በቻይና ምእራባዊ ጐንዶንግ ግዛት የሎንታንግ ከተማ ኗሪው የ56 ዓመቱ ጐልማሳ ለሦስት ዓመታት ሲያሰቃየው ከነበረ ህመም እና መሽናት ያለመቻል ችግር ለመዳን ወደ ጤና ተቋም ያመራል፤ እናም በቀዶ ህክምና አንድ ነጥብ ሦስት ኪሎ ግራም የሚመዝን ጠጠር የወጣለት መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
በእርሻ የሚተዳደረው ቼን የተባለው ጐልማሳ የሽንት መቆራረጥ እና ህመም ያሰቃየው እንደነበረም ነው የተመላከተው፡፡
ለችግሩ ስርነቀል መድሃኒት ሳያገኝ ማስታገሻ እየወሰደ የቆየው ጐልማሳ ሲብስበት በአቅራቢያው “ሹዌን” አካባቢ ወደ ሚገኝ ጐንዶንግ ሆስፒታል ያመራል፡፡ ሆስፒታሉ በጐንዶንግ ህክምና ዩኒቨርሲቲ የተካተተ ነው፡፡ በጤና ተቋሙ ያሉ ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎችም ምርመራ ያደርጉለታል፡፡
በምርመራ ውጤቱም በሽንት ፊኛው ውስጥ ትልቅ መጠን ያለው ጠጠር መታየቱን እና ጠጠሩ የሽንት ቱቦ መውጫውን መድፈኑ የጤና እክል እንደፈጠረበት ይነገረዋል ̄ ታማሚው፡፡
በሆስፒታሉ የ “ዩሮሎጂ” ክፍል ምክትል ኃላፊ ሊንዩዋን እንደገለጹት በሽንት ፊኛ ውስጥ በ “ኤክስሬይ” አንድ ነጥብ ሦስት ኪሎ ግራም በግምት ሁለት የአዋቂ ቡጢ የሚያክል ጠጠር መኖሩን አረጋግጠዋል፡፡
ጠጠሩ ትልቅ በመሆኑ ፈጥኖ ካልወጣ የከፋ ሁኔታ ሊያስከትል እንደሚችል አምነው ታማሚውን አማክረው በመስማማቱ የህክምና ቡድን አቋቁመው ቀዶ ህክምና ይሰራለታል፡፡
በውጤቱም ለሆስፒታሉ በትልቅነቱ የመጀመሪያ የሆነ አንድ ነጥብ ሦስት ኪሎ ግራም ጠጠር የወጣለት መሆኑን ጽሁፉ በማደማደሚያነት አስፍሯል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


