ሙታን የሚያጫውቱበት

0
151

የዐቢይ ጾም ወራት ሲገቡ የከተማዋና የገዳማቱ ድባብ በዝምታና በተመስጦ ሲዋጥ ከርቀት የሚሰማ አንድ ረቂቅና ሰላማዊ የድምፅ ሞገድ አለ። በኃይለኛ የሙዚቃ መሣሪያዎች ጩኸት ለደከመችው የሰው ልጅ ነፍስ ይህ ከቆዳ፣ ከእንጨትና ከጅማት የሚወጣ የበገና ድምፅ ልዩ በረከትና ዕረፍት ነው።

“ሙታን ሕያዋንን ያጫውታሉ” እንደሚባለው ከሞቱ እንስሳትና ዕፅዋት የተገኘው ይህ መሣሪያ በሰዎች እጅ ላይ ሕያው ሆኖ መንፈሳዊ ድምፁን ሲያስተጋባ ነፍስን ከምድራዊ ጭንቀት አውጥቶ ወደ ሰማያዊ ተመስጦ ያሻግራል። በገና መሣሪያ ብቻ አይደለም፤ እርሱ የሺህ ዓመታት የታሪክ አሻራ፣ የቅዱሳን ምስጢር፣ የማኅበረሰባችን የኑሮና የፍልስፍና መስታወት ነው።

በገና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ እጅግ ጥንታዊ ከሆኑ የዜማ መሣሪያዎች መካከል አንደኛው ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ ሰነዶች እንደሚያስረዱት የበገና መነሻ ከዮባል (ኦሪት ዘፍጥረት 4፥21) ጋር ይያያዛል።

መጽሐፍ ቅዱስ “በገናና መለከትን ለሚይዙ ሁሉ አባት ነበር” ሲል የዩባልን የበገና ታሪክ ቀዳሚነት ያረጋግጣል። ሆኖም ግን በገናን በታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ እንዲያገኝ ያደረገው ንጉሥ ዳዊት ነው። ዳዊት 150 መዝሙራትን በገና እየደረደረ በመዘመሩና መሣሪያውን ለፈውስና ለጸሎት አገልግሎት በመጠቀሙ በገና እስከ ዛሬ ድረስ የዳዊት በገና እየተባለ ይጠራል።

ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ3000 እስከ 1000 ዓመት ባለው ጊዜ በጥንቷ ግብፅና ሜሶፖታሚያ ነገሥታት ለአምልኮና ለሥርዓተ መንግሥት ይጠቀሙበት እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።

ወደ ኢትዮጵያ እንዴትና መቼ መጣ? ለሚለው ጥያቄ የታሪክ ድርሳናት የሚያመለክቱት በቀዳማዊ ምኒልክ ዘመን (ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት) ታቦተ ጽዮንን ይዘው የመጡት ሌዋውያን በገናን ይዘው እንደገቡ ነው። በገና በኢትዮጵያ ገዳማትና አድባራት ውስጥ በካህናትና መነኮሳት አማካኝነት ለብዙ ዘመናት ተጠብቆ ቆይቷል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ማህበረ ቅዱሳን የባሕርዳር ማዕከል ያሰለጠናቸውን የበገና ተማሪዎች ሲያስመርቅ የበገና ታሪክ፣ ክብር እና ተግዳሮቶች ላይ ጥናት ያቀረቡት ዲያቆን ዶክተር ታደሰ ዘርፉ የዳሰሳ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በገና ከመንፈሳዊ አምልኮ ባሻገር ማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ጠቃሜታው እጅግ የጎላ መሣሪያ ነው። “በዘመናዊው የነርቭ ሳይንስ (Neuroscience) ጥናት መሠረት የበገና ድምፅ ዝቅተኛ ድግግሞሽ (frequency) ስላለው የሰውን ልጅ የመረጋጋት ነርቭ  ያነቃቃል። ይህም ጭንቀትን በመቀነስ፣ የልብ ምትን በማስተካከልና ሰላምን በመስጠት ረገድ ከፍተኛ የጤና ጠቃሜታ አለው። በሳይንሳዊ ሙከራዎች እንደተረጋገጠው፣ የበገና ድምፅ ሰዎችን ከተለያዩ የድብርትና የጭንቀት ስሜቶች ያሳርፋል” ያሉት ዶክተር ታደሰ ናቸው።

