በምርጫ ወቅት ብዙኃን መገናኛ ሚናዎቹን በአግባቡ መወጣት ከቻለ ለሀገር ሰላም እና መረጋጋት ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ የገለፀልን በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሥልጠናና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ሐሰን መሀመድ ነው፡፡ እንደ ዳዳይሬክተሩ ማብራሪያ የግልም ይሁኑ የመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎች በምርጫ ወቅት ማድረግ ያለባቸው ዋና ዋና ሚና ተለይቶ የተቀመጠ ነው፡፡
የብዙኃን መገናኛ አውታሮች በመጀመሪያ የተሰጣቸው ሚና በሀገሪቱ ስለሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ መረጃን በአግባቡ እንዲያኝ ማስቻል ነው፡፡ ይህን ተከትሎም ተፎካካሪ ፓርቲዎች መርሃ ግብራቸውን (ማንፌስቶ) ማስተዋወቅ ፣ ምን ሠርተዋል፣ ቢመረጡ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ… የሚለውን ሃሳብ መራጩ ሕዝብ እንዲያውቅ መሥራት፣ በምዝገባ፣ በምርጫ ፣ በድምጽ ቆጠራ… ያለውን ሂደት ማሳወቅ እንዲሁም ሲጠናቀቅ (ውጤት ሲገለፅ) ያሉትን መረጃዎች መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሚሰጡት መረጃ ደግሞ ወቅቱን የጠበቀ፣ በቂ ፣ ትክክለኛ፣ ሚዛናዊ …ሆኖ ሲገኝ ሚናቸውን በትክክል ተወጥተዋል ማለት እንደሚቻል ጋዜጠኛ ሐሰን አስገንዝቧል፡፡
ብዙኃን መገናኛዎች መረጃ ከማቅረብ ቀጥሎ ያላቸው ሚና የውይይት መድረክ መፍጠር ነው፡፡ በዚህ ደግሞ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ተፎካካሪዎች የሚንቀሳሱት በምርጫ ወቅት በመሆኑ የሚከራከሩበት፣ ሕዝቡ ጥያቄ የሚጠይቅበት ፣ ከማንም ያልወገነ ገለልተኛ መድረክ የሚዘጋጅበት የውይይት መድረክ መፍጠር ሌላው የብዙኃን መገናኛ ሚና ነው፡፡
ብዙኃን መገናኛዎች የጥበቃ እና የክትትል ሚና እንደሚኖራቸውም ጋዜጠኛ ሐሰን ጠቁሟል፡፡ ይሄ ማለት የምርጫው ሂደት ፍትሐዊ፣ ነፃ እና ግልፅ መሆኑን መከታተል ዋና ሚናቸው ነው፡፡ መረጃ ከመስጠት፣ የውይይት መድረክ ከመፍጠር ባሻገር የክትትል ሚናቸው በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ጥሰቶች እንዳይኖሩ፣ የመንግሥት ሃብት ለምርጫ ቅስቀሳ እንዳይውል፣ ምርጫው ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ ፣ ነፃ እና ገለልተኛ እንዲሆን በማድረግ የክትትል ሚናቸውን የሚወጡበት ጊዜ ነው፡፡
ጋዜጠኛ ሐሰን እንዳብራራው ሌላው የብዙኃን መገናኛ ሚና ማረጋጋት እና ሰላም መስበክ ነው፡፡ የማህበረሰቡን የሃሳብ ልዩነቶች በአግባቡ ያስተናግዳሉ፤ ምርጫን እና የምርጫ ቆጠራ ሂደቱ በትክክል መደረጉን ያሳውቃሉ፡፡
የብዙኃን መገናኛዎች ሚናቸውን ሲወጡ እና ሳይወጡ አሉታዊ እና አወንታዊ ችግሮች መኖራቸውን የጠቆመው ጋዜጠኛ ሐሰን፤ ሚዲያ ኃላፊነቱን ሲወጣ ለሀገር መረጋጋት፣ ለአንድነት፣ ለመተማመን በተለይ ዴሞክራሲ አድጎ ሰላም እንዲሰፍን እና ልማት እንዲወጣ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ በምዕራብ አፍሪካዋ ጋና የምርጫ ፉክክር በሚካሄድበት ወቅት የግልም ሆነ የሕዝብ ሚዲያዎች የምርጫ ውጤቶችን ከታችኛው እስከ ላይኛው ምርጫ ጣቢያ ድረስ በፍጥነት በማድረስ በታማኝነት እና በሚዛናዊነት በመዘገባቸው በመጣው ውጤት ሕዝቡም ለማመስገን በቅቷል፡፡ ሚዲያዎች የምርጫ ኮሚሽኑን ሥራ በንቃት በመከታተል ሠርተዋል፡፡ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ሚናቸውን ፊት ለፊት በቀጥታ ስርጭት በመወጣት አወንታዊ አስተዋፅኦ አበርከተዋል፡፡
