ኢቦላ ምንድን ነው?

0
142

ኢቦላ በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ እና በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው በኢቦላ ቫይረስ ከሚያዙ ሰዎች 9ዐ በመቶ ያህሉን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው፡፡

በሽታው ሰውን ብቻ ሳይሆን እንደ ጦጣ፣ ጉማሬና ዝንጀሮ ያሉ እንስሳትንም እንደሚያጠቃ የድርጅቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

የኢቦላ ወረርሽኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው እ.አ.አ በ1976 በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ ኢቦላ በተሰኘ ወንዝ አካባቢ በሚገኝ መንደር ነው፡፡ የቫይረሱ ምንጭ ምን እንደሆነ እስካሁን በውል እንደማይታወቅ የጠቀሰው መረጃው መጀመሪያ በተከሰተበት ወቅት  በሌሊት ወፍ ላይ እንደተከሰተ ነው ያመላከተው፡፡

በሽታው በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው በንክኪ በመተላለፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት ይዳርጋል፤ ከፍተኛ የስርጭት ፍጥነትና የሞት ምጣኔ ያለው እጅግ አደገኛ ወረርሽኝ መሆኑንም መረጃው አመላክቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና በዩጋንዳ በቡንዲቡግዮ የቫይረስ ዝርያ የሚመጣ አደገኛ የኢቦላ ወረርሽኝ መከሰቱን የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ግንቦት 09 ቀን 2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። እስከ ግንቦት 16 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜም በቤተ ሙከራ የተረጋገጠ ከ101 የሚበልጡ ታማሚዎች ተመዝግበዋል፡፡

ከ900 በላይ ከበሽታው ጋር ንክኪ ያላቸው ተጠርጣሪዎችም በከፍተኛ የሕክምና ክትትል ላይ ይገኛሉ።

 

ቫይረሱ እንዴት ይተላለፋል?

የኢቮላ ቫይረስ  ከታመመው ሰው ቁስል፣ ደም፣ ምራቅ፣ ትውከት፣ አይነ ምድር እና ሽንት ጋር በቀጥታ በመነካካት ወይም እነዚህ ፈሳሾች ወደ ጤነኛ ሰው ዐይን ተረጭተው ከገቡ፣ ከሕመምተኛው ሰው በወጣ ፈሳሽ የተከበለ ጨርቅን በመጠቀም፣ ንጽሕናቸው ባልተረጋገጠ ወይም ሌሎች ሕሙማን የተጠቀሙባቸውን መርፌ ሳይቀቅሉ በመጠቀም፣ ታማሚው የተጠቀመበትን መርፌና ስለትነት ያላቸውን መሣሪያዎች በመጠቀም እና በበሽታው የሞተ ሰውን አስክሬን በቀጥታ በመንካት ይተላለፋል፡፡

ምልክቶች

በኢቦላ በሽታ የተጠቃ ሰው በመጀመሪዎቹ ቀናት ከፍተኛ የሆነ እና ድንገተኛ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ከፍተኛ የድካም ስሜት እና ራስ ምታት ይታይበታል፤ ከዚያም የቆዳ ሽፍታ ይከተላል፡፡

ከነዚህ ምልክቶች በኋላም ማስመለስ/ትውከት/፣ የሆድ እና የጉሮሮ ሕመም እንዲሁም ተቅማጥ ያስከትላል፡፡ ምልክቶቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመባባስ ወደ ጉበት ሕመም፣ ክብደት መቀነስ፣ መቃዠት፣ የኩላሊትና የሳንባ ሕመም ሲሸጋገሩ አንዳንድ ጊዜም ከሁሉም የሰውነታችን ክፍት ቦታዎች ደም መፍሰስ እና የዋና ዋና የሰውነታችን አካላት በአንድ ጊዜ ሥራ ማቆም ሊከሰት ይችላል፡፡

አንድ ሰው በኢቦላ በሽታ አምጪ ተህዋስ ከተለከፈበት ጀምሮ ምልክቱ ከሁለት እስከ 21 (በአማዛኙ ከ8 እስከ 12) ቀናትን ሊወስድ ይችላል፡፡ ታማሚው ምልክቶችን ካሳየበት ጊዜ ጀምሮ በሽታውን ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በበሽታው ተይዞ ምልክቶቹን ማሳየት ባልጀመረባቸው ቀናት በሽታው አይተላልፍም፡፡

 