“በአብዛኛው ቤተክርስቲያናችን በገናን አባቶቻችን በሁሉም ቦታ ይገለገሉበታል፤ ነገር ግን በአብይ ጾም ወቅት በብዛት የሚደረደር የዜማ መሣሪያ ነው። እንዲሁም ለግል ጸሎትና ለንስሐ፣ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ፣ ለተመስጦ፣ በተለይ ባሕታውያን በአምልኮቱ ሁሉ የሚዘምሩበት የዜማ መሣሪያ ነው” በማለት ጥቅሙን አስታውሰዋል።

በሌላ በኩል በገና በኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ውስጥ የቅኔ፣ የሞራልና የሕይወት ፍልስፍና መግለጫ መስታወት ሆኖ አገልግሏል። ቀደምት አባቶቻችን በገናን ለሃይማኖታዊ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ስለ አገር ፍቅር፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ትዕግሥትና በተለይም ስለ ሞት አይቀሬነት ጥልቅ ቅኔዎችን የሚቀኙበት መሣሪያ ነው ብለዋል።

“እኔስ መስሎኝ ነበር ደሃ ነው ደካሚ፣

ለካስ ሁሉ ኖሯል አፈር ተሸካሚ”

የሚለው የበገና ግጥም ሰውን ሁሉ እኩል የሚያደርገውን ሞትና ምድራዊ ሕይወት አላፊ መሆኑን ያስተምራል።

በገና አጨዋወቱና አጠቃቀሙ የራሱ የሆነ ትዕግሥትና ሥርዓት ይጠይቃል። በጥንት ዘመን መሣሪያው የሚሠራው ከከባድ እንጨት ስለነበር ዘማሪው ተቀምጦ እንዲደረድር ይገደድ ነበር። አሁን አሁን ግን ቀለል ካሉ እንጨቶች መሠራት በመጀመሩ ቆሞ መጫወትም ተችሏል። በገና ሲደረደር የግራ እጅ ጣቶች በአውታሮቹ ላይ ድምፅን ለመቆጣጠር ይቀመጣሉ፤ በቀኝ እጅ ደግሞ አውታሮቹ ይመታሉ (ይደረደራሉ)። ይህም ጥልቅ ትኩረትንና መንፈሳዊ ተመስጦን የሚጠይቅ የተለየ ጥበብ ነው።

ብዙ ጥቅሞች ያሉት በገና ከአጼ ኀይለሥላሴ የንግሥና ጊዜ ማብቃት በኋላ ክብሩ ተቀዛቅዞ ነበር። በቤተክርስቲያን ውስጥ በተቀዛቀዘ መንፈስ ውስጥ ቀጥሎ ከኢትዮጵያውያን ሚሊኒየም በኋላ በበገና ትምህርት ቤቶች እና  በተለያዩ ማሠልጠኛዎች አማካኝነት በወጣቶች ዘንድ ሰፊ መነቃቃትን አሳይቷል።

አሁን ላይ በገና በመንፈሳዊ የአደባባይ በዓላት በስፋት ጥቅም ላይ የሚል መሣሪያ ሆኗል። በበገና በብዛት ሆነው የሚዘምሩ ወጣቶችን ማየት የተለመደ ነው። በገናን የሚያሰለጥኑ ትምህርት ቤቶችም እየተበራከቱ ነው። የዳሰሳ ጽሁፍ ያቀረቡት ዶክተር ታደሰ “በገና ማደጉ እና መስፋፋቱ ጥሩ ቢሆንም ችግሮችም ገጥመውታል” ይላሉ።