በምርጫ ዘገባ አስፈላጊ ሚናቸውን ባለመወጣታቸው ደግሞ አሁንም ድረስ ስማቸው በክፉ የሚጠቀሱ ብዙኃን መገናኛዎች አሉ፡፡ ለዚህ በምሳሌነት የምትነሳው ጎረቤት ሀገር ኬንያ ናት፡፡ እ.አ.አ በ2007 የምርጫ ወቅት አንዳንድ ሚዲያዎች በተለይ (ካስ) የሚባል ጣቢያ የዘረኝነት ወሬን በቀጥታ ስርጭት ላይ በማስተላለፉ እስከ አንድ ሺህ ሰዎች ሲገደሉ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ከአካባቢያቸው እንዲፈናቀሉ፣ በርካታ ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንዲደርስባቸው ምክንያት ሆኗል፡፡
በአሜሪካም ፎክስ ኒውስ የተባለው የዜና ማሰራጫ የምርጫ ማሽኑ የተጭበረበረ ነው ብሎ ባሰራጨው ያልተረጋገጠ መረጃ ብዙ ከተሞች ላይ ግጭቶች ተነስተው ብዙ ሃብትና ንብረት ወድሟል፡፡ እውነታው ሲረጋገጥ ደግሞ ሚዲያው ወደ አንድ ቢሊዮን ብር እንዲቀጣ ተደርጓል፡፡ ሚዲያ ምንጊዜም ለሕዝቡ ማድረግ ካለበት ነገር ይልቅ የራሱን ጥቅም ብቻ ካስቀደመ እና ሚናውን ካልተወጣ ብዙ ችግር እንደሚያመጣ እነዚህን ማሳያዎች ማየት ብቻ በቂ እንደሆነ ጋዜጠኛ ሐሰን አስገንዝቧል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ጋዜጣኛ ሚናውን ይወጣ ሲባል መረጃዎችን በተለያየ መንገድ አጣርቶ (ፋክት ቼክ) መያዝ ይገባዋል ማለትም ነው፡፡ ሁል ጊዜ በዘገባ ወቅት ነገሮችን ማጣራት አለበት፡፡ እውነታው ከተረጋገጠ በኋላ ደግሞ በቃለ መጠይቅ ወቅት የጥላቻ ንግግር እና የግለሰብ ስሜት መቀላቀል የለበትም፡፡ ሁልጊዜም የምርጫ ዘገባ ሚዛናዊ እና ፍትሐዊ እንዲሆን ከጅምሩ እስከ ውጤቱ ድረስ መሥራት ይገባል፡፡ሥልጣን ላይ ያለውን እና የሌሎችን ተፎካካሪ ፖርቲዎች ድምጽ እኩል ሚዛን ላይ አስቀምጦ መሥራት ይገባል፡፡ ለሁሉም ተገቢውን የአየር ሰዓት እና ዓምድ በመመደብ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማስተናገድም ይገባል፡፡
ምርጫን የሚዘግቡ የጋዜጠኞችን ደኅንነት እና ሥነ ምግባርም መቆጣጠር ደግሞ ተገቢ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ሐሰን እንደሚለው የሚዲያ ተቋማት በምርጫ ዙሪያ ለጋዜጠኞቻቸው ሥልጠና መስጠት እና ሥራቸውን መከታተል ይኖርባቸዋል፡፡
“በምርጫ ወቅት የሚዲያ ዋና ሚና የዳኝነት እንጂ የተጫዋችነት ሚና አይደለም” ያለው ዳይሬክተሩ ነገሮችን ከግራም ከቀኝም ማየት አለበት፡፡ በዚህ ደግሞ ጋዜጠኛው የሀገርን ሰላም የመጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነቱን ይወጣል ማለት ነው፡፡ የብዙኃን መገናኛ የብዝኃነት፣ የፍተሐዊነት እና በዲሞክራሲያዊነት የማመን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህንን ከተወጡ ደግሞ በሕዝቡ ተአማኒነት እንደሚያገኙ ጋዜጠኛ ሐሰን አስገንዝቧል፡፡
በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት መምህሩ ዘለቀ ተሾመ (ዶ/ር) በበኩላቸው ለአሚኮ በሰጡት መረጃ መገናኛ ብዙኃን በምርጫ ወቅት ሀሰተኛ መረጃዎች የሚበዙበት በመሆኑ ይህን ቀድመው መከላከልና የተረጋገጡ መረጃዎች የማስተላለፍ ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል ። በተለይም በምርጫ ወቅት በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚተላለፉ ሀሰተኛ መረጃዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉና ህብረታቡስ እንዴት መለየት ይችላል? የሚለዉን ግንዛቤ መፍጠር እንደ ሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡
ምርጫ ለሀገር ግንባታ አንዱ ሂደት ነው፤ የሚሉት የጋዜጠኝነትና የሥነ-ተግባቦት መምህሩ፣ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ኢትዮጵያ የሚለውን ሀገራዊ ስሜት በመላበስ እና በጋራ በመሥራት ለምርጫው ስኬታማነት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
መረጃ
በኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ መሠረት
- በምርጫ ጣቢያ የተደረገ የቆጠራ ውጤት ቆጠራው በተጠናቀቀ በአንድ ሰዓት ውስጥ በምርጫ ጣቢያው ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ወጥቶ ለሕዝብ በይፋ ይገለጻል፡፡
- የምርጫ ክልል የምርጫ ጽሕፈት ቤቶች የምርጫ ውጤት ከየምርጫ ጣቢያው እንደደረሳቸው ወይም የተረጋገጠ ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ካላጋጠመ በስተቀር በምርጫ ክልሉ የድምጽ መስጫ ጊዜው ከተጠናቀቀ በኋላ ከአምስት ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተወዳዳሪዎች ወይም ወኪሎቻቸው በተገኙበት ደምረው የተገኘውን ውጤት ለሕዝብ ይፋ ያደርጋሉ፡፡
- የምርጫ ቦርድ በአጠቃላይ የምርጫ ውጤት ከየምርጫ ክልሉ ተጠናቆ እስኪደርሰው ድረስ ከየምርጫ ክልሉ የመጣለትን የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች አባላት የምርጫ ውጤት በጊዜያዊነት በቦርዱ ጽሕፈት ቤት ሊገልጽ ይችላል፡፡ ሆኖም የምርጫው ይፋዊ ውጤት በ10 ቀናት ውስጥ ካልተገለጸ ቦርዱ ጊዜያዊ ውጤቱን ይፋ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
- የምርጫው ሂደት ከተጠናቀቀና አስፈላጊ መረጃዎች ከተሰበሰቡ በኋላ የተረጋገጠ ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ካላጋጠመ በስተቀር ከምርጫው ቀን ቀጥሎ ባሉት 10 ቀናት ውስጥ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር፤ ድምፅ የሰጡ መራጮች ቁጥር፤ ድምፅ የሰጡና ያልሰጡ የተመዘገቡ መራጮች መጠን በመቶኛ፤ የተመረጡ እጩዎች የስም ዝርዝርና የተመረጡበት የምርጫ ክልል፤ የአሸናፊ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የግል ተወዳዳሪዎች ስምና ለየምክር ቤቱ ያሸነፉትን መቀመጫ ብዛት፤ ጥቅም ላይ የዋለ፣ ያልዋለ፣ ከጥቅም ውጭ የሆነ የድምፅ መስጫ ወረቀት እያንዳንዱ እጩ በየምርጫ ጣቢያው ያገኘው የድምፅ ውጤት እና ሌሎች አግባብነት ያላቸው መረጃዎች የያዘ ይፋዊ መግለጫ ያወጣል፡፡
- በምርጫ ክልል ደረጃ በተገለጹ ውጤቶች ላይ የቀረቡ አቤቱታዎች ውጤት መግለጹን እንዲዘገይ የሚያደርግ ከሆነ ይፋዊ ውጤት የሚገለጽበት ጊዜ እስከ 20 ቀን ድረስ ሊዘገይ ይችላል፡፡
ምንጭ- የምርጫ ቦርድ ድረ ገፅ
(ማራኪ ሰውነት)
በኲር የግንባት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ዕትም