የኢቦላ ዓይነቶች

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ አምስት ተለይተው የታወቁ የኢቦላ ቫይረስ ዝርያዎች አሉ፡፡ እነዚህም ዛየር ኢቦላ ቫይረስ፣ ሱዳን ኢቦላ ቫይረስ፣ ቡንዲቡግዮ ኢቦላ ቫይረስ፣ ታኢ ደን ኢቦላ ቫይረስ እና ሬስቶን ኢቦላ ቫይረስ ናቸው።  እያንዳንዱ ዝርያ በአካባቢያዊ ስርጭት እና ተያያዥ ወረርሽኞች ይለያያል።

 

ጥንቃቄ እና የሕክምና ርዳታ

በኢቦላ በሽታ የተጠቃን ወይም የተጠረጠረን ሰው በተቻለ መጠን ለብቻው በተዘጋጀ ቦታ ለይቶ ማስቀመጥ ይገባል፤ ወደ ጤና ተቋማት በሚወሰድበት ወቅትም ከታማሚው ጋር አላስፈላጊ ንክኪ አለማድረግ፣ በበሽታው ከተጠቃ ወይም ከተጠረጠረ ሰው ወይም የሰውነት ፈሳሽ ጋር ንክኪ ከተፈጠረ ወዲያውኑ እጅን በውኃና በሳሙና መታጠብ፣ በበሽታው የተጠቃውን ሰው በምንረዳበት ወይም በምንንከባከብበት ጊዜ የእጅ ጓንት፣ የዐይን፣ የፊት መሸፈኛ እና ሌሎች የሰውነት መከላከያ መሣሪያዎች መጠቀም ግዴታ ነው፡፡

በበሽታው የተጠቃ ወይም የተጠረጠረ ሰው የሰውነት ፈሳሽ መሬት ከበከለ በረኪና ጨምሮ ከ15 ደቂቃ በኋላ ማጽዳት እንዲሁም በቆሻሻ የተነካኩ ቁሶችንና አልባሳትን መቃጠል፣ የጋራ እጅ መታጠቢያ አለመጠቀም፣ እንዲሁም የቀብር ሥነ ሥርዓት ሲፈፀም አስከሬኑን በኘላስቲክ ከረጢት መጠቅለል፣ የቀብር ሥነ ሥርዓቱም በሰለጠነ የጤና ባለሙያ ምክር መታገዝ  እንደሚገባው  መረጀጃው አመላክቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት በኢቦላ ቫይረስ የተጠረጠረ ወይም የታመመ ሰው አለመገኘቱን ጤና ሚኒሥቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

አንድ ሰው የኢቦላ በሽታ በተከሰተበት አካባቢ ከነበረና  በበሽታው ከተያዘ ወይም ከተጠረጠረ ሰው ጋር ንክኪ ፈጽሞ ከሆነ በአፋጣኝ የሕክምና ርዳታ ማግኘት አለበት፡፡ የሚደረገው ርዳታ ሰዎችን ከበሽታው ለመታደግ እና  የበሽታውን መስፋፋት ለመግታትም ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ የዓለም የጤና ድርግት መረጃ ያመላክታል፡፡

ይሁን እንጂ በሽታው ከተገኘባቸው ሀገራት ጋር ቀጥተኛ የድንበር ግንኙነት ባይኖርም የበሽታውን አስከፊነትና ዓለም አቀፍ አደገኛነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ወረርሽኙ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥት ከፍተኛ ጥንቃቄ የታከለበት የቅድመ ዝግጅት ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።

ይህንን ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የወረርሽኝ መከላከያ እርምጃዎችን አጠናክሯል። በሁሉም ዓለም አቀፍ የየብስ መግቢያና መውጫ ኬላዎች እንዲሁም በአየር ማረፊያዎች ላይ ጥብቅ የልየታና የቅኝት ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የሚኒሥትሩ መረጃ ጠቁሟል።

በተጨማሪም የጤና ተቋማትና የቤተ ሙከራዎች ዝግጁነት እንዲጨምር ተደርጓል፤ አስፈላጊ የሕክምና ግብዓቶች አቅርቦትን የማሟላት ሥራም በተጠናከረ ደረጃ እየተከናወነ መሆኑን ሚኒሥቴሩ ገልጿል።

መረጃ

የኢቦላ ዓይነቶች

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ አምስት ተለይተው የታወቁ የኢቦላ ቫይረስ ዝርያዎች አሉ፡፡ እነዚህም ዛየር ኢቦላ ቫይረስ፣ ሱዳን ኢቦላ ቫይረስ፣ ቡንዲቡግዮ ኢቦላ ቫይረስ፣ ታኢ ደን ኢቦላ ቫይረስ እና ሬስቶን ኢቦላ ቫይረስ ናቸው።  እያንዳንዱ ዝርያ በአካባቢያዊ ስርጭት እና ተያያዥ ወረርሽኞች ይለያያል።

 

(ሙሉ ዓብይ)

በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here