አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሀግ፣ የባየርሙኒኩ አሰልጣኝ ቪኒሴንት ኮምፓኒ፣ የፈረንሳዩ ክለብ አሰልጣኝ ሊዊስ ኢኔሪኬ፣ ሚኬል አርቴታ፣ ዣቢ አሎንሶ እና የመሳሰሉት የጓርዲዮላ ደቀመዛሙርት ናቸው፡፡
ይህ የእግር ኳስ ሊቅ እና መምህር ዐስር ዓመታትን ከቆየበት ኢትሀድ ስቴዲየም በመጨረሻው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ተሸኝቷል፡፡ የጓርዲዮላ መዳረሻ ለጊዜው ባይታወቅም ማንቸስተር ሲቲ ግን ሳይውል ሳያድር ኤንዞ ማሬስካን የእርሱ ተተኪ አድርጎ መሾሙን አሳውቋል፡፡
“ስኬት ማለት ድል ብቻ አይደለም፤ ስኬት ማለት የምታምንበትን ፍልስፍና ሜዳ ላይ በተግባር ማየት ነው” ፔፕ ጓርዲዮላ፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


