የኢትዮጵያ እግር ኳስ እና የዓለም ዋንጫ ህልም

0
221

ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መስራች ከመሆኗም ባሻገር በ1962 ዓ.ም የአፍሪካን ዋንጫ ማንሳቷ እንደ ትልቅ ብሔራዊ ኩራት የሚወሳ ነው፡፡ እነ መንግስቱ ወርቁ፣ ሉቺያኖ ቫሳሎ እና ኢታሎ ቫሳሎ የመሳሰሉ ጠንካራ ተጫዋቾችን የያዘው ብሄራዊ ቡድን በወቅቱ በአፍሪካ እግር ኳስ  ገናና ስም እንደነበረው የኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ ነገር ግን ይህ አንጸባራቂ ታሪክ የትላንት ጣፋጭ ትዝታ ብቻ ሆኖ ቀርቷል፡፡ እግር ኳስ ወደ ሳይንስ እና ግዙፍ ኢንዱስትሪ በተቀየረበት በዚህ ዘመን እኛ አሁንም በ60ዎቹ ገድል ከመኩራት አልፈን አዲስ ታሪክ መጻፍ ተስኖናል፡፡

እ.አ.አ በ2014 በብራዚል ለተካሄደው የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ከጫፍ ደርሳ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ይመራ የነበረው ያ ስብስብ ኢትዮጵያውያንን አንድ አድርጎ የዓለም ዋንጫን ህልም ለማሳካት ተቃርቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዋሊያዎቹ በጥሎ ማለፉ በናይጀሪያ ተሸንፈው ነበር ህልማቸው የተሰናከለው፡፡ ዛሬም ድረስ “ለምን በዓለም ዋንጫ መሳተፍ ተሳነን?” የሚለው ጥያቄ የስፖርት ቤተሰቡ የዘወትር ጥያቄ ነው፡፡

የፊፋ የዓለም ዋንጫ ከተጀመረበት ከ1930 እ.አ.አ አንስቶ እስካሁን ድረስ 14 የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በአጠቃላይ 61 ጊዜ አህጉሪቱን ወክለው በውድድሩ ላይ ተሳትፏል፡፡ የካፍ መስራቿ ኢትዮጵያ ግን አንድም ጊዜ በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ መሳተፍ አልቻለችም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  በየጊዜው በሚደረጉ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች ላይ ተስፋ አስቆራጭ ውጤት ሲያስመዘግብ ቆይቷል፤ እያስመዘገበም ይገኛል፡፡

ይህ የሆነውም  ዘመናዊ እግር ኳስ ከሚጠይቀው ሳይንሳዊ አካሄድ እጅግ በጣም የራቀ ጉዞ እያደረጉ በመሆኑ ነው ሲል በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ  አቶ አዲስዓለም ምህረት ከአሚኮ በኩር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ  ተናግረዋል፡፡

የእግር ኳስ ተሰጥኦ ብቻውን በቂ የሚሆንበት ጊዜ አሁን አልፏል፡፡

“ታላላቅ ሀገራትን ስንመለከት ተጫዋቾቻቸውን ከስድስት እና ከስምንት ዓመት ዕድሜያቸው ጀምረው በዘመናዊ አካዳሚዎች ውስጥ በስነምግብ፣ በአካል ብቃት፣ በታክቲክ እና በስነ ልቦና ኮትኩተው ነው የሚያሳድጉት” በማለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከዘመኑ ጋር እኩል እየተጓዘ እንዳልሆነ አቶ አዲስዓለም ያስረዳሉ፡፡

ይሁን እንጂ የዓለም ዋንጫን ትተን በመጀመሪያ አፍሪካ ዋንጫው ላይ አዘወትረን መሳተፍ ከቻልን የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ  በሂደት የሚመጣ ይሆናል- የአቶ አዲስዓለም ምህረት አስተያየት ነው፡፡ “ስለ ዓለም ዋንጫ ከማለማችን በፊት በአፍሪካ ዋንጫ በደንብ መሳተፍ ይኖርብናል፡፡ ማንኛውም ሀገር በአህጉሩ ውስጥ ያሉትን ጠንካራ ተጋጣሚዎች እንደ ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ እና ኮትዲቯር የመሳሰሉትን ማሸነፍ እና በቋሚነት መፎካከር ሳይችል በዓለም ዋንጫ መድረክ የላቲን አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀያላንን ለመግጠም ማለም አይቻልም” ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቁ ችግር መሰረታዊ ነገሮችን ካለመስራት እና ካለመተግበር የሚመነጭ መሆኑንም የስፖርት ሳይንስ  መምህሩ  እና ተመራማሪው አልሸሸጉም፡፡  “ታዳጊዎች ላይ ሲሰራ ዓለም ዋንጫን አቅደን አይደለም የምንሰራው” ይላሉ፡፡  በተለይ የህፃናት አካላዊ እድገትን  ከግምት ያስገባ ስልጠና እና አመጋገብ እንደሌለም ገልጸዋል፡፡ ጥራት ያላቸው እና ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ አካዳሚዎች በኢትዮጵያ በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው  ተጫዋቾች ዘመናዊውን የእግር ኳስ አመጋገብ እና ዲሲፕሊን እንደማይማሩ አቶ አዲስዓለም ይናገራሉ፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያ ስታዲየሞች በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ (ፊፋ) እና በካፍ መመዘኛ መሠረት ደረጃቸውን የጠበቁ ሆነው ባለመገኘታቸው ዋሊያዎቹ ጨዋታዎቻቸውን በገዛ ሀገራቸው እና በደጋፊያቸው ፊት ማድረግ እንዳልቻሉ ይታወሳል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታውን በገለልተኛ ሜዳ (እንደ ሞሮኮ እና ማላዊ ባሉ ሌሎች ሀገራት) እንዲጫወት መገደዱ ተጫዋቾች ከደጋፊዎቻቸው የሚያገኙትን ትልቅ የስነ ልቦና እና ሞራል ድጋፍ እንዲያጡ አድርጓቸዋል፡፡ የተሻለ እና ሀገርን የሚወክል ብሄራዊ ቡድን ለመገንባት ደረጃውን የጠበቀ የልምምድ ማዕከል እና የጨዋታ ሜዳ ሊሟላ እንደሚገባ የስፖርት ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት አቶ አዲስዓለም ያስረዳሉ፡፡

