ምርጫ ማለት በአንድ ማህበረሰብ ወይም ሀገር ውስጥ ዜጎች ከበርካታ አማራጮች መካከል ፍላጎታቸውን የሚገልጹበት፣ ተወካዮቻቸውን ወይም መሪዎቻቸውን በነጻነት የሚመርጡበት እና የፖለቲካ ስልጣን በሰላማዊ መንገድ እንዲያዝ የሚያደርጉበት መሰረታዊ የዲሞክራሲ ስርዓት መገለጫ ሂደት ነው።
መሪ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች እኔ ብመረጥ ይህንን አደርጋለሁ እያሉ ሃሳባቸውን ለሕዝብ ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች ዕጩዎች ይባላሉ። ዕጩዎቹ መራጮችን ለማሳመን ጥሩ ሃሳባቸውን ያጋራሉ። ለምሳሌ በአንድ የጨዋታ ሜዳ ላይ እኔ ብመረጥ አዳዲስ ኳሶችን አመጣለሁ ወይም እኔ ብመረጥ ሜዳውን አጸዳለሁ ብለው ቃል ሊገቡ ይችላሉ። ይህ የምርጫ ቅስቀሳ ይባላል።
የመምረጥ መብት ያላቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ የምርጫ ካርድ ያወጡ ሰዎች ወደ ምርጫ ጣቢያ ይሄዳሉ። እዚያም ማንም ሰው ሳያያቸው በሚስጥር የፈለጉትን ሰው ስም የያዘ ወረቀት ላይ ምልክት አድርገው በሳጥን ውስጥ ይከታሉ። ይህ ድምፅ መስጠት ይባላል።
ድምፅ መስጠቱ ሲያልቅ ሳጥኑ ይከፈትና ወረቀቶቹ በጥንቃቄ ይቆጠራሉ። ብዙ ሰው የመረጠው እና ከፍተኛ ድምፅ ያገኘው ዕጩ አሸናፊ ሆኖ ለመራጩ ወኪል ይሆናል።
ምርጫ ሁሉም ሰው በእኩልነት ድምፁን የሚያሰማበት በጣም ጥሩ መንገድ ነው። ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ ትልልቅ ሰዎች በሙሉ ሀገራቸውን የሚመራ መልካም ሰው ለመምረጥ ድምፅ ይሰጣሉ። ይህ ሥርዓት ሁሉም ሰው ተከባብሮና ተስማምቶ በሰላም እንዲኖር ይረዳል።
ልጆችም ቢሆኑ በትምህርት ቤት ዛሬ ምን እንጫወት ወይም የትኛውን መጽሐፍ እናንብብ ለሚለው ጥያቄ እጅ በማውጣት ድምፅ ሲሰጡ ትንሽ የምርጫ ጨዋታ እያካሄዱ ነው ማለት ነው።
ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ኢፌዴሪ)
ተረት
ኤሊ እና ቶሚ
ቶሚ በጫካው ውስጥ ካሉ እንስሳት ሁሉ እሱ ብቻ በጣም ፈጣን እንደሆነ ያስብ ስለነበር ሁልጊዜ በትዕቢት ይፎክር ነበር። አንድ ቀን መንገዱ ላይ በዝግታ የምትጓዘውን ኤሊ አገኛትና “አንቺ ድንጋይ የምታክዪ ኤሊ እኔ እኮ በደቂቃ ውስጥ ሙሉውን ጫካ እዞረዋለሁ፤ አንቺ ግን እስከ ማታም ከአንድ ዛፍ ስር አትንቀሳቀሺም” እያለ ይሳለቅባት ጀመር።
ኤሊዋም በትዕግሥት ፈገግ አለችና “እስቲ ካልከኝ እዚያ ማዶ ከሚታየው ትልቅ የዋርካ ዛፍ ድረስ የመሮጥ ውድድር እናድርግ” ስትል ጠየቀችው። ቶሚም በሃሳቡ እየሳቀ “ውድድሩን አሁኑኑ እንጀምር” አላትና መሮጥ ጀመረ።
ቶሚ በጥቂት ሰኮንዶች ውስጥ በጣም ርቆ ሄደ። ወደ ኋላው ዞሮ ሲያይ ኤሊዋ ገና ከጀመረችበት ቦታ እንኳ ብዙ አልራቀችም ነበር። በዚህ ጊዜ ቶሚ “ይህች ኤሊ እኔ ጋር ለመድረስ ብዙ ሰዓት ይፈጅባታል፤ ስለዚህ እዚህ ጥላ ስር ጥቂት ላሸልብ” አለና በትልቅ ዛፍ ስር ጋደም ብሎ እንቅልፍ ወሰደው።
ኤሊዋ ግን ሳታቋርጥ በአንድ አቋም እና በዝግታ ጉዞዋን ቀጠለች። ቶሚ እዚያው በረጅም እንቅልፍ ውስጥ እያለ ኤሊዋ ሳታቋርጥ በመጓዝ እሱ የተኛበትን ዛፍ አልፋ ሄደች።
ቶሚ በድንገት ከእንቅልፉ ሲነቃ ፀሐይዋ ልትጠልቅ አዘቅዝቃ ነበር። ደንግጦ ወደ መጨረሻው መስመር ሲመለከት ኤሊዋ ቀድማው ትልቁ የዋርካ ዛፍ ጋር ደርሳ አሸናፊ ሆና አገኛት። ቶሚም በትዕቢቱ በጣም አፈረ። ይህ ተረት የሚያስተምረን በችሎታችን መታበይ እንደሌለብን እና ማንኛውንም ሥራ በትዕግሥትና ባለማቋረጥ መሥራት ሁልጊዜ ወደ ስኬት እንደሚያደርስ ነው።
ምንጭ፡- የኤሶፕ ተረቶች
ሞክሩ
- በዓለም ላይ ካሉ ሀገራት ሁሉ በቆዳ ስፋት (በትልቅነት) አንደኛ የሆነችው ሀገር ማን ናት?
- በሰውነታችን ውስጥ ደም በመላው አካላችን እንዲሰራጭ የሚረጨው (ፓምፕ የሚያደርገው) አካል የትኛው ነው?
- እናቱ ሳትወለድ ልጇ ይሮጣል?
መልስ
- ሩሲያ
- ልባችን
- ጭስ
ነገር በምሳሌ
ድር ቢያብር አንበሳ ያስር፦
በአንድነት ሲረዱዱ ትልቅ ሥራ ይሠራል።
-ላም አለኝ በሰማይ ወተቷንም አላይ፦
በአፍ ብቻ ትልቅ ነገር አለኝ እያሉ መፎከር ዋጋ እንደሌለውና በተግባር የሚታይ እውነተኛ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ያስተምራል።
-”የታላቅ ምክር ከጥላ ስር ያሳድራል፦ የትልልቅ ሰዎችን ምክር መስማት ሁልጊዜ ከመጥፎ ነገር ይጠብቀናል፤ ጥላም ይሆነናል።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