የመጀመሪያው ችግር የክብር መሸርሸር ነው። መዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ በዓለማዊ መድረኮች፣ ለንግድና ለዝና ያለ ሥርዓቱና ያለ ክብሩ ጥቅም ላይ መዋሉ አደጋ ነው ብለዋል።

ቀጥሎ የሚመጣው ችግር ከስርዓት ውጪ መጠቀም ነው። በገናን ያለአግባብ፣ ከቤተክርስቲያን ሥርዓትና ትውፊት ውጭ በሆኑ የዓለማዊ ሙዚቃ ስልቶችና ባልተፈቀዱ መድረኮች ላይ መጫወትም አሁናዊ ችግር ነው ብለዋል።

ሌላኛው ችግር በገና ማሠልጠኛ ተቋማትን የሚመለከት ነው።  ትኩረታቸውን ከጥንታዊው መንፈሳዊ ሥርዓት ይልቅ ወደ ንግድና ወደ ተራ የሙዚቃ መሣሪያነት በመቀየር የበገናን ክብርና ምስጢር ማቃለላቸው ዋነኛ ችግሮች ናቸው።

በገና አሰልጣኞች በቤተክርስቲያን ስርዓት የሚታቀፉበት አሠራር አለመኖሩ ሰልጣኞችን በገንዘብ የሚያስተምሩ በመሆናቸው አዝማሚያው የንግድ መስመር እየያዘ ነውም ብለዋል።

ጥናት አቅራቢው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የግሏ የሆነውን መንፈሳዊ የዜማ ማሣሪያ በገናን መቆጣጠር እና የማሰልጠኛ ተቋማትን መደገፍ እና መቆጣጠር እንዳለባት አሳስበዋል።

በገና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እጅግ ውድ መንፈሳዊና ታሪካዊ ቅርስ ነው። ድምፁ ነፍስን የሚያረጋጋ፣ ይዘቱ ምስጢረ መለኮትን የሚሰብክ ማኅበራዊ ቅኔው ደግሞ የማኅበረሰባችንን ጥልቅ ፍልስፍና የሚያንጸባርቅ ነው።

ዛሬ ላይ የተጋረጡበትን የክብር መሸርሸር ፈተናዎች ለመቅረፍ ቤተክርስቲያንና የሚመለከታቸው ተቋማት የበገናን ትክክለኛ ሥርዓት አዘማመርና ትውፊት ጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል።

በገና በብዛት ሃይማኖታዊ  ይዘቱን ጠብቆ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ስለ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለ ስቅለቱ፣ ስለ ጸሎት፣ ስለ ሥነምግባር፣ ስለ ሞት የሚጠቅሱ ይዘቶች ይዳሰሱበታል።

“ከቶ አይቀርም ሞቱ

ምንም ቢታከቱ፣

ምንም ቢሰነብቱ”

በማለት የሰው ልጅን ያጽናናሉ፣ ያስጠነቅቃሉ፣ ይመክራሉ፣ ስለሞት እንዲያውቅ ያደርጋሉ። ምን ያህል ብንፈራ ሞት የማይቀር ነውና አይቀሬነቱን አውቆ የሰው ልጅ በጥንቃቄ እንዲኖር ይመክራሉ።

 

 

ማረፊያ

የበገና ግጥም

መከራውን ሳስብ ሳስታውስ ቀኑን

ይቆስላል ይደማል ልቤ በኀዘን

መች ለራሱ ነበር ይህ ሁሉ መከራ

መስቀል ተሸክሞ የወጣው ተራራ

ሲያጎርሱት ሚናከስ ሰው ክፉ ነውና

እውሩን ቢያበራ ጎባጣን ቢያቀና

ጌታዬ ሰቀሉህ አይሁድ ጨከኑና

ምነው አያሳዝን የአይሁድ ክፋት

የዝናቡን ጌታ ውኃ ሲነፍጉት፡፡

(አቢብ በዓለሜ)

በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here