በተለያዩ ተቋማት የሚጠኑ ጥናቶች ተግባራዊ አለመሆናቸው ብሄራዊ ቡድኑ ለውጥ እንዳያመጣ አድርጓል፡፡ “ጥናቶች ቢጠኑም አንዱም ተግባራዊ ሲሆን  አንመለከትም” በማለት የፌዴሬሽኑን እና የሚመለከታቸውን አካላት የአፈጻጸም ድክመት ይጠቁማሉ ሲል አሰልጣኝ አዲስዓለም ተናግሯል፡፡ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች ቶሎ ቶሎ መቀያየር ቡድኑ ቋሚ የእግር ኳስ ባህል እና መለያ እንዳይኖረውም አድርጓል፡፡ አዲስ አሰልጣኝ በመጣ ቁጥር አዲስ ፍልስፍና ይዞ ይመጣል፤ ውጤት ሲያጣ ወዲያው ይባረራል፡፡

ይህ አዙሪት ተጫዋቾች ከአንዱ አሰልጣኝ ጋር ሳይላመዱ ሌላ ስለሚመጣባቸው በሜዳ ላይ የሚኖራቸው መግባባት እጅግ እንዲዳከም አድርጎታልም ብሏል አቶ አዲስዓለም፡፡

በዓለም አቀፍ መድረክ በተለይም በዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተወዳዳሪ እንዳይሆን የተጫዋቾች አካላዊ ብቃት፣ ስነ ልቦና እና የፕሮፌሽናሊዝም ማነስ ትልቅ መሰናክል ሆኖበታል፡፡ እንደ አቶ አዲስዓለም ገለጻ ፕሮፌሽናሊዝም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ገና ያልሰረጸ እሴት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ  ብሄራዊ ቡድን ከሰሜን እና ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ሲነጻጸሩ የአሸናፊነት ስነ ልቦናቸው እና የአካል ብቃታቸው ደካማ መሆናቸውንም ያስረዳሉ፡፡ አመጋገብን፣ የእረፍት ጊዜ አጠቃቀም እና የቡድን ሥራ በተመለከተ ትልቅ ክፍተት አለ ነው የተባለው፡፡ የሳይንሳዊ አመጋገብ እጦት የተጫዋቾችን አካላዊ እድገት እንደሚገታ ይገልጻሉ፡፡

በዓለም ዋንጫ በተደጋጋሚ የሚሳተፉት ሴኔጋል፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ እና ካሜሩንን የመሳሰሉ ሀገራት አብዛኞቹ ተጫዋቾቻቸው ኳስን በሚገባ በሚያውቁት እና ከፍተኛ ፉክክር ባለባቸው የአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ናቸው፡፡

ዘመናዊ እግር ኳስ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን የእግር ኳስ ክለቦችም ሆኑ ብሄራዊ ቡድኑ ከጥቂት የመንግሥት ተቋማት ውጪ ድጋፍ አያገኙም፡፡ እግር ኳሱ ራሱን የቻለ ገቢ የሚያመነጭ የንግድ ዘርፍ እስካልሆነ ድረስ ከመንግሥት በጀት ብቻ እየጠበቁ የዓለም ዋንጫ መድረክን ማለም አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ካለበት ድቅድቅ ጨለማ ወጥቶ የዓለም ዋንጫ ብርሃን እንዲያይ ከተፈለገ ታሪክን ከማውሳት ባለፈ በሳይንሳዊ መንገድ የታገዘ የረጅም ጊዜ ሥራ ከፌዴሬሽኑ ይጠበቃል፡፡

የታዳጊዎች ሥራ ከወሬ ባለፈ ሜዳ ላይ ሊተገበር፣ አሰልጣኞችም በዘመናዊ እውቀት ሊታነጹ ይገባል፡፡ የ2029ኙን የአፍሪካ ዋንጫ የዝግጅት ሂደት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመን ዛሬ ላይ ትክክለኛውን ዘር ከዘራን፣ የዋሊያዎቹ መለያ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በምድራችን ግዙፉ የእግር ኳሱ መድረክ የዓለም ዋንጫ ላይ የኢትዮጵያ ስም የሚጠራበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር የሰኔ 1   ቀን 2018 ዓ.ም  ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